Ethsat.com: ኢትዮጵያ ለወሲብ ንግድና ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ አገር ሆናለች ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ
ኢትዮጵያ ለወሲብ ንግድና ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ አገር ሆናለች ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ
30.12.2014
ታኀሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው የ2014 ሪፖርት ኢትዮጵያ ለግዳጅ ሥራ፣ ለወሲብ ንግድና ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተዳረጉ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት መነሻ፤ በተወሰነ ደረጃም መዳረሻ አገር ናት ብሎአል።
አዲስ አበባ የሚገኘው ዋና የገበያ ማዕከል ከአፍሪካ ቀዳሚው የወሲብ ንግድ ቤቶች መገኛ ነው የሚለው ሪፖርቱ፣ ዕድሜያቸው እስከ 8 ዓመት የሚሆኑ ልጃገረዶች በነዚህ ቤቶች በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተዋል ይላል።
ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ከኢትዮጵያ ውጪም በተለይ በጂቡቲ፣ደቡብ ሱዳን እና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት እና በሴተኛ አዳሪነት እንዲሰሩ እንደሚገደዱ፣ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወንዶች ደግሞ ጂቡቲ ውስጥ በሱቅ ሰራተኝነት፣ በተላላኪነት፣ በቤት ሰራተኝነት፣ በስርቆት እና በጎዳና ላይ ልመና ለግዳጅ ሥራ ተዳርገዋል ብሎአል።
በርካታ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲሰደዱ ጂቡቲ፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ወይም የመንን እንደመሸጋገሪያ ይጠቀማሉ የሚለው ሪፖርቱ፣አንዳንዶቹ ሊሄዱ ካሰቡበት አገር ሳይደርሱ እንደመሸጋገሪያነት ባረፉበት አገር ተይዘው ለብዝበዛ፣ለእስራት፣ለግዳጅ ስራ እና ለመታገት ይዳረጋሉ ብሎአል።
በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት፣ ደሞዝ ክልከላ፣ እንቅልፍ መነፈግ፣ የፓስፖርት መያዝ፣ በቤት ውስጥ መታገት እና ግድያን ጨምሮ አስከፊ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስራ ፍለጋ ከአገር ከወጡ በኋላ፣ በወሲብ ንግድ ቤቶች፣ በማዕድን ማውጫ ቦታዎች፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ነዳጅ ዘይት ማውጫ አካባቢዎች ለወሲብ ንግድ ብዝበዛ ይዳረጋሉ ብሎአል።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀን እስከ 1500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውን በሕጋዊ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ቢገልጽም፣ ይህ ቁጥር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ30 እስከ 40 በመቶ ብቻ የሚወክል ብሎአል። ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች በሕገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይንም ስደት እንደሚዳረጉ ጠቅሷል።
መንግስት በአስቀጣሪ ኤጀንሲዎች ላይ ክልከላ ቢጥልም ክልከላውን ተከትሎ በሱዳን በኩል የሚደረግ ሕገወጥ የሰራተኞች ፍልሰት መጨመሩን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሪፖርት ጠቁሟል። እ.ኤ.አ. ከሕዳር 2013 ጀምሮ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከ163 ሺ 000 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ያስወጣ ሲሆን ከነዚህም መካከል ከ94 ሺ 000 የሚበልጡት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ወንዶች፤ ከ8 ሺ 000 የሚልቁት ደግሞ በእረኝነት እና በቤት ሰራተኝነት የተቀጠሩ ሕጻናት ናቸው ብሎአል።
መንግሥት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ የተቀመጡትን ዝቅተኛ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ባያሟላም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል የሚለው ሪፖርቱ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 106 ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የፈጸሙ ወንጀለኞች ሕግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ ያደረገ ሲሆን፤ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች መጠለያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አድርጓል ሲል አትቷል።
መንግስት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑትን ጨምሮ ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ከሌሎችም አገራት የተባረሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማመቻቸት ስራ ቢሰራም፣ የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ሳያደርግ የውጭ አገር ድርጅቶች ይወጡት በማለት ሃላፊነቱን ለእነሱ መተውን ገልጿል።
መንግስት ውጭ አገር በሚገኙ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች የሰራተኛ ጉዳዮችን የሚመለከቱ አታሼዎችን አለመመደቡ፤በኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች በሚሰጡ የዜጎች ደህንነት አገልግሎቶች ላይም ማሻሻያ አለማድረጉም ተጠቅሷል፡፡
መንግስት የሕጻናት የወሲብ ንግድን እና ሌሎች በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን በሕግ ማስከበር፣ ከለላበመስጠት እና በመከላከል በኩል በቂ ሥራ አልተሰራም በሚል ስቴት ዲፓርመንት ትችት አቅርቧል።
Received on Tue Dec 30 2014 - 18:09:58 EST
Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved