Ethsat.com: የመንግስት ካድሬዎች በኦሮምያ የተነሳውን ግጭት የብሄር ግጭት ለማስመሰል ዘመቻ መጀመራቸው ታወቀ።

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 7 May 2014 22:59:10 +0200

የመንግስት ካድሬዎች በኦሮምያ የተነሳውን ግጭት የብሄር ግጭት ለማስመሰል ዘመቻ መጀመራቸው ታወቀ።

May 7, 2014

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከኦህዴድ ምንጮች ባገኘው መረጃ ተንተርሶ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ልዩነትን በመዝራት ሁለቱን ታላላቅ ብሄሮች ለማጋጨት ያቀዱትን ሴራ ይፋ ካደረገ በሁዋላ፣ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተሰማሩ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች እንዲጋጩ ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

በሃሮማያ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች አንዱን ብሄር የሚያጥላሉ ንግግሮች ሆን ተብሎ ተልእኮ በተሰጣቸው ካድሬዎች እየተነገሩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተመሳሳይ ልዩነት ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

ካድሬዎቹ በቅርቡ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የስፖርት ቬስቲቫል ላይ አማራ ኦሮሞዎችን ተሳድቧል የሚል ወሬ በመንዛት የኦሮሞዎችን ስሜት ለመቀስቀስ እየሞከሩ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ህወሃት ሆን ብሎ ያሰማራቸው ጥቂት ካድሬዎች በባህርዳር ያሰሙትን ዘለፋ ሆን ብሎ የመላው አማራ ህዝብ አቋም አድርጎ በማድረግ ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሰው ህወሃት ፣ የአብዛኛውን ህዝብ ትኩረት ባያገኝም በወጥመዱ ውስጥ የገቡ ጥቂት ተማሪዎች፣ የህወሃትን አጀንዳ እያራገቡ መሆኑን ምንጫችን ገልጿል።

በአገራችን እየታየው ያለው ሁኔታ አስፈሪ መሆኑን እና ህዝቡ ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ እንደኖረው ሁሉ አሁንም በካድሬዎች ቅስቀሳ ሳይታለል ጊዜውን በጥንቃቄ ማለፍ እንደሚገባ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በኢሳት ላይ እየገለጹ ነው።

ከቀናት በፊት አዳማ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የኦህዴድ ስብሰባ እውቁን የሰብአዊ መብት ተማጋቹን አርቲስት ታማኝ በየነን የሚዘልፉና አማራውን የሚያንቋሽሹ ንግግሮች ሲደረጉ እንደነበር እንዲሁም በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ የዘር ጉዳይ አድርጎ ለማቅረብ አመራሮች የማሳመን ስራ ሲሰሩ እንደነበር የኢሳት ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በሚዳቀኝና ባለሚ አካባቢዎች ትናንት በበርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፣ እናቶችና ሽማግሌዎች ታፍሰው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። አንድ የአይን እማኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ልጆችን እንደ ሚዳቆ እያባረሩ እየያዙዋቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል

*********************************************************************************************


በአምቦ ለደረሰው የሰው እልቂትና የንብረት ውድመት መንግስት ራሱን ነጻ ለማድረግ ዘመቻ ጀመረ


May 7, 2014


ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባን አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም በአምቦና አካባቢው በሚገኙ ከተሞች ወደ አደባባይ የወጡትን ከ40 በላይ ንጹሃን ዜጎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ያስገደለው መንግስት ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን የጀመረውን ፕሮፓጋንዳ በስፍራው ላይ የነበሩ አንዳንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውመውታል።

አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ በኢቲቪ ቀርበው የተማሪዎችን ጥያቄ ኦነግ እና ግንቦት7 የተባሉት አሸባሪ ቡድኖች አይዟችሁ በማለት አቀጣጥለውታል ብለው ተናግረዋል።

የተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሃዊ ቢሆንም፣ ሌሎች ሃይሎች ግን መጠቀሚያ አድርገውታል በማለት አፈ ጉባኤው አክለዋል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንለት የ3ኛ አመት የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እንደተናገረው አባ ዱላ ገመዳ የተናገሩት ፍጹም ሀሰትና ጨርሶ ያልሆነ ነው ብሎአል።

“በመጀመሪያ ጥያቄውን ለማቅረብ ስንሰበሰብ መልስ እንደሚሰጡን ከነገሩን በሁዋላ ወዲያው በፌደራል እንድንከበብ አደረጉ፣ ትንሽ ቆይተው ፌደራሎች አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ጀመሩ። በአካባቢው ቆሞ ሲመለከት የነበረው ህዝብ ተማሪዎችን ለምን ትነኩዋቸዋላችሁ ብሎ ከፖሊሶች ጋር መጋጨቱን ተናግሯል።

ሌላ አንዲት ልጃቸው በገፍ የተገደለባቸው እናት በበኩላቸው፣ በብዛት ያለቁት ከ7 አመት እስከ 11 አመት የሆናቸው ምንም የማያውቁ ህጻናት መሆናቸውንና ህጻናቱ ጥይት ለመሸሽ በሚል ወደ ጫካ ሲገቡ ጨካ ውስጥ መገደላቸውን በመግለጽ እነ አባዱላ እርምጃ የተወሰደው ንብረት ስለወደመ ነው የሚለውን አስተያየት አልተቀበሉትም።

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና አለማቀፍ ተቋማት መንግስት በአምቦ እና በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች የፈጸመውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸው ይታወቃል።

ሂውማን ራይትስ ወች ግድያውን የፈጸሙትም ሆነ ትእዛዙን የሰጡት ባለስልጣናት ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ መግለጹ ይታወሳል።

 

 

Received on Wed May 07 2014 - 16:59:14 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved