Goolgule.com: የድህረ-መለሱ ኢሕአዴግ አሰላለፍና የ“አዲሱ” ሥራ አስፈጻሚ የቢሆን ዕድል

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sun, 23 Aug 2015 16:18:10 +0200
tplf eprdf
 

የአራት ድርጅቶች ስብሰብ የሆነው ኢሕአዴግ፤ በሕወሓታዊ የድርጅት መንፈስ እየተመራ የስልጣን ቆይታ ዘመኑን ከአመታት ልኬት ወደ አስርታት ያሻገረ በመሆኑ፣ ከእንግዲህ የአገዛዝ ዘመኑን በክፍለ ዘመን ክፋይ አገላለጽ መጥራቱ ተራዛሚ የስልጣን ቆይታውን ይበልጥ የሚገልፀው ይሆናል፡፡ እናም ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል በስልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ በሰሜን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋረድ አገሪቱን “እየመራ” እዚህ ደርሷል፡፡ ግንባሩ ከፊት ለፊቱ አንደ “ትልቅ” ድርጅታዊ ጉባኤ ይጠብቀዋል፡፡

ነሐሴ 20/2007 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የድርጅቱ አስረኛ ጉባኤ መካሄድ ይጀምራል፡፡ የመቀሌው ጉባኤ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት፣ አራቱም ድርጅቶች በየክልል ርዕስ ከተማቸዉ የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ የድርጅታችዉን ሊቀ-መንበርና ም/ሊቀመንበር የሚመርጡ ይሆናል፡፡ ዛሬ ላይ እየታየ ካለው የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች እንቅስቃሴ አኳያ፣ አራቱም አባል ድርጅቶች የሊቀመንበር ለውጥ የሚያደርጉ አይመስልም፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ፣ ህወሓት አባይ ወልዱንና ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ ብአዴን ደመቀ መኮንንና ገዱ እንዳርጋቸውን፣ ኦህዴድ ሙክታር ከድርንና አስቴር ማሞን እንደ ቅደም ተከተላቸው በሊቀመንበርነትና ምክትል ሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ ይደረግ ይሆናል፡፡ ደኢህዴን በበኩሉ የድርጅቱ እና የኢሕአዴግ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑትን ኃይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበር ማስቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡

ይሁንና በሥራ አፈጻጸም ድክመት ከደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳደርነታቸው በመነሳት የትምህርት ሚኒስትር በመሆን እንደ ተሾሙ የሚነገርላቸዉ (ትምህርት ሚኒስቴር ግን የ“ዲሞሽን” ማራገፊያ ሆነ ማለት ነዉ!?) አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የወቅቱ የደኢህዴን ምክትል ሊቀ መንበር ቢሆኑም አሁን ካላቸው አፈጻጸም አኳያ የድርጅቱ ም/ሊቀመንበር እንደሆኑ እንዲቀጥሉ የሚደረግበት ሁኔታ የሚኖር አይመስልም፡፡ ሰውየው በምክትል ሊቀ መንበርነት የማይቀጥሉ ከሆነ ቦታው ላይ አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ መተካታቸው አይቀሬ ነው፡፡

የሆነዉ ሆኖ፤ በቀኝ ሲጠብቁት በግራ፣ መኃል ላይ ሲፈልጉት ከዳር የሚገኘው ኢሕአዴግ፤ በመቀሌው አጠቃላይ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ከሚወስናቸው ተጠባቂ ውሳኔዎች ውስጥ ድርጅቱን እስከ ቀጣዩ ጉባኤ ድረስ በሊቀ-መንበርነት እና ምክትል ሊቀመንበርነት የሚመሩትን አመራሮች መምረጥ እንዲሁም ለረጅም አመታት ያገለገሉ አንጋፋ አመራሮችን ማሰናበት ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉት ዉሳኔዎች ይገኙበታል፡፡ የዚህን ጉባኤ ውሳኔ ተከትሎ በአዲሱ ዓመት መግቢያ ወር ላይ “አዲስ” የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ እንደሚዋቀርም ይጠበቃል፡፡ የቀጣይ ጊዜያት የግንባሩ ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሊቀ-መንበር ማን ይሆናል? በ“አዲሱ” የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ እነ ማን ይቆያሉ? እነ ማንስ ይሰናበታሉ? የሚሉ ጉዳዮችን በቢሆን እድል ከማስቀመጣችን በፊት በድህረ-መለስ አጠቃላይ የስልጣን ገፅታ የአራቱ አባል ድርጅቶች አሰላለፍ ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ አንድ በአንድ ማየቱ የሚጠቅም ይሆናል፡-

አስኳሉ-ሕወሓት

የፖለቲካ መሪነትን በበረሃ ትግል ተፈትኖ ከማለፍ ጋር ብቻ በማያያዝ የሚተረጉሙ የፖለቲካ ትምክህተኞች ስብሰብ የሆነው ይሄው ድርጅት በግንባሩ ውስጥ ያለውን የበላይነት ለመግለፅ “የኢሕአዴግ አስኳል” የሚለው ሀረግ የድርጅቱን ጉልበታምነት ይበልጥ የሚገልፀው ይሆናል፡፡ የግንባሩን አባል ፓርቲዎች በራሱ የፖለቲካ አጀንዳ ልክ ቀርፆ በመስራትም ሆነ “አጋር ፓርቲዎች”ን ለ’ንጉስ አንጋሽ’ነት ፖለቲካ አመቻችቶ በመፍጠሩ ረገድ ረጅም ርቀት የተጓዘው ይሄው ድርጅት፤ ከድህረ መለስ በኋላ ያለው የስልጣን ከራሞቱ በመተካካት ችግር (succession crisis) የተጠቃ አስመስሎታል፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የሰውየውን ቦታ አሳልፎ ላለመስጠት በህወሃት በኩል ለህዝብ ይፋ ያልወጡ ድርጅታዊ መተጋገሎች ተከስተው እንደነበር እሙን ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ሆኖ የሚቀርበው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ የአቶ ኃይለማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ለማፅደቅ የወሰደው ጊዜ፣ በነዚህ ጊዜያት አቶ ኃይለማርያም ይጠሩባቸው የነበሩ የሹመት መጠሪያዎች (አንዴ ውጪ ጉዳይና ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላ ጊዜ ደግሞ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚል መሆኑ) እንዲሁም ከሰውየው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት በኋላ ለሠላሳ አንድ ቀናት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን ባለመልቀቅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከብስራተ ገብርኤል አራት ኪሎ ድረስ በተመላላሽ እንዲቆዩ የተደረገበት አጋጣሚ እና ህገ መንግስታዊ አግባብ በሌለው መልኩ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር (በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ … የምትለዋ ሀረግ የፖለቲካ ሀሁ ስለገባን ለጊዜው እናቆያት) የተሾመበት መንገድ ላስተዋለ ሰው ሕወሓት እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉንም ስልጣን መጠቅለል የሚችል ሁነኛ የፖለቲካ መሪ በማጣቱ የተነሳ አሳልፎ የሰጠው ወንበር ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

በርግጥ ህወሓት ሁነኛ የፖለቲካ መሪዎቹን ያጣው (ጥብቅ ብሔርተኝነታቸውን ተከትሎ ይታይባቸው የነበሩ አምባገነናዊ ባህሪያቶችን ሳንዘነጋ) የኢትዮ-ኤርትራ ግጭትን ተከትሎ በድርጅቱ ውስጥ በታየው መከፋፈል የተነሳ ነው፡፡ በወቅቱ “አንጃ” በሚል ፍረጃ መጀመሪያ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ቀጥሎም ከድርጅቱ አባልነት ከታገዱት ሲቪል ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ተወልደ ወ/ማርያም፣ ስየ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ዓለምሰገደ ገ/አምላክ፣ አውዓሎም ወልዱን የመሳሰሉ ጉምቱ የፖለቲካ አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ ከዚህ ጊዜ በኋላ እነዚህን የፖለቲካ መሪዎች የሚስተካከሉ የአደባባይ ፖለቲከኞችን ወደ ፊት ማውጣት ያልቻለው ድርጅት ከመለስ ሞት በኋላ የመተካካት ችግሩ ይፋ ሆኖ ወጥቷል፡፡ በ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል ወቅት አባይ ፀሐየ እና ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከ“አንጃ”ው ጋር ተፈርጀው የነበረ ቢሆንም በድርጅቱ “ተሐድሶ” ሂሳቸውን በመዋጥ ለመመለስ በቅተዋል (ምናልባትም ህወሓት እነዚህን ሁለት የጊዜያችን አራጊ ፈጣሪ የፖለቲካ መሪዎች በ“ተሐድሶ” መልክ ባይቀበላቸው ኑሮ ዛሬ ላይ ድርጅቱ በእነ ቴድሮስ አድሐኖም እንዴት ሊደገፍና የበላይነቱን ሊያስረግጥ እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል)

እጅግ አስገራሚዉ ነገር! አባይ ጸሀየ የዛሬ አርባ አመት (1968ዓ.ም) የህወሓት የህዝብ አደረጃጀት በመሆን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ ይሄዉ ከአርባ አመት በኋላም የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል ናቸዉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ገና ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የህወሓት ፖሊት ቢሮና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል በመሆን የጀርባ አሽከርካሪነታቸዉን አጠንክረዉ ይቀጥላሉ፡፡ የድህረ-መለሱ የስልጣን ሽግሽግ በህወሓት ዉስጥ የአባይ ጸሃየን ያህል የጠቀመዉ ሰዉ የለም፡፡ ድርጅቱም የመተካካት ድርቅ እንዳጋጠመዉ የሰዉየዉ ተራዛሚ የስልጣን ቆይታ ጮኾ ይመሰክራል፡፡ ድንቄም መተካካት!!

የሆነው ሆነ በፖለቲካ መሪ መኻንነት አብዝተን ልንተቸው የሚቻለን ህወሓት ከአረጋሽ አዳነ በኋላ አዜብ መስፍንን እንጂ የተሻለች ሴት ፖለቲከኛ ወደ አደባባይ ለማውጣት አልተቻለም፣ እንደ ገብሩ አስራት ያለ ሞግዚት ፖለቲከኛ በትግራይ ክልል አመራሮች ማየት የማይታሰብ ሆኗል፤ እንደ ዓለምሰገደ ገ/አምላክ ያለ የሚዲያ ጠርናፊ በህወሓት ቤት ደግሞ አልተከሰተም … ድርጅቱ እነዚህን የፖለቲካ መሪዎች በማጣቱ በብዙ መልኩ የፖለቲካ ባዶነት ታይቶበታል፡፡ ለዚህ እኮ ነው ድርጅቱ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በጤና አጠባበቅ ዙሪያ የሰሩትን ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖምን ከጤና ሚኒስትርነት በማንሳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማድረግ ለማስቀመጥ የተገደደው፤ ሰውየው ለቦታው ምን ያህል ይመጥናሉ? የትምህርት ዝግጅታቸውና ዝርዝር የሥራ ኃላፊነትና ተግባራቸው ይመሳሰላል? ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ወደ ጎን ተገፍተው፣ ስለ ስልጣን ሽሚያ ሲባል የድርጅቱ ሰው ስለሆኑ ብቻ እንዲቀመጡ የተደረገበት መንገድ ሕወሓት በምን ያህል መጠን የአመራር ድርቅ እንዳጋጠመው ያሳያል፡፡

ያም ሆኖ ግን፣ ሕወሓት የፖለቲካ አመራር ድርቀቱን የሚሻገርባቸው ሁለት ዋና ዋና ምርኩዞች አሉት፡፡ አንደኛው የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰራዊቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋማት ለጊዜውም ቢሆን የድርጅቱ ፖለቲካዊ ጉልበት እንዳይነጠቅ የላቀ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ የድርጅቱ የአስኳልነት ምንጭም ይሄው ነው፡፡

ሁሌም ለደረጃ ሁለት – ብአዴን

በ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል ወቅት የብርቱ ደጀንነት ሚና የተጫወቱት የብአዴን አመራሮች ከህወሓት/ኢሕአዴግ የድርጅት “ተሐድሶ” በኋላም ቢሆን የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀንደኛ ደጋፊ በመሆን በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ የሁለተኛ ደረጃ የመሪነት ተሳትፏቸው እንዳይነጠቅ የፖለቲካ ታማኝነታቸውን ገቢር ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡ የብአዴን አመራሮች ጮክ ብለው ስለከፈሉት መስዋዕትነት የሚያወሩትን ያህል ባይሆንም እንኳ ከወታደራዊ አበርክቶ ይልቅ የፖለቲካ አበርክቷቸው የላቀ እንደነበር ይታመናል፡፡ ይህ ሲባል ግን ደርግን በመፋለም ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ የኢህዴን/ብአዴግ ታጋዮችን ዋጋ ለማቅለል እንዳልሆነ ልብ ይባል፡፡ ሁሌም ቢሆን ኢህአዴግ ከወቅታዊ የፖለቲካ መሪነት ብቃት ይልቅ የበረሃ ላይ መስዋዕትነትን ታሳቢ ያደረገ የስልጣን ድልደል ያለው በመሆኑ እንጂ፡፡

በድህረ-መለስ የስልጣን እርካብ ላይ የብአዴን አመራሮች በተለይም በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት ሰሞን ብዙዎቹ የህወሓት አመራሮች ድምፃቸው በጠፋበት ሁኔታ የበረከት ስምኦንና የአዲሱ ለገሰ ለሚዲያ ቅርብ መሆን፣ ካሳ ተክለብርሃን ከቀብር አስፈፃሚነት እስከ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጪነት የደረሰ ድርብ ሚና ይዘው ብቅ ያሉበትን ሁኔታ ስናስታውስ፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው የደረጃ ሁለት የመሪነት ሚናቸውን ለማሳደግ ሙከራ ውስጥ ገብተው እንደነበር አስረጂ ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ አልሆነም እንጂ፡፡

ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በተደረገው የአመራር ሽግሽግ የብአዴን አመራሮች የተመኙነትን የደረጃ አንድ መሪነት ሚና ባያሳኩም፤ በመተካካት ሰበብ አጥተውት የነበረውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ እንዲሁም በአቶ መለስ የስልጣን ቆይታ ጊዜ “የቦዘኔ ቦታ” በአቶ ኃይለማርያም ጊዜ ደግሞ በግልባጩ “የስልጣን የሻሞ ውጤት” ተደርጎ በሚወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊስና ጥናትና ምርምር አማካሪነት ቦታ ላይ ከባድ ሚዛን ተጫዎቹን አቶ በረከት ሰምኦንን ማስቀመጥ መቻላቸው፣ አቶ አዲሱ ለገሰ በጡረታ ከተሸኙበት ድርጅታቸው ዳግም በስራ አስፈፃሚነት ሚና እንዲከሰቱ የተደረገበትን አጋጣሚ ስናስተውል … ደረጃ ሁለት የሆኑት የድርጅቱ አመራሮች የሰርክ ቦታቸውን በማስጠበቅ ለቀጣዩ ቦታ የስልጣን ሽሚያ ውስጥ ለመግባት ያቆበቆቡ ይመስላል፡፡ በአንፃራዊ እይታ ብዛት ያላቸው የተማሩ መካከለኛ አመራሮች እንዳሉት የሚነገርለት ይሄው ድርጅት በየትኛውም መጠን ተተኪ አመራሮችን አዘጋጀ ቢባል እንኳ ወደ ደረጃ እንድ የፖለቲካ መሪነት የማደግ እድሉ ጠባብ መሆኑን በአዲስ መስመር እንመልከት፡-

ብአዴን “እየመራሁት ነው” በሚለው ክልል ውስጥ እንደ ድርጅት የህዝባዊ ቅቡልነት ችግር እንዳለበት ከአንባቢ የተሰወረ አይደለም፡፡ ከዚህም ባለፈ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ሲፋቁ አርበኞች ግንቦት ሰባት ናቸው” የሚል የአደባባይ ሐሜት ተንሰራፍቷል፡፡ ለዚህ ጉዳይ አስረጂ ምሳሌ ሆኖ የሚቀርበው በ2006 ዓ.ም በጥር ወር ላይ የብአዴን ዋና ፀሐፊና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሆነው አቶ አለምነው መኮንን በባህር ዳር ከተማ የድርጅቱን መካከለኛ አመራሮች ሰብስቦ “አማራ”ን በተመለከተ ያደረገው የጥላቻ ንግግር (hate speech) ተቀርጾ ለኢሳት መድረሱና የአንድ ሰሞን የማህበራዊ ድረ ገፆች መነጋገሪያ የመሆኑ ጉዳይ አንደኛው አስረጂ ምሳሌ ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በ2007 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በበረከት ስሞንና አዲሱ ለገሰ ሰብሳቢነት ያደረጉት ዝግ ስብሰባ ላይ የተቀነጨበ የድምፅ ሪከርድ ለኢሳት ጋዜጠኞች የደረሰበትን አጋጣሚ ስናስታዉስ፣ የድርጅቱን መካከለኛ አመራሮች በውስጥ አርበኝነት ለመበየን ድፍረት ይሰጠናል፡፡

ዛሬ ላይ ከህወሓት/ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ብአዴንን በድፍረት “የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ሲፋቁ አርበኞች ግንቦት ሰባት ናቸው” ለማለት የሚደፍር የፖለቲካ መሪ ባይኖርም፣ ከቃላት በላይ አንዳንድ ድርጊቶች ጮኸው እየተናገሩ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ እናም የዚህ ድርጅት መካከለኛ አመራሮች የጀርባ መደብ ፈርጅ በፈርጅ ባልተጠናበት ሁኔታ ስለ ድርጅታዊ ኮታ ሲባል ወደ ከፍተኛ አመራርነት በተለይም ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ ይሳባሉ ብሎ መጠበቅ አንድም የዋህነት ሁለትም የሕወሓትን ጫፍ የረገጠ ጥርጣሬ ካለመረዳት የሚመነጭ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ “እኛ ከፊት መስመር ገለል ብለን ከኋላ መደገፍ ይኖርብናል” በሚለው የበረከት ስምኦን አገላለፅ መሰረት፣ ደረጃ ሁለትነቱን አምኖ የሚቀበል ተተኪ አመራር እየተመለመለ በኋላ ደጀኖች እየተደገፈ ድርጅቱ የሚቀጥል ይመስላል፡፡

በጥንቸሎች የታሰረው ዝሆን – ኦሕዴድ

ኦሕዴድ፣ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በቀዳሚነት የተረጋጋ አመራር የሌለው ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ሁለት የድርጅት ሊቀመንበሮች ያየ ሲሆን፣ በአንፃሩ ኦሕዴድ ኩማ ደመቅሳ፣ አባዱላ ገመዳ፣ አለማየሁ አቶምሳ (ነፍስ ይማር!) እና ሙክታርና ከድር ተፈራርቀውበታል፡፡ ሃያ ሰባት ሚሊዮን የሚሻገር ህዝብ “የሚመራው” ኦሕዴድ ያልተረጋጋ አመራር እና እርስ በርስ ባለመተማመን የተከፋፈሉ የፖለቲካ መሪዎች ያሉበት ድርጅት ለመሆኑ ከኩማ ደመቅሳ እስከ ሙክታር ከድር ድረስ ያለው የድርጅቱ ታሪክ የአደባባይ ምስክር ነው፡፡ ከግንባሩ አባል ድርጅቶች በተለየ መልኩ የአቶ መለስ ጣልቃ ገብነት ረዝሞ ይታይ የነበረው በዚሁ ድርጅት ላይ ነበር፡፡

የኩማ ደመቅሳ የቀደመ የፖለቲካ ፊትነት ከ1993ቱ የህወሃት ክፍፍል በኋላ መገታት፣ የአባዱላ ገመዳ የኔትወርክ ፖለቲካ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ያለፉ መካከለኛ አመራሮችን የማፍራት ሂደት ሰውየውን ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ መቀመጫ በመሳብ ሂደቱ መጨናገፉ፣ የአቦ አለማየሁ አቶምሳ ፀረ-ሙስና ትግል መስመር ሳይዝ አወዛጋቢ በሆነ መልኩ በምግብ መመረዝ ምክንያት ለሞት መዳረግ፣ አቶ ሙክታር ከድር የህዝብ ተወካዮች የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባል ባልሆኑበት ሁኔታ የክልሉ ፕሬዚዳንት በመሆን መሾማቸውና ሌሎች መሰል ክስተቶችን ከህግ አግባብ አኳያ ላስተዋለ ሰው፣ ድርጅቱ በአባላት ብዛት የገዘፈ ቢሆንም አነስተኛ የህዝብ ውክልና ይዘው ማዕከላዊ መንግስቱን በተቆጣጠሩት የህወሓት ባለስልጣናት ዕዝ ሥር የወደቀ ፓርቲ ለመሆኑ መረዳት አያዳግትም፡፡

ማዕከላዊ ኃይል አልባነትና የኢኮኖሚ በዝባዥነት መገለጫቸዉ የሆነው የኦህዴድ አመራሮች በድህረ-መለስ የስልጣን እርካብ፣ ድርጅታዊ ኮታን ከማስጠበቅ አኳያ የሙክታር ከድር ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ከመሳብ፣ ቆይቶም በአስቴር ማሞ ከመተካቱ ውጭ፣ የድርጅቱን አመራሮች ይህ ነው በሚባል የስልጣን ከፍታ ላይ ለማየት አልቻልንም፡፡ የአምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በመቀበልና በመሸኘት የተገደበው የማዕከላዊ መንግስቱ የፕሬዝዳንትነት ቦታ እንደሆነ ከድሮውም ቢሆን የኦህዴድ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ጥናትና ምርምር አማካሪ በሚል ተሹመው የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር በሚል ከተሾሙ በኋላ በምትኩ የኦህዴድ አባል የሆነ አመራር አለመተካቱ፣ ፓርቲው በግንባሩ ውስጥ በምን ያህል መጠን እየተገፋ እንዳለ ያሳያል፡፡

በኦህዴድ የፖለቲካ መስመር ላይ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ በመሮጣቸው የተነሳ “መተካት” በሚለው ድርጅታዊ ፈሊጥ ከኦህዴድ ስራ አስፈጻሚነት የተነሱት አቶ አባዱላ ገመዳ በድህረ-መለስ የፖለቲካ ሜዳ ላይ በአንፃሩ ጎላ ብለው የታዩ ብቸኛው የድርጅቱ ሰው ናቸዉ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ ከአምቦና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት የፊት መስመር ተሰላፊ መሆናቸው፣ በወቅቱ ለአንድ የውጭ አገር ሚዲያ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ በሟች ወጣቶች ላይ የስርዓቱ ወታደሮች የወሰዱት እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን በድፍረት የገለፁበት ሁኔታ፣ “የአዉራ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያት” በሚል ርዕስ ዙሪያ የኢሕአዴግን አዲስ የስልጣን አቋም የሚያስተነትን የጥናት ወረቀት የምክር ቤቱ ቋሚ የኮሚቴ አባላት፣ ከሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤት የተወከሉ አመራሮች እና የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በተገኙበት ማቅረባቸው፣ በ2007 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባህር ዳር ላይ በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ስለ ጦር ሰራዊቱ አጠቃላይ ሁኔታ የሚያተኩር የጥናት ወረቀት ማቅረባቸው፣ በአባይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራውን አዲሱን “የፐብሊክ ዲፕሎማሲ” ቡድን በመምራት ወደ ተለያዩ አገራት ማቅናታቸው፣ የ2007ቱን ሀገር አቀፍ ምርጫን አስመልክቶ በነበረው ቅድመ ዝግጅት ቴክኒካዊና ስትራቴጂያዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደ ሀሳብ አመንጪነት ማገልገላቸው፣ በኦህዴድ ምስረታ የብር እዮቤልዬ በዓል አከባበር ላይ የኦህዴዱ መለስ በሚመስል ድርጊት መወከላቸውን እና ሌሎች የአደባባይ እንቅስቃሴያቸውን ስናስተውል፣ ያረጀ እባብ ቆዳውን ገፎ እንደሚወጣው ሁሉ ሰውየም የመለስ አለመኖር የፈጠረላቸውን ምቹ እድል ተጠቅመው እያንሰራሩ እንዳለ ለመገመት አይከብድም፡፡

በድህረ-መለስ የስልጣን እርካብ ላይ ኦህዴድ እንደ ድርጅት ካሳየው እንቅስቃሴ በላይ የአባዱላ ገመዳ ፖለቲካዊ ጥን-ጥን የተሻለ ለመሆኑ የሰውየውን የሦስት አመት ቆይታ ማስተዋል በቂ ነው፡፡ የነገሩ ምፀታዊነትም ይኼው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሰፊውን የቆዳ ስፋትና ቀዳሚውን የህዝብ ቁጥር የያዘውን የኦሮሚያ ክልልን “የሚመራው” ኦህዴድ፣ ኢሕአዴግ አሉኝ ከሚላቸው ስድስት ሚሊዮን አባት ውስጥ ሁለት ሚሊዮኑን ቢረክዝም፣ የ“አጋር ድርጅቶች”ን ወንበር ሳይጨምር ኢሕአዴግ በፓርላማው ካለው 501 የምክር ቤት መቀመጫ ውስጥ 178 ወንበሮችን ቢያዋጣም (የትግራይ ክልል በፓርላማው ያለው የመቀመጫ ብዛት ሠላሳ ስምንት ከመሆኑ አንፃር፣ ኦህዴድ ከህወሓት አራት እጥፍ ዋጋ ያለው የወንበር መጠን እንዳለው ልብ ይሏል) የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እስረኛው ኦህዴድ፣ በጥንቸሎች እንደታሰረ ዝሆን ግዝፈቱ እንጂ እንቅስቃሴው ሊታይ አልቻለም፡፡

ሚዛን አስጠባቂው – የደኢሕዴን

የድል አጥቢያ መሪዎች ስብስብ የሆነው የደኢህዴን፣ በመለስ/ኢህሐዴግ ዘመን እንደ “አቻ”ዎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች (በዋናነት ህወሓት-ብአዴን) ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ መሪነት ሚናውን የሚያሳይባቸው የስልጣን ቦታዎች አምብዛም አልነበሩትም፡፡ የግንባሩ የመተካካት ፖሊሲ ይፋ ከሆነበት የሐዋሳው ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ፣ የ2002ቱን “ምርጫ” ተከትሎ የመጀመሪያው ዙር መተካካት ገቢር በሆነበት ጊዜ፣ ከዚህ ቀደም በማዕከላዊ መንግስቱ የፖለቲካ አደባባይ ላይ በአንፃሩ ይታወቁ ከነበሩት ከእነ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ የወቅቱ አፈ-ጉባኤ ተሾመ ቶጋና መሰል አመራሮች በተሻለ ቦታ በዋናነት ኃይለማርያም ደሳለኝ ውጭ ጉዳይና ም/ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ሽፈራው ተክለማርያም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ሲራጅ ፈጌሳ የመከላከያ፣ መኩሪያ ኃይሌ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ደሴ ዳልኬ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ሲሆኑ፤ ጥቂት የማይባሉ የድርጅቱ አመራሮች በልዩ ልዩ ሚኒስተር መስሪ ያቤቶች በሚኒስተር ዲኤታነትና በዋና ዳይሬክተርነት በቀድሞዎቹ የሕወሓት-ብአዴን አመራሮች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ተክተው በመስራት የአደባባይ ፖለቲከኛነታቸው በስፋት መታየት ጀመረ፡፡

በመጀመሪያው ዙር የመተካካት ሂደት ውስጥ እንደ “ኃይል” (ያው ዋናው ኃይል ያለው ደህንነት መሰሪያ ቤቱና መከላከያ ውስጥ ስለሆነ በሚል ነው ቃሉ ትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ የገባው) ሚዛን ማስጠበቂያነት የደኢህዴን አመራሮች አገልግለዋል ማለት ይቻላል፡፡ የደኢህዴንን ሚዛን አስጠባቂነት በተሻለ የሚገልፀው አጋጣሚ ደግሞ የአቶ መለስን የደህንነት ህልፈት ተከትሎ በግንባሩ አባል ድርጅቶች በተለይም በህወሓትና ብአዴን ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስተርነት ቦታውን ለመውሰድ የነበረውን የድርጅት ውስጥ መተጋገል ለማስታረቅ የተሄደበት መንገድ የድርጅቱን ሚዛን አስጠባቂነት ይበልጥ ያስረግጠዋል (ርግጥ ህወሓት በወቅቱ ሁነኛ ጠቅላይ ፖለቲከኛ ቢኖረው የብአዴን አቅም ያን ያህል ባላስቸገረው ነበር፡፡ ዳሩ፣ አቶ መለስ ከ1993ቱ የህወሓት ክፍፍል በኋላ ህወሓትን ለመቀሌ አመራሮች ትተው የብቻ ጠቅላይነታቸውን “ግፋ ብለው” ያሉ በመሆኑ በማዕካለዊ መንግስቱ ላይ የተሻለ አቅም ያለው የህወሓት ሰው አልነበረም፡፡ በጊዜዉ ከስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊነት ተስበው የመጡት አባይ ፀሐየም ቢሆን የዛሬን አያድርገውና ከህወሓት አመራሮች ጋር በድህረ 93ቱ የህወሓት ክፍፍል የዋጡት ሂስ እንደፈለጉት ለመናገር “ስትራፖ” ሆኗቸው ስለ ነበር እድሉ አምልጧቸዋል)

የሆነው ሆኖ ዘመን የፈቀደለት ሚዛን አስጠባቂው ደኢህዴን የመለስን ሞት ተከትሎ ከምስረታ ጊዜው 1984 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በሃያ አመታት ቆይታው በእውኑም ይሁኑ በድርጅታዊ ህልሙ አልሟቸው ይሁን አስቧቸው የማያውቃቸው የስልጣን ቦታዎች ለአመራሮቹ ክፍት ሆኑለት፡፡ በዋናነት የአቶ መለስ ህልፈት ኃይለማርያምን ወደ አይነኬ-አይጠጌው ወንበር ሲያመጣ፣ ለሬድዋን ሁሴን ደግሞ ያልታሰበ ሲሳይ ጥሎ አልፏል፡፡ ዶ/ር ካሱ ኢላላም ቢሆኑ በአስራ አንደኛው ሠዓት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊስና ጥናትና ምርምር አማካሪ በመሆን ተሹመዋል፡፡ (መቼም በ“ዲሞሽን” ከደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳደርነት ወደ ትምህርት ሚኒስተርነት የመጡትን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን እንደ ሹመት መቁጠር የሚጠበቅብን አይመስለኝም)

ምንም እንኳ የደኢህዴን አመራሮች ሹመት ጉዳይ ከሚዛን አስጠባቂነት ጋር የተያያዘ ቢሆንም የድህረ መለስ የስልጣን እርካብ ላይ ላዩን ላየው በአመዛኙ ለደኢህዴን የተመቸ ይመስላል፡፡ በተለይም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስተር ቦታ ከያዙ በኋላ እንደ ቀላል የማይታዩ የስልጣን ቦታዎች ላይ የደኢህዴን ጓዶቻቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ለአብነት፡- በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ቦታ ላይ አሰፋ አብዮን፣ ደበበ አበራን የኢሕአዴግ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ውዱ ሀቶን የፀረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር፣ አማኑኤል አብርሃምን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ፣ ሰለሞን ተስፋየን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ አማካሪ፣ ካይዛ ኬ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር (የገብረዋህድ ቦታ መሆኑን ያስታውሷል)

ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው ሹመቶች ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በማዕከላዊ መንግስቱ ለደኢህዴን አመራሮች የተሰጡ መሆናቸውን ስናስተዉል፣ የደህንነት መስሪያ ቤትና መከላከያ ሰራዊት የተባሉ ቁልፍ የኃይል ማዕከሎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ደኢህዴን የደቡቡ ህወሓት፣ ኃይለማርያም ደግሞ የደቡቡ መለስ ለመሆን ባስቻላቸው ነበር:: ነገሩ ያለው ወዲህ ነውና ይሄ ሁሉ የደኢህዴን አመራሮች ያልተጠበቀ ሹመት ከሚዛን አስጠባቂነት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ቢሆንም ግን! የአቶ መለስ ሞት ለደኢህዴን አመራሮች የትንሳኤ ያህል ለማገልገሉ ከሰውየው ህልፈት በኋላ ወደ ፊት መስመር የቀረቡትን የደኢህዴን አመራሮችን ብዛት ማስተዋል በቂ ይመስላል፡፡

ከመቀሌው ጉባኤ ምን ይጠበቃል?

አብዮታዊ ግንባር፣ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ አጠቃላይ ድርጅታዊ ጉባኤውን በመቀሌ ከተማ ያካሂዳል፡፡ በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከተዉ ግንባሩ በዚህ ድርጅዊ ጉባኤ ላይ ውሳኔ ያሳልፍባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ ወሳኝ አጀንዳዎች መካከል፣ ድርጅቱን ለቀጣይ አምስት አመታት በሊቀ መንበርነትና ምክትል ሊቀ መንበርነት የሚመሩትን መሪዎች መምረጥ የሚለው አንዱ ነው፡፡

በድህረ መለሱ የስልጣን እርካብ የግንባሩን አባል ድርጅቶች አሰላለፍ ለማየት እንደተሞከረው፣ በእስካሁኑ ሂደት እንደ ኦህዴድ የከሰረ፣ እንደ ደኢህዴድ የተሻለ እድል ያጋጠመው ድርጅት የለም፡፡ ብአዴንም በአቅሙ በድህረ መለስ የስልጣን ሽሚያ የጠበቀውን ያህል ማትረፍ ባይችልም ዋናውን አስጠብቆ የዘለቀ ይመስላል፡፡ ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ቢያጣውም፣ “በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ” ይሉት ሹመትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሚል ሰበብ የሀገሪቱን ቁልፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ሜጋ ፕርጀክቶችን መቆጣጠር ችሏል፡፡ በአናቱም የሀገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ኃይል ማዕከል የሆኑት የደህንነትና የመከላከያ ሰራዊት ቁልፍ አዛዦች፣ ዋነኛ የኦፕሬሽንና የመስመር ኃይል አመራሮች … በግልፅም ሆነ በህቡዕ ለህወሓት አመራሮች ያደሩ በመሆኑ፣ እነዚህ ተቋማት በህወሓት ሰዎች እስከተያዙ ድረስ ማዕከላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር ከበቂ በላይ ነው፡፡ በመሆኑም በአባይ ወልዱና ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት (በሌላ አጠራር የጠቅላይ ሚኒስትርነት) ቦታውን “ስሙ ነው የባሰን፣ ታንክና ባንኩን ከያዝን ይበቃናል” በሚል የሚዛን አስጠባቂው ደኢህዴንና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር የሆኑት ኃይለማርያም ደሳለኝ ባሉበት እንዲቀጥሉ ሊያደርግ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ርግጥ ይህን ውሳኔ የሚቃወሙ የህወሓት ሰዎች አይጠፉም፡፡ ይሁንና በህወሓት በኩል ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልም ሆኑ ቴድሮስ አድሃኖም በሚዲያ ቀርበው ሃሳባቸውን አፍታቶ የመናገር አቅማቸው እንኳንስ ከአቶ መለስ አንፃር ቀርቶ ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ሊወዳደሩ የሚችሉ ባለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስተርነቱ ቦታ በህወሓት ሰዎች ብዙም የሚደፈር አይመስልም፡፡ አርከበ እቁባይም ቢሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት መቀመጫ በሌላቸው ሁኔታ ለዚህ መሰል ሹመት የሚበቁበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ ሰውየውን መርሳት ይቀላል፡፡

በተለምዷዊ የድርጅቱ አሰራር የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆኖ በጉባኤው የሚመረጠው አካል፣ የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የሚሾም ይሆናል (በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ … የሚለውን ሹመት ሳያካትት) ይህን ቦታ ለማግኘት ብአዴንና ኦህዴድ የበለጠ ፉክክር የሚያደርጉ ይመስላል፡፡ አንደኛው ዋናውን ለማስጠበቅ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አዲስ የድርጅት ሪከርድ ለማስመዝገብ፡፡ በዚህ ድርጅታዊ መተጋገል ውስጥ የህወሓትን ባርኮት የሚያገኘው ድርጅት የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀ መንበርነቱን ቦታ የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ከድህረ መለስ ወዲህ ከኦህዴድ የተሻለ የፖለቲካ ተሳትፎ እያሳየ ያለው ብአዴን እንደመሆኑ መጠን እድሉን አሳልፎ የሚሰጥ አይመስልም፡፡ በአናቱም የወቅቱ የኦህዴድ ሊቀ-መንበር ሙክታር ከድር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆኖ በመሾሙ ወደ ማዕከላዊ መንግሥቱ የመመለስ እድል የሚኖረዉ አይመስልም፡፡ የሆነዉ ሆኖ፣ ከሁለት አንዱ ድርጅት የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነቱን (ም/ጠ/ሚኒስትርነቱ) ቢያጡት እንኳ፣ በም/ጠ/ሚንስትር ማዕረግ … የሚለው የድህረ መለሱ ሹመት (የመስተዛዘኛው ዕጣ) እንደተጠበቀ ይሆናል፡፡

በጉባኤው ማነው ተሰናባች? ማነዉስ ቀጣይ?

ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ የተረሳ የሚመስለው ሁለተኛው ዙር የመተካካት ሂደት በኃይለማርያም ደሳለኝ አስፈፃሚነት እንዲቀጥል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች እንዳሳሰቡ መረጃዎች እየወጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ 2002ቱ ባይሆንም እንኳ የተወሰኑ የግንባሩ አባል ድርጅት ነባር አመራሮች የሚሰናበቱ ይሆናል፡፡ ከዚህ የቢሆን እድል በመነሳት ከአራቱም አባል ድርጅቶች እነ ማን ይሰናበታሉ? እነማንስ ከ“አዲስ” አመራሮች ጋር ይቀጥላሉ የሚለው ቅድመ-ግምት የሚከተለውን ይመስላል፡- (“ይሰናበቱ ይሆናል” በሚል የቢሆን እድል የተጠቀሱ አመራሮች የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የነበሩትን ብቻ ሳይሆን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሁነዉ ወሳኝ ድርጅታዊ ስራዎችን ሲሰሩ የነበሩ ነባር አመራሮችንም የሚጨምር ይሆናል፡፡ ከግንባሩ የፖለቲካ ባህሪ አኳያ፤ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የድርጅቱ ቀኖና በመሆኑ በዚህ የቢሆን እድል ስር የተካተቱ አመራሮች በቀጣይ ድርጅታቸዉን ወክለዉ የእናት ድርጅታቸዉ ኢህአዴግ ሥራአስፈጻሚ የሚሁኑትን ሰላሳ ስድስት አመራሮችን የሚመለከት መሆኑን ልብ ይሏል)

ሕወሓት፡- እንደ አዜብ መስፍን፣ ቅዱሳን ነጋ፣ ሮማን ገ/ስላሴ፣ ኪሮስ ቢተው … ያሉ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት (ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ውጪ ያሉት በእድሜ መግፋት) ለተተኪ አመራሮች ቦታ ይለቁ ይሆናል፡፡ በአንፃሩ አባይ ወልዱ፣ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ፀሐየ፣ ፀጋየ በርሃ፣ ቴድሮስ አድሃኖም፣ አስመላሽ ወልደ ስላሴ ነባር ስልጣናቸውን በማጠናከር/በማሻሻል፤ አዲስ ይገባሉ ብየ የምገምታቸውን አዲስ አለም ባሌማ፣ አብርሃም ተከስተ እና አርከበ እቁባይን እንደ “አዲስ” አመራር በመተካት የህወሓት ፖሊት ቢሮ እና የኢህአዴግ ሥራአስፈጻሚን ይቀላቀላሉ የሚለው ግምት ሰፊ ነው፡፡ የአርከበ እቁባይን የአደባባይ ፖለቲካ ፊት ፊት ማለት ስናስተዉል ሰዉየዉ በአዲስ መልኩ የኢህአዴግን ስራ አስፈጻሚ መቀላቀላችዉ እንደማይቀር ለማመን እንገደዳለን፡፡

ብአዴን፡- በሰሜን-ምዕራብ ኢትዮጵያ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እንቅስቃሴ ከመጠናከሩና ከዚሁ ድርጅት ንክኪ ያላቸው የውስጥ አርበኞች ከመከሰታቸው ጋር በተያያዘ ብአዴንን ወክለው ወደ ሥራ አስፈጻሚነት የሚመጡ አመራሮች በጥንቃቄ እንደሚመረጡ አስቀድሞ መገመት ይቻላል፡፡ እንደ በረከት ስሞን (ከጤና ጋር በተያያዘ)፣ አዲሱ ለገሰ፣ ኤሌው ጎበዜ (ቀድሞ የተሰናበቱ ቢሆንም በይፋ ስንብት)፣ ዘነቡ ታደሰ፣ ዮሴፍ ረታ፣ ታደሰ ካሳ … ያሉ የድርጅቱ ነባር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ለተተኪ አመራሮች ቦታ ይለቁ ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አለምነው መኮንን፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ ተፈራ ደርበው፣ ብናልፈው አንዷለም ነባር ስልጠናቸውን በማጠናከር/በማሻሻል፤ አዲስ ይገባሉ ብዬ የምገምታቸውን ደስታ ተስፋው፣ አባተ ስጦታው እና የሴት አመራሮችን ተሳትፎ ማጠናከር በሚል ፍሬህይወት አያሌውን እንደ “አዲስ” አመራር በመተካት የብአዴን ፖሊት ቢሮ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚን ይቀላቀላሉ የሚለው ግምት ሰፊ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ከባድ ሚዛን ተጫዋቹ አቶ በረከት ስሞን ከወቅታዊ የጤና ሁኔታ አኳያ ከኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚነታቸው ገለል ቢሉም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሙዳየ ቃላት (Vocabulary) በመሆናቸው ከመጋረጃው ጀርባ ርቀው አይርቁም፡፡ የአቶ አዲሱ ለገሰ ጉዳም ቢሆን የኢህአዴግን የካድሬ ት/ቤት በማጠናከር ረገድ የቀደመ ተሞክሮ ያላቸው በመሆኑ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ከአቶ በረከት የተለየ የማይሆንበት እድል ይኖራል፡፡

ኦሕዴድ፡- “በትልቁ ህዝብ ውስጥ ያለው ትንሹ ድርጅት” በተረጋጋ አመራርና ከጎጠኝነት በተሻገረ (ከአርሲ Vs ወለጋ ኦሮሞ አተካራ በፀዳ) መልኩ ድርጅቱ እንዲታደስ፣ ከፍ ሲል የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኝነት ዝቅ ሲል ደግሞ የሕወሓት ራሮት ያስፈልጋል (መቼም የኦህዴድ አመራሮች ሙሉ ቁርጠኝነት ባሳዩበት ሁኔታ የህወሓት አመራሮች ድርጅቱን ለመጠምዘዝ የሚያስችል ድፍረት የሚያገኙ አይመስለኝም፤ ከሆነም የግንባሩም ሆነ የአገሪቷ ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት አጋጣሚ ይፈጠራል) የሆነው ሆኖ ኦህዴድ አሁን ካለበት የፍዘት ጎዳና እንዲወጣ የሚያስችሉ ጠንካራ ስራ አስፈፃሚዎች እንደሚያስፈልጉት ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ እንደ ኩማ ደመቅሳ (ቀድሞ የተሰናበቱ በመሆኑ)፣ ሶፊያን አህመድ (በጤና ሁኔታ)፣ አሊ ሲራጅ (በቅርቡ በሞት የተለዩ) እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ አለቅጥ ተለጥጦ ካለው ሰማንያ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ የመስራት አቅም ያላቸውን በማስቀረት ቀሪዎቹን በአዲስ የመተካት ስራ ከተሰራ የድርጅቱ እድል አሁንም የከሰመ አይደለም፡፡ በዚህ አግባብ ሙክታር ከድር፣ ሀብታሙ ኃ/ሚካኤል፣ አስቴር ማሞ፣ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ድሪባ ኩማ፣ አብዱልአዚዝ መሀመድ ነባር ስልጣናቸውን በማጠናከር/በማሻሻል፤ አዲስ ይገባሉ ብየ የምገምታቸውን አብይ አህመድ፣ ደሚቱ ሃምቢሳ እና አባዱላ ገመዳን (ብአዴን ውስጥ አዲሱ ለገሰ ከይፋዊ ስንብት በኋላ የድርጅቱን ክፍተት ለመጠገን እንደተመለሰ ያስታውሷል፤ በተመሳሳይ መልኩ ለአባዱላም ይሄው እድል ይሰጥ ይሆናል ከሚል ምልከታ በመነሳት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰውየው እድሉ የሚሰጣቸው ከሆነ የአቶ ኩማ ደመቅሳን ቦታ በመተካት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ጥናትና ምርምር አማካሪ በመሆን ይሰሩ ይሆናል) እንደ “አዲስ” አመራር በመተካት የኦህዴድን ፖሊት ቢሮ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚን ይቀላቀሉ ይሆናል፡፡ መስከረም ላይ በሚሰየመው “አዲስ” የመንግስት ካቢኔ ውስጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኦሮሞ ተዋጽዖ የሳሳ እንዲሆን የሚደረግ ከሆነ ግን ጊዜ ጠብቆ በሚፈነዳዉ ሦስተኛዉ የኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ የኦህዴድ መካከለኛ አመራሮችን ከፊት መስመር ፈልጎ ማግኘት አይከብድም፡፡

ደኢህዴን፡- በድህረ-መለሱ የስልጣን ሽግሽግ የበዛ ሲሳይ የዘነበለት ለዚህ ድርጅት እንደሆነ ከላይ ለማሳያነት የጠቀስናቸው ሹመኞች አስረጂ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡ የሃያ ሶስት አመት “ብላቴናው” ደኢህዴን፣ እንደ ካሱ ኢላላ ያሉትን አመራሮች አንፃራዊ የስልጣን ቆይታ ጊዜ ያላቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በመተካካት ስም ካላሰናበተ በስተቀር፣ በተለይም በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ የድርጅቱ አመራሮች “ለጋ ባለስልጣናት” ናቸው፡፡ በመሆኑም በደኢህዴን ቤት “ቁም ስቅል” ከሚያሳየው ግምገማ ጋር በተያያዘ ከሚሰናበቱ የድርጅቱ አመራሮች ውጪ ያን ያህል ነባር አመራር በመተካካት ስም የሚሰናበት አይመስልም፡፡ ከዚህ አኳያ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ደሴ ዳልኬ፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ሽፈራው ተ/ማርያም፣ አለማየሁ አሰፋ፣ አሰፋ አብዩ፣ ደበበ አበራ ነባር ስልጣናቸውን በማጠናከር/በማሻሻል የደኢህዴንና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚን ይቀላቀሉ ይሆናል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁለተኛው ዙር የስልጣን ዘመናቸው “የጀርባ አሸከርካሪዎችን” ተፅዕኖ ለመቀነስ በተቻለ መጠን የደኢህዴን ሥራ አስፈፃሚ አባላት ጠንካራ እንዲሆኑ ያቅማቸውን ያህል መሞከራቸው አይቀሬ ነው፡፡

ያም ተባለ ይህ ግን፣ የሀገሪቱ ደህንነት መዋቅር የአደረጃጀት ባህሪ አስካልተቀየረና ፍትሃዊ የብሔር ውክልና እስካልያዘ ድረስ፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉ ነባር የህወሓት ጄነራሎች በጡረታ ለተተኪ አመራሮች ቦታ እስካለቀቁ ድረስ … የደህንነት መስሪያ ቤቱና መከላከያ ሰራዊት የህወሓትን የፖለቲካ አሸከርካሪነት በማስቀጠሉ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይዘዉ ይዘልቃሉ፡፡ “እስከ መቼ?” የኢትዮጵያ ህዝብ የቀንድ አዉጣ ኑሮዉን እስከሚያቆም ድረስ!!

(የዚህ ጦማር አቅራቢ ጋዜጠኛ ሙሉዓለም ገ/መድህን ሲሆን በቅርቡ “የኢሕአዴግ ቁልቁለት” በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሀፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ይህ ጽሁፍ በተለይ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ ነው፡፡)

Received on Sun Aug 23 2015 - 10:18:11 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved