የማልረሳት አበሻ
03.01.2015
(ይህን ታሪክ የሰማሁት ከኒውዮርክ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በአውቶብስ በመጓዝ ላይ ሳለሁ ሲሆን፤ የታሪኩ ባለቤት አውቶብሱ ላይ ተሳፍሮ ነበር። እኔ ባላውቀውም እሱ በመፅሃፎቼ ያውቀኝ ኖሮ በቀላሉ መግባባት ቻልን። ወግን ወግ እያነሳው ብዙ ተጨዋወትን። እነሆ! የመንገድ ላይ ወዳጄ እንደዋዛ ያጫወተኝን ታሪክ በኔው ብእር ልተርክላችሁ...)
•••
በሰማንያዎቹ አጋማሽ አንዲት አሪፍጓደኛ ይዤ ነበር። አስታውሳለሁ! ነጋ - መሸ ተያይዞ መክነፍ ብቻ ሆነን ነበር። በቁሜ ገነት የገባሁ እስኪመስለኝ የፍቅርስሜቷን ሁሉ ያለ ስስት ሰጠችኝ። ስራዬን እስክዘነጋ ሆንኩ። አሳቤ ሁሉ ስለርሷ ሆነ። ደግነቱ በወቅቱ የምሰራበት የኮንስትራክሽን ድርጅት ስራው ቀዝቅዞ ‘የት ነበርክ? በየት ወጣህ?’ ብሎ የሚቆጣጠር አለቃ አልነበረኝም።
ከጥቂት ወራት በሁዋላ ቁጭ አድርጌ በቁምነገር አናገርኳት፣
“ብንጋባ ምን ይመስልሻል?”
በጥያቄዬ የተገረመች መሰለች፣
“ምነው?” አልኩ ያጠፋሁ መስሎኝ።
“መጠየቅህ ገርሞኝ ነው። እኔ እንደተጋባን ከቆጠርኩት ቆይቻለሁ።” አለች።
የትውልድ አገሬን ላሳያት ቃል ገብቼላት ነበር። የሚመች ጊዜ ስንጠብቅ ከቆየን በሁዋላ በክረምቱ ወራት ማብቂያ ላይ፤ በእለተ ቅዳሜ ማለዳ ተያይዘን ከአዲስአበባ ወጣን። ሽው አልን ወደ ምስራቅ። እሷ ከአዲስአበባ ወጥታ አታውቅም ነበር። እኔ ያን ጊዜ 27 ስሆን፣ እሷ 19 ነበረች። በመንገዳችን ላይ የሞቀ የፍቅር ወግ እያወጋን ነጎድን። ወጋችን ማቋረጫ አልነበረውም። ፍፁም የተዋሃሃደ ስሜት ነበረን። ያበደ ፖለቲካም ሆነ የከረረ የሃይማኖት ልዩነት እንኳ ሊለያየን በማይችልበት ሁኔታ በጣም ተግባብተን ነበር። ሎሜ ልንደርስ አካባቢ የፖለቲካ ወግ ቀላቀለች፣
“የኛ ዘመን ፖለቲካ ሲያስጠላ?” አለች።
“ምነው?”
“ወሬ ሁሉ ስለ ዘርሆኖአል። ገበያ ብትሄድ፣ ዩንቨርስቲ ብትገባ፣ መፅሄቱ፣ ጋዜጣው፣ የትም የትም ሄደህ ስለ ዘር ነው።አማራ - ኦሮሞ - ጉራጌ - ትግሬ - የማናውቀውን አመጡብን። አሁን ለምሳሌ እኔ አማራ ነኝ። አንተ ምን እንደሆንክ አላውቅም።ከስምህ ተነስቼ ስገምት ግን ያው ኦሮሞ ልትሆን ትችላለህ።የፈለገውን ብትሆን ምን ልዩነት ያመጣል? ወደድከኝ፣ ወደድኩህ። የሚያለያየን ነገር የለም። በቃ!ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። ከዚያ ካለፍን አፍሪቃዊ ነን። በመጨረሻ ደግሞ ሰዎች ነን።”
አባባሏን ደገፍኩት፣
“ያልሽው እውነት ነው። ከፍቅር በላይ ሃያል ነገር የለም። ፍቅር ከሃይማኖት እና ከጎሳ በላይ ነው። በዚህች ደቂቃ እንኳ ስለ ዘር ወሬ በመነሳቱ ስሜቴ ጨፈገገ...”
መኪናዬን ዳር አቆምኩና ሳምኳት። ተጠመጠመችብኝ። ከንፈሮቿ ውስጥ እንደኤሌክትሪክ የሚነዝር ከፍተኛ ሃይል ያለ ይመስላል። ትኩስ ነበረች። ከንፈሮቻችንን ማላቀቅ አቃተን። እሷ እኔ ውስጥ ገባች። የጎን አጥንቴ መሆኗን እስካምን ድረስ ስጋዬና አጥንቴ ውስጥ ገብታ ተደባለቀች። ከመኪናው ወጣንና አስፓልቱ ዳር የለመለመው ሳር ላይ ቁጭ አልን። ከግራና ከቀኝ ውሃ የጠገበ የቱለማዎች ሁዳድ በሰፊው ተዘርግቶአል። የገብስና የአተር ሰብል ምድሩን አልብሶታል። በፍጥነት ከሚያልፉ መኪኖች በቀር የሚታይ ሰው አልነበረም። ሳሩ ላይ ጋደም እንዳልን መሳሳሙን ቀጠልን። በተለይ በመሳቅ ላይ ሳለች ስስማት አእምሮዬን ልስት ምንም አይቀረኝ። ከንፈሯን ሳይሆን ሳቋን ነበር የምስመው። ከዚያ ወዲህ የሴት ልጅን ከንፈር በሁለት ከፍዬ አየዋለሁ። አንደኛው የሚስቅ ከንፈር ሲሆን፤ ሌላው ያኮረፈ ከንፈር ነው።እነሆ! መሳሳሙ የሚጠገብ ባለመሆኑ እረፍት ለማድረግ ተገደድን።
በጀርባችን ሳሩ ላይ ጋደም እንዳልን ጣፋጭ ወግ አመጣች፣
“ስንት ልጆች እንድወልድልህ ትፈልጋለህ?”
“እግዜር ከፈቀደ አራት ልጆች።” ስል መለስኩ፣ “...ማለትም ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች...”
ጮኸችና በስሜት ተናገረች፣
“ልክ እኔ የምፈልገውን ተናገርክ። የሰው ፍላጎት እንዲህ ሊገጣጠም ይችላል?”
በፍፁም ማስመሰል አልነበረባትም። ቅን ነበረች። ተንኮል አታውቅም። ቀልድ ትወዳለች። መሳቅ ትወዳለች። ሃይል አላት። ሰፊና በፍቅር ያበበ ቤተሰብ የመመስረት ፍላጎቷ ከፍተኛ ነበር። እኔም ብሆን ስሜቴ የእውነት ነበር። ለጊዜያዊ ደስታ የማደርገው ቴአትር አልነበረም። ከልቤ ወድጄያት ነበር። ላገባት ወስኜ ነበር። በርግጥም ቀለበት ለማሰር ጭምር በቅተን ነበር። እስከዚህ አስተማማኝ መሰረት የነበረው ፍቅራችን ግን ለጋብቻ አልበቃም።ጋብቻው ባይሳካም ያቺ ልዩ ልጅ ከአእምሮዬ ጠፍታ አታውቅም። በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ፈፅሞ ሊረሱ የማይችሉ ጥቂት በጎም ሆነ ክፉ ደቂቃዎች ምንጊዜም ይኖራሉ።
አስፓልቱ ዳር ጋደም ብለን ስናወጋ የክረምቱ አየር ልብ ያነሆልል ነበር። ደካማ ፀሃይ ከአናታችን እየተሽከረከረች የተመጠነ ሙቀቷን እየመገበችን ነበር።በመካከሉ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብላ አንድ ነገር ሹክ አለችኝ።አላመነታሁም።የጠየቀችኝን ለመፈፀም እጇን ይዤ ተነሳሁ።
ከፊታችን ወደ ተዘረጋው የገብስ ማሳ ገባን። ምቹ ቦታ መረጥኩና የገብሱን ሰብል እየነቀልኩ የታረሰውን አባጣ ጎርባጣ መሬት በጫማዬ ደለደልኩት። በተደለደለው መሬት ላይ የገብሱን ነዶ እየነቀልኩ እንደ ምንጣፍ አነጠፍኩት። በጫማ የተረገጠው የገብስ ነዶ ትኩስ ጣእም ያለው ሽታ በማፍለቁ፣ ሽቶ የተርከፈከፈበት አረንጓዴ ምንጣፍ መሰለ። ቁጭ ስንል በዙሪያችን በገብስ ተከበን ነበር። በነፋሱ የሚወዛወዙት የገብስ ነዶዎች የሚሰግዱልን መሰሉ።
ምን ያህል እንደቆየን እንጃ። ከአንድ ሰአት በላይ ሊሆን ይችላል። በጣም ግሩም ነበር። ሌላ ልዩና ቅዱስ አለም ውስጥ ገብተን ነበር። ሁሉን ፈጽመን ፈፃፅመን ከማሳው በዝግታ ወጣን። ስንወጣ አስፓልቱ ዳር ከቆመች መኪናችን አጠገብ ረጅም መጥረቢያ ትከሻው ላይ ያነገበ ገበሬ ቆሞ ተመለከትን። ሁለታችንም በቁማችን ቀዘቀዝን። በጭንቀት እጄን ያዘችኝ። እኔም አጥብቄ ያዝኳትና ሞራል ሰጠሁዋት፣
“ላበላሸነው ገብስ ገንዘብ እንከፍለዋለን። ከዚያ ያለፈ ችግር የሚኖር አይመስለኝም።”
በዝግታ ወደ መኪናችን ተራመድን። ገበሬው በግራ እጁ የአተር እሸት ጥቅልል ጠምጥሞ ይዞ ነበር።አጠገቡ ከመድረሴ በፊት የሞቀ ሰላምታ አቀረብኩለት። የኦሮምኛ ቅላፄ በሚጫነው አማርኛ ለሰላምታችን ምላሽ ከሰጠ በሁዋላ፣
“አተር እሸት ትወዳላችሁ?” ሲል ጠየቀ።
“እንዴታ!” ስል መለስኩ።
እጁን ዘረጋልን። ሁለታችንም በአክብሮት የእሸት ስጦታውን ተቀበልን። በተዝናና መንፈስም እየጠረጠርን መብላት ጀመርን። በዚህ ቅፅበት እጄን ወደ ገንዘብ መያዣ ቦርሳዬ በመስደድ አስር ብር አወጣሁና ዘረጋሁለት። ለአተር እሸቱ ሳይሆን ላበላሸነው የገብስ ነዶ በሚል ነበር። ገበሬው ግን አልተቀበለም፣
“ወንድሜ! ለምኑ ነው?” ሲል ኮራ ብሎ ጠየቀ። እጆቹን ግራና ቀኝ ዘረጋጋ። ወደ ሰማይ ጭምር እያመላከተ ተናገረ፣ “...ይሄ ሁሉ እርሻ የኔ ነው። ብዙ ከብቶችም አሉኝ።”
ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ፣
“ጥቂት የገብስ ነዶ አበላሽተናል። ይቅርታ።” አልኩ።
“አይቻለሁ።” አለ ፈገግ ብሎ፣ “...ምንም አይደል። ልጆች ናችሁ...”
እንደገና ጥቂት ዝምታ፣
“እናመሰግናለን።” አልኩ።
ፈገግታ አሳየን። እኛም ተመሳሳዩን መለስንለት። እና ተሰናብተነው መንገዳችንን ቀጠልን። መስኮቶችን ከፋፈትን። በግራና በቀኝ ከተዘረጋው ማሳ ከነፋስ ተቀላቅሎ የሚመጣውን ጥዑም መአዛ እየተመገብን ነጎድን።አዎን መኪናችን ወደ አዋሽ ከነፈች...
• • •
የመንገድ ላይ ወዳጄ የፍቅር ታሪኩን ተርኮ ሲያበቃ በጉጉት ጠየቅሁት፣
“ለምን ተለያያችሁ? በምን ምክንያት ሳትጋቡ ቀራችሁ?”
ገፅታው ላይ ቅሬታ በግልፅ እየተነበበ ሊያስረዳኝ ሞከረ፣
“በኔ በኩል የፖለቲካውን ተፅእኖ አልቻልኩትም። ከከበበኝ ህብረተሰብ ተነጥዬ መኖርና ማሰብ አልቻልኩም። ዋናው ጉዳይ በርግጥ ሌላ ነው። እንደው በቀላሉ ግን የምንወልዳቸው ልጆች የሚገጥማቸውን ፈተና ሳስብ ገና ሳይወለዱ አዘንኩላቸው። ቀደም ሲል ተቀላቅለው የተወለዱ ልጆች የገጠማቸውን የስነልቦና ችግር እያየሁ፣ በተመሳሳይ ሌሎች የሚጎዱ ልጆችን ወደዚህች አለም ማምጣት ራስ ወዳድነት ሆኖ ተሰማኝ። እና ምንም ማድረግ አልቻልኩም። እየወደድኳት ተለየሁዋት።”
“በቂ ምክንያት አይደለም።” ብዬ ተቃወምኩ።
“ምክንያቱ ለኔ በቂ ሆኖ ከተገኘ በቂ ነው። ለሌሎች በቂ ላይሆን ይችላል። ስለራሴ ነው የነገርኩህ።”
“አሁን አግብተሃል?”
“አግብቻለሁ። ልጆች አሉኝ።”
“ሚስትህ ኦሮሞ ናት?”
“ልክ ነው። ኦሮሞ ናት።”
“እንዳሰብከው ሆነልህ? አሁን ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ነህ?”
ጥቂት እያሰበ ቆየና እንዲህ አለ፣
“ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ነኝ ልልህ አልችልም። እንደማስበው ግን ህይወት ማግኘትና ማጣት ነው። አሁን ባለኝ ትዳር ያገኘሁት ጥቅም አለ። የመጀመሪያ እጮኛዬን ባለማግባቴ ያጣሁት ብዙ ነገርም አለ። በጥቅሉ በህይወት ላይ የተሟላ ደስታ ሊኖር አይችልም።”
“ከልጆቹ ጉዳይ ባሻገር ሌላ ምን ምክንያት ነበረህ?” ስል ጠየቅሁት።
“በአመለካከት እንደማንግባባ ተረዳሁ...”
“በምን አጀንዳ ላይ?”
“እንደነገርኩህ በመጀመሪያው ላይ ጥሩ ነበርን። ሁዋላ ግን ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚለው ማንነት ላይ የአተረጓገም ልዩነት መጣ። ‘እሷ የሚሰማት አይነት ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እኔ ለምን የለኝም?’ ብዬ ራሴን ስጠይቅ፤ እሷ ኢትዮጵያዊነት የምትለው አስኳሉ አማራዊነት መሆኑን አወቅሁ። ይህን ጊዜ ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አለመሆናችንን ተረዳሁ። መጋጨታችን እንደማይቀር ገመትኩ። ልጆች ከወለድን ለልጆቹ ሲባል አንዳችን መለሳለስ ሊኖርብን ነው። ሳስበው የመለሳለሱ እጣ እኔ ላይ ነው የሚወድቀው። እንደማልችል ስለተረዳሁ መለያየቱን መረጥኩ...”
ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ፣
“ምን አስተያየት አለህ?” ሲል ጠየቀኝ።
“አንተ ጥልቅ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ባትገባ ጥሩ ባልና ሚስት ይወጣችሁ ነበር። ከነቃህ በሁዋላ ግን እንዳልከው አስቸጋሪ ነው። ያጫወትከኝ የፍቅር ታሪካችሁ ደስ ይል ስለነበር እንዳጀማመርህ ደግ፣ ቅን እና ቅዱስ ሆነህ ብትቀጥል እመርጥ ነበር።” አልኩ።
በከፍተኛ ድምፅ ሳቀ፣
“ምናሳቀህ?”
“በአበሻ ፖለቲከኞች አተረጓገም ደግነትና ቅንነት ‘ሞኝነት’ ማለት ስለሆኑ አልፈልጋቸውም።”
ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ፣
“ለመሆኑ ስለ ልጅቱ ወሬ አለህ?” ስል ጠየቅሁት።
“አግብታ ልጆች መውለዷን ሰምቻለሁ።”
“የት ናት?”
“እዚሁ አሜሪካ - አሪዞና ክፍለሃገር አለች...”
ሳላስበው ረጅም ሳቅ ሳቅሁ።
“ምነው?” አለ ደንገጥ ብሎ።
“በመጨረሻ ሁለታችሁም ልጆቻችሁን ለአሜሪካ አስረከባችሁ...” ብዬ ቀለድኩበት።
የመሳቁ ተራ የሱ ሆነ። አስተያየት ግን አልሰጠም።
“ልታገኛት አልሞከርክም?” ስል ጠየቅሁት።
“አልሞከርኩም።” አለ ትክዝ ብሎ፣ “...ዘረኛ እንደሆንኩ ስላመነች ላገኛት አልሞከርኩም። በወቅቱ እኔ የተገነዘብኩትን እውነት ላስረዳት ሞክሬ አልተሳካልኝም።”
“በመለያየታችሁ ፀፀት የለብህም?”
እንደገና ተከዘ፣
“አንዳንድ ጊዜ ፀፀትና ትዝታ ተቀላቅለው እየመጡ ይረብሹኛል። ሌላ ጊዜ ውስጤ ያለው ትዝታ ወደ ፀፀት ሊቀየር ይፈልጋል። እርግጥ ነው፣ ልጅቱን ገፍቻታለሁ። በማታውቀው ፖለቲካ ምክንያት ተጎድታለች። እኔም የፍቅር ጀግና አለመሆኔ ይሰማኛል። የወሰድኩት ርምጃ ስህተት ነው ብዬ ግን አላምንም። በርግጥ መርዶውን ስነግራት የተሰማትን ድንጋጤ ሳስታውስ ዛሬም ድረስ ጥሩ አይሰማኝም። ከርሷ ጋር ያሳለፍኳቸውን ጊዜያት በማስታወስ ተመልሰው እንዲመጡ ማንኛውንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆንኩ መስሎ የሚሰማኝ ጊዜ አለ። ይህ ስሜት ግን ዘላቂ አይደለም። ወዲያው በንኖ ይጠፋል።ሳልጠነቀቅ ያለገደብ ማሰብ እንደምፈልግ ርግጠኛ ነኝ። ለምወዳት ልጅ ስል የማሰብ ነፃነቴ ላይ ገደብ ማበጀት አልፈልግም። ስለዚህ ‘ውሳኔዬ ልክ ነበር’ እላለሁ።”
እንደገና ከአፍታ ዝምታ በሁዋላ ጥቂት ጨመረበት፣
“ከሷ ከተለየሁ ረጅም ጊዜ አልፎአል። ከማግባቴ በፊት እንደማንኛውም ወንድ ብዙ አይቻለሁ።እጅግ ውድና ምቹ አልጋዎችን አውቃለሁ። ምርጥ ቆነጃጅት ጓደኞች ነበሩኝ። ከዚያች የ19 አመት ልጅ ጋር በተጎዘጎዘ የገብስ ነዶ ላይ የፈፀምኩት ፍቅር ግን ወደር አልባ ሆኖ አሁንም በትዝታዬ ውስጥ ነግሶአል።”
የቅዳሜማስታወሻ - ተስፋዬገብረአብ (Gadaa), January 1 2015 Email: ttgebreab@gmail.com