Goolgule.com: ኢህአዴግ በኤርትራ አራት አቅጣጫዎች ጥቃት ሊሰነዝር አስቧል

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 8 Aug 2015 12:42:56 +0200
አሜሪካ ሃሳቡ ቀርቦላታል ተብሏል
four front map

ኢህአዴግ በአራት አቅጣጫዎች የጦር ጥቃት ለመሰንዘር ማሰቡ ተሰማ፡፡ ይኸው ሃሳብ ለአሜሪካ ቀርቦላታል፡፡

በቅርቡ የተጠናከረ እንቅስቃሴ የጀመረው የአርበኞች ግንቦት ፯ ኃይል በተደጋጋሚ በሚያወጣው መረጃ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ማድረሱን በይፋ ቢገልጽም ኢህአዴግ ጥቃቱን በቀጥታ ለማስተባበል እስካሁን አልወደደም። ይሁን እንጂ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ “ህዝብ አስፈቅደን” ሲሉ ኤርትራን እንደሚወጉ ይፋ አድርገዋል። አብዛኞች እንደሚስማሙበት ዛቻው ግጭት ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ ነው። በሌላው አንጻር ደግሞ ይህንን የሃይለማርያም ንግግር የኤርትራው ሹም በዓለምአቀፍ መድረክ ላይ የተለመደ የህወሃት/ኢህአዴግ ማስፈራሪያና ዛቻ በማለት አጣጥለውታል፡፡

የግጭቱን ደረጃና በኢህአዴግ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ኢሳት ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ኤርትራን መውቀሰና ማስፈራራት የጀመረው ኢህአዴግ፣ ቀጣናው ሊተራመስ እንደሚችል ስጋቱን ገልጾ ኤርትራን ለመደብደብ የሚያስችለውን ፈቃድ ስለማግኘቱ ጎልጉል መረጃ ደርሶታል። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) አራተኛዋ ሹም ዊንዲ ሼርማን ግንቦት ፯ን በስም በመጥቀስ በተቃወሙ ማግስት የባለሥልጣኗን የድጋፍ ቃል አስመልክቶ ቴድሮስ አድሃኖም በኢህአዴግ በኩል ያለውን ውለታ ሲናገሩ “ለምንከፍለው ዋጋ መጠን ተመጣጣኝ ክፍያ ነው” ሲሉ ውስጡ በርካታ የፖለቲካ “ጥሬ ሃብት” የሞላበት አስተያየት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሰጥተው ነበር።

የጎልጉል ታማኝ የመረጃ ምንጭ እንዳሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት የህወሃት ሰዎች ይህንኑ ጉዳይ በዋናነት አንስተው ነበር። ኢህአዴግ በሶማሊያ እያበረከተ ላለው ተግባር መሰናክል ተደርጎ የቀረበው የኤርትራ ተቃዋሚዎችን የመርዳት ጉዳይ እልባት እንዲበጅለት አሜሪካ ድጋፍ እንድትሰጥ የጠየቀው ኢህአዴግ፣ አሜሪካ ያሉ የከፍተኛ ተቃዋሚ አመራሮች ገደብ እንዲጣልባቸው ተማጽኗል። አሜሪካ ኢህአዴግ “አሸባሪ” ብሎ የሚፈርጃቸውን በሙሉ በሽብርተኛነት በመፈረጅ የመን የተጫወተችውን አይነት ሚና እንድትደግም ተጠይቃለች። ጥያቄው የቅዠትም ሆነ የምር፣ የግንቦት ፯ አመራሮች ነቅለው አስመራ መግባታቸው ጥያቄውን ዋጋ ቢስ አድርጎታል የሚሉ አሉ

አሜሪካ የቀረበላትን ጥያቄዎች ስለመቀበሏ ያልጠቀሱት የመረጃው ባለቤቶች፣ ኤርትራ ውስጥ መተራመስ ሳይፈጠርና ክልሉና ቀጣናው ሳይናጋ ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ቢወሰድ አሜሪካ ተቃውሞ እንደማይኖራት ማረጋገጫ መስጠቷን አመልክተዋል። ይህ አቋም ኦባማ አዲስ አበባ ከመሄዳቸው በፊት በተለያዩ ደረጃዎች ተመክሮበት ከስምምነት የተደረሰበት ስለመሆኑም ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር አቶ ስብሃት ነጋ “ከኤርትራ ጋር የሚካሄድ ውጊያ ጥንቃቄ ይጠይቃል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በዚሁ መነሻ ኢህአዴግ በጎንደር፣ በሱዳን ድንበር፣ በአፋርና በትግራይ የተለያዩ ግንባሮች ድንገተኛ ማጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ወቅቱ የዝናብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ለዚሁ ጥቃት ሠራዊቱ የሚወጋው “ተቃዋሚ የሆኑ የራሱን ወገኖች ሳይሆን ሻእቢያን ነው” በሚል የማነቃቂያ ስራ እየተሰራ እንደሆነ የመረጃው ሰዎች ተናግረዋል። በድጋሚ የመሥራቱ ጉዳይ ገና ባይታወቅም ይህ አካሄድ በባድመ እንደተደረገው የወኔ ማነቃቂያ እና የውጊያ ሞራል ማነሳሻ ለማድረግ ታስቦ በጥናት የተደረገ ለመሆኑ የመረጃው አቀባዮች ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም “ጦርነቱ ኢህአዴግ ካሰበው ውጪ ባንድ በኩል ከተሰበረ በጦሩ ውስጥ የሚገኙ የሌሎች ኅብረተሰብ ክፍል አባላት የሆኑ ወታደሮች ሊከዱና የተቃዋሚ ኃይሎችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ” የሚል ስጋት ስለመኖሩ ሪፖርት መቅረቡን ይጠቅሳሉ።

በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለው ሚዛን ያልጠበቀ የኃላፊነት ደረጃና የህወሃት አባላት ያላቸው የተጋነነ የበላይነት በመሃል አገር ከሚፈጸመው ረገጣ ጋር ተዳምሮ የተከማቸው ቅሬታ ሊፈነዳ ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳለም እነዚሁ ክፍሎች ያስረዳሉ።

ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል አውጀው ኤርትራ ከመሸጉና መሣሪያ አንግበው ትግል እያደረጉ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉ ግንባሮች ሁሉ በድርጅታዊ አቅሙ ከፍተኛ የሚባለውን (ደሚት/ትህዴን) የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን እስካሁን በሽብርተኛነት አለመፈረጁ ይታወቃል።

Received on Sat Aug 08 2015 - 06:42:57 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved