<
http://ethiopianewsforum.com/viewtopic.php?t=61006&p=370484#p370484> የፖለቲካ ካሊፕሶ (ተስፋዬ ገብረአብ)
<
http://ethiopianewsforum.com/viewtopic.php?p=370484&sid=6bad663afcdbdaf3e1b9ba55ca5b964e#p370484> Postby ተስፋዬ ገብረአብ » Today, 05:52
13/09/2013
ለኢትዮጵያ የ2006 አዲስ አመት እንኳን አደረሰን!
በተጨማሪ ለኤርትራ የቅዱስ ዮሃንስ በአል እንኳን አደረሰን!
በኢትዮጵያና በኤርትራ የምትገኙ የበአሉ ባለቤቶች ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ!
እንዲህ ለኢትዮጵያና ለኤርትራውያን በዘዴ ሰላምታ ማቅረቡን ከቴዲ አፍሮ ነው የተማርኩት። ቴዲ ገና በወጣትነቱ የፖለቲካ ካሊፕሶ ገብቶታል። ቴዲ አፍሮ ባለፈው ሃምሌ ወር አምስተርዳም ላይ ኮንሰርት አቅርቦ እንደነበር ሰማሁ። እኔ እንኳ ለእረፍት ወጣ ብዬ ስለነበር አመለጠኝ። እንደሰማሁት ከ40% በላይ ታዳሚዎቹ ኤርትራውያን ነበሩ። የኤርትራን ባንዴራ ይዘው ቀወጡት አሉ። እሱም “ፊዮሪና ጓል አስመራን” ደጋግሞ ዘፈነላቸው። ዘፍኖ ሲጨርስ የኤርትራን ባንዴራ ሸለሙት (አለበሱት?) ብለው ነገሩኝ። ድንቅ ነው። ቴዲ ወደ አስመራ ብቅ ብሎ ኮንሰርት ቢያቀርብ ርግጠኛ ነኝ አስመራ ስታድየም አይበቃውም። እንዲህ ያለውን የፖለቲካ ካሊፕሶ ሄለን መለስም ብትሞክረው አይከፋም። ከጋሽ ግርማ ይልቅ ሄለን እና ቴዲ አዲሳባ - መቀሌ - አስመራ አንድ ዙር ጉዞ ቢያደርጉ ተአምር መፍጠር የሚችሉ ይመስለኛል። መቼም የድንበር ውዝግቡን ባይፈቱትም፣ ያንዣበበውን የጥላቻና የጦርነት ደመና መግፈፍ አይሳናቸውም።
ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከትናንት በስትያ አንድ ነጣላ ቀልድ መልቀቃቸውን የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ላይ ሰማሁ። አስመራ ለመሄድ ማሰባቸውን ተናገሩ። ጋሽ ግርማ እንድችው እንደቀለዱ የስልጣን ዘመናቸውን ጨረሱ። ከዚህ ቀደም ቢያንስ ሶስት ጊዜ እንደተኮረኮረ ሰው አስቀውኛል።
አንድ ጊዜ 12 ሙሉ ሱፍ ልብሳቸውን ለተቸገሩ ሰዎች ማበርከታቸው ተሰማ። በመሰረቱ የተቸገረ ሰው የእሳቸው ልብስ ሊበቃው አይችልም። አስጠብበው ይለብሱታል ቢባል እንኳ፣ በጣም ሞራል ይነካል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ፓርላማ ላይ ቀርበው፣
“ቆሜ የማልናገረው በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ነው” ብለው ይቅርታ ጠየቁ።
እንቅልፋሙ የወያኔ ፓርላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቡ ሳቀ። ደግ አደረጉ! ቁጭ ከማለት መሳቅ ይሻላል። ለነገሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቤቴ ስለሌለኝ ይህን ትርኢት በቀጥታ አልሰማሁትም ነበር። ኤልያስ ክፍሌ መቼም ክፉ ነው። “ፕሬዚዳንት ግርማ ይቅርታ ጠየቁ!” ብሎ ዜና ሰራ። “ምን ይሆን?” ብዬ ሰፍ ብዬ ብገባ ነገሩ ሌላ ነበር።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋሽ ግርማ፣ “ፕሬዚዳንት እንደምሆን ወላጅ እናቴ ህልም አይታ ነበር” ማለታቸውን ሰማሁ።
ይኸው እንግዲህ በመጨረሻ የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር ውዝግብ ለመሸምገል ወደ አስመራ መጓዝ እንደሚፈልጉ ሰማን።
የሚገርመው የያዙት የመፍትሄ ሃሳብ፣ “በአከራካሪው መሬት ላይ የሚገኘው ህዝብ የሚመርጠውን መፈፀም ይገባል” የሚል ነው። ይህን ለሻእቢያ ለመንገር አስመራ ድረስ መጓዝ አያስፈልጋቸውም። ሰው ቢያማክሩ ይሻላቸዋል። በርግጥ አስመራ የሚገኙ የቀድሞ ወዳጆቻቸውን ለመጠየቅ፣ የባለቤታቸውን ዘመዶች ለማየት፣ እግረመንገድ ደግሞ ምፅዋ ብቅ ብለው አሸዋ ላይ ለመቀበር ቢጓዙ አይከፋም።
ባሳለፍነው አሮጌ አመት በርካታ የፖለቲካ ካሊፕሶ ተመልክተናል።
የመለስ ራእይ መለስን ሲደበድብ ታዝቤ ከልቤ ተገርሜያለሁ። “የመለስን ራእይ እናስፈፅማለን!” እያሉ ከፍ ባለ ድምፅ ቢናገሩም መለስ ቁልፍ ቦታ ያስቀመጣቸውን ቁልፍ ሰዎቹን ይመነጥሯቸው ይዘዋል። መለስ የመቃብር ሳጥኑን በርግዶ ቢነሳ መጀመሪያ የሚፈፅመው ነገር ቢኖር፣ አዜብን ወደ ኤፈርት ይመልሳታል። ገብረዋህድን ከእስር በመፍታት ስልጣን ጨምሮ ይሰጠዋል። ወልደስላሴን በጌታቸው አሰፋ ቦታ ያስቀምጠዋል። በመጨረሻ አባይ ፀሃዬን ወደ እስርቤት ይልከው ነበር።
ህወሃት የእርስበርስ ጦርነት በማድረግ ላይ መሆኑን እየሰማን ሰንብተናል። ጦርነቱ በመቀሌ እና በአዲሳባዎች መካከል መሆኑ ተሰምቶአል። የአዲሳባዎቹ መቀሌ ላይ እጅ አላቸው፡፤ የመቀሌዎቹም በአንፃሩ አዲሳባ ላይ መረባቸውን ዘርግተዋል። ብአዴን ቋሚ የምክትልነት ወንበሩን ለደመቀ መኮንን መሰጠቱን ካረጋገጠ በሁዋላ “ድርሻዬን አጊኝቻለሁ” ብሎ የህወሃትን የርስበርስ ጦርነት ዳር ላይ ቆሞ ይመለከታል። ኦህዴድ አለ ይባላል እንጂ በህይወት የለም። እነርሱም “አልሞትንም!” ብለው አልዋሹም። ሌንጮ እና ዲማ ሸገር ገብተው በወደቀ ዋጋ እስኪገዟቸው እየጠበቁ ይመስላሉ። ህወሃት ከሚያንገላታቸው ይሻላቸዋል። የፖለቲካው ካሊፕሶ በዚህ አላበቃም። እመለስበታለሁ…
የሰላም አዲስ አመት ያድርግልን።
(በነገራችን ላይ “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለ መፅሃፍ ፅፌያለሁ። 418 ገፆችና 39 ምእራፋት ይዞአል። ለመግዛት ወይም ለማከፋፈል የምትፈልጉ ነፃነት አሳታሚን ጎብኙ። በትክክል ለገበያ የሚቀርብበትን ቀን፣ የሚሸጡባቸውን ከተሞች ዝርዝር በድረገፃቸው ላይ እንደሚገልፁ ነግረውኛል።
http://www.npabooks.com)
Received on Fri Sep 13 2013 - 20:59:14 EDT