መንግስት አቀባባይ የሆነበት የእህቶቻችን ስቃይ
"እኛን ማገዝ ግድ ነው" ዶ/ር ማይገነት
April 1, 2013 08:16 am
“በግል ጥሪ የላከልኝ የለም። ያገባኛል የምትሉ እንድትገኙ የሚል መልዕክት ሰማሁና መጣሁ። የማውቀውንና ያየሁትን እውነት ተናገርኩ። ስቃዩ ከሚነገረው በላይ ነው። የሚነገረውና በተግባር የሚደርሰው በእጅጉ የተለያየ ነው …” በማለት ምስክርነቷን ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ለጀመሩት ወገኖች ማካፈሏን የምትናገረው ወ/ት ዘቢባ ዘለቀ ናት። በንግግሯ ሁሉ መፍትሔ አንዲፈለግ አበክራ ትጠይቃለች።
በቡድን ተደፍረው፣ በመከራ አልፈው፣ በስልክ የሚጠየቀው ተከፍሎላቸው ጂዳና ሪያድ የሚገቡትን እህቶች አግኝታ አነጋግራለች። በቡድን የተደፈሩት እህቶች መንፈሳቸው የተሰበረ ነው። በፍጹም ስነ ልቦናቸው የሚያገግም አይመስልም። ጭው ባለ በረሃ መጫወቻ ሆነው ያሰቡበት ደርሰው ያገኘቻቸው የሚነገራቸውና የሚያጋጥማቸው ፈጽሞ የተለያየ እንደሆነ ለጎልጉል በስልክ አስታውቃለች።
በህጋዊ መንገድ በኤጀንሲ ካገር ከሚወጡት መካከል ድብደባና መከራ የሚገጥማቸው መኖራቸውን፣ ይህ የተለመደ እንደሆነ የጠቀሰችው ወ/ት ዘቢባ “ወገኖቻችን አንዴ ካገር ከወጡ አስተዋሽ ስለሌላቸው እየተገደሉ ነው። ማጣራትና መመርመር ቢቻል ብዙ ጉድ አለው። ወገኖቻችን አልቀዋል። እያለቁ ነው” ብላለች።
ጂቡቲ ደርሰው ወደ የመን የሚያደርጉት ጉዞና የመን ከደረሱ በኋላ የሚያጋጥማቸው መከራ በቃላት የሚገለጽ እንዳልሆነ ያመለከተችው ዘቢባ፣ በየመን ያለው ችግር በወንድሞች ላይም በእኩል ደረጃ ይፈጸማል ብላለች። ከየመን ወደ ወደ ሳዑዲ ለመግባት በእግርና በመኪና በሚደረገው ጉዞ ያለው ፈተና እጅግ ዘግናኝ መሆኑንን በመግለጽ ይህ ሰቆቃ ሊያበቃ የሚችልበትን መንግድ መፈለግ እንደሚያሻ ተናግራለች። ለዚሁም የአቅሟን ለማበርከት የኢትዮጵያ የሴቶች መብት ማዕከል ስብሰባ መገኘቷን አመልክታለች።
አካላቸው እየተሰረቀ በየስርቻው በረሃ ውስጥ የተጣሉትን የሚያውቃቸው ቁጥሩ የጎደለበት ቤተሰብ ብቻ ነው። በባህር ሰምጠው የቀሩትን ማን ቆጥሮ ይጨርሳቸዋል? በክብር ላፈር ሳይበቁ ስደት የበላቸውን ማን ሊዘረዝራቸው ይችላል? የጎደለው እንዲሞላላት ልጇን ስደት የላከች እናት ስብራቷን ማን ይረዳላታል? የብሄር ፖለቲካ ገፍትሮ ለአሰቃቂው ሞት የገፋቸውን የትኛው መዝገብ ዘርዝሮ ይጨርሳቸዋል? እንደ ሸቀጥ ሰዎችን ሸጠው የከበሩት በደምና አጥንት ላይ ቆመው እንደሚደንሱ፣ እንደሚገነቡ፣ እንደሚፈነድቁ፣ አልኮል እንደሚራጩ መንገርስ የማን ፈንታ ነው? ይህ የጎልጉል ጥያቄ ለሁሉም ወገኖች ነው።
ድህነትንና የፖለቲካ ችግርን ተከትሎ ለሚመጣው እንዲህ ያለ ፈተና በግንባር ቀደምትነት መፍትሔ ማፈላለግ ያለበት መንግስት ቢሆንም፣ ባገራችን የሚታየው የተለየ ነው። ገንዘብ ማግኘት ወይም በሌላ ቋንቋ “ተራ ሽቀላ” ከዜጎች በላይ ያስጨነቀው የሚመስለው መንግስት ሰራተኞችን ወደ አረብ አገራት ለመላክ ኮታ አስቀምጦ ውል ፈጽሟል። በኮታው መሰረት ስለመጋዛቸው ይገመግማል።
የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል ሊቀ መንበር ዶ/ር ማይገነት ሽፈራው “መንግስት ዜጎቹን ከመጠበቅ አንጻር ሃላፊነቱን አልተወጣም” በማለት ለጎልጉል በተለይ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። የማዕከሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወ/ሮ ለምለም ጸጋው በበኩላቸው “መንግስት ዜጎቹን ከመጠበቅ ይልቅ አቀባባይ ሆነ። ደላሎች ተፈጠሩ። ፈቃድ ተሰጣቸው። ቢሮ ከፍተውና በየክልሉ በመዘዋወር ወገኖቻችንን እያባበሉ ወደ አረብ አገራት በመላክ ገንዘብ ሰሩባቸው” ሲሉ የዶ/ር ማይገነትን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወገኖች ለወገኖቻቸው ድምጽና ተከራካሪ ለመሆን ወሰኑ። ከአንድ ዓመት በፊት በችግሩ ላይ ለመምከር ተቀመጡ። በሴቶች እህቶቻቸው ላይ የሚደርሰውን በደልና ግፍ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ለሚመለከታቸውና ያገባናል ለሚሉ ሁሉ ለማድረስ ድርጅት ማቋቋምና የውትወታ ስራ መስራት እንዳለባቸው ተስማሙ። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል ተመሰረተ። ዶ/ር ማይገነት እንደሚሉት ማዕከሉ መረጃ የማሰባሰብ፣ ግንዛቤ የማስጨበጥና በአገር ቤትና ከአገር ውጪ በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው በደል በተመለከተ ለአንድ ዓመት ያህል ሲሰራ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ማዕከሉ ባካሄደው ሁለተኛ የምክክር ስብሰባው እንዲህ ያለውን መረን የለቀቀ ግፍ እንዴት ማስቆም ይቻላል? በሚሉና በተለያዩ ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ነበር። ተናጋሪዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ውይይትም ተደርጎ ነበር። ዛሬ ችግሩ አሳሳቢ በሆነበት ወቅት ላይ ሆነን ጥናትና ምክክር መጀመር መልካም ጅምር ቢሆንም ምን ያህል ሊያራምድ ይችላል? የኢትዮጵያ ችግርስ እስከመቼ በወረቀት እየተጠና፣ በተግባር እየተረሳ ይኖራል? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።
ከአገር ይልቅ ለድርጅት ልዕልና ሲመክር የሰነበተው ኢህአዴግ በየአቅጣጫው ስለሚሰማው የኢትዮጵያ ስደተኞች ስቃይ፣ በተለይም በሴት ወገኖች ላይ በሚደርሰው አሳዛኝ ግፍ ትኩረት ሰጥቶ አለመነጋገሩ እያስተቸው ነው። ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ረድፍ ቆመው “ኢህአዴግ ሲወድቅ አማራጭ ነን” የሚሉትም ቢሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው አነጋጋሪ ከሆነ ደግሞ ሰነባብቷል። አንዳንዶቹንም እያስገመታቸው ነው።
ዶ/ር ማይገነት ለጎልጉል በተለይ እንደተናገሩት የሴቶችን ጥያቄ፣ አጀንዳና የፖለቲካ አቋም ትልቅ ጉዳይ በመሆኑ በየትኛውም ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በፕሮግራማቸው ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ። “የሴቶችን መብት መጠበቅ ማለት አገርን የመጠበቅ፣ ራስንም የማክበር ያህል ነው” የሚሉት ዶ/ር ማይገነት፣ የሁሉም የፖለቲካ ተቋማት፣ በሰብአዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች፣ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም ሚዲያዎች ሰፊ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ያሳስባሉ። “እኛን መርዳት ግድ ነው” የሚል ማሳሰቢያም አላቸው።
በስብሳበው ላይ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራርነታቸው የሚታወቁ፣ “የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን” የሚሉና ለወትሮው በተለያዩ አገራዊ ጉባኤዎች ከፊትለፊት የሚታዩ ክፍሎች አለመገኘታቸው ቅሬታ ባይፈጥርም ምክንያቱ ግን ግልጽ አይደለም። ለዚህ መነሻው ምን ይሁን? ለይተው ጥሪ አስተላልፈው ከሆነም በዝርዝር እንዲያስረዱን ለጠየቅናቸው ወ/ሮ ለምለም ጸጋው “ጥሪው አስቀድሞ በመተላለፉ ያልደረሰውና ያልሰማ አካል አለ ለማለት ያስቸግራል” በማለት መልሳቸውን ይጀምራሉ።
ስብሰባውን ስፖንሰር ያደረገውን በሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽንን በማመስገን መልሳቸውን የጀመሩት ወ/ሮ ለምለም፣ በተለያዩ ድረገጾች፣ በሬዲዮ፣ በተለያዩ ቦታዎችና መድረኮች የስብሰባው ቀንና ቦታ ተገልጾ ማስታወቂያና ጽሁፍ መበተኑን ይናገራሉ። አያይዘውም “ማንንም ለይተን አልጠራንም። ለተገኙልን ምስጋናችን ከፍተኛ ነው። ስራችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። አክለውም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ ጥሪውን አክብረው ከመገኘት በተጨማሪ ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ የመሬት ነጠቃን አስመልክቶ ከመኖሪያ ቦታ በግዳጅ ማፈናቀል የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በማብራራት ሰፋ ያለ ንግግር ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ( <
http://www.goolgule.com/mr-obang-metho-addresses-ethiopian-women-conference/> የአቶ ኦባንግ ሙሉ ንግግር እዚህ ላይ ይገኛል)
አንዳንድ አካልት ለምን “የሴቶች” በሚል ለብቻቸው ድርጅት ለምን መሰረቱ በሚል እንደሚጠይቁ ያስታወቁት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዋ “እስከዛሬ ከልምድ እንደታየው ከፖለቲካው ውጪ እኛ በጀመርነው መንገድ ሲሰራ አይታይም። የሴቶች እህቶቻችን ስቃይ ከልክ እያለፈ በመሄዱ ጉዳዩን በባለቤትነት ለማንቀሳቀስ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ በማተኮር እንደምንሰራ ሁሉም ወገን ሊረዳ ይገባዋል” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ከተለያዩ አገራት በድህነት የተነሳ ስራ ፍለጋ ወደ አረብ አገራት የሚጓዙ መኖራቸውን ያወሱት ወ/ሮ ለምለም “የሌሎች አገር ዜጎች ከመንግስታቸው ጥበቃና ክትትል ሲደረግላቸው የእኛ ወገኖች ግን ተረስተዋል፣ አስታዋሽ የላቸውም። ኤምባሲ በር ላይ ተጎትታ ስትሞት እንኳ ለምን የሚል ወኪል ማግኘት አልተቻለም። የችግሩ ስፋት ጊዜ የሚሰጥ ባይሆንም አሁን ጀምረናል እንገፋበታለን። ሁሉም ወገን ድጋፍ ሊሰጠን ይገባል። ደግሞም ግድ ነው” ብለዋል።
ከገጠር ያልተማሩትን ሰብስቦ የሚልካቸው ማን ነው? ደላላ ሆኖ ገንዘብ እየተቀበለ ወገኖቹን በገንዘብ የሚለውጠው ማን ነው? ሁሉንም ስራ በህጋዊነት ፈቃድ ወስዶስ የሚሰራው ማን ነው? ችግሩ የባሰባቸው የማይታሰበውን ያደርጋሉ፣ ችግርን መጠቀሚያ በማድረግ የራሳቸውን ወገኖች ለብር ሲሉ ለመከራ የሚዳርጉ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የተማጸኑት ወ/ሮ ለምለም “እንዲህ ያለውን አስነዋሪ ግፍ በገዛ እህቶቻችን ላይ እንፈጽማለን? እንደዚህ የምታደርጉ ወገኖች እባካችሁን የምትሰሙት የወገኖቻችሁ ስቃይና አሰቃቂ ዜና በሁሉም በእህቶቻችሁ ላይ እንደሚፈጸም ቁጠሩት። ይብቃችሁ” የሚል ጥሪ በማዕከላቸው ስም አቅርበዋል።
<
http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2013/04/women-conference-e1364792669282.jpg> <
http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2013/04/maigenet-shiferaw.jpg>
ዶ/ር ማይገነት ሽፈራው
<
http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2013/04/obang-metho.jpg>
አቶ ኦባንግ ሜቶ
<
http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2013/04/lemlem-tsegaw.jpg>
ወ/ሮ ለምለም ጸጋው
Received on Mon Apr 01 2013 - 10:33:09 EDT