Ethsat.com: በህወሃት ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት መኖሩን አቶ ስብሃት ተናገሩ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 18 Feb 2015 23:32:42 +0100

በህወሃት ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት መኖሩን አቶ ስብሃት ተናገሩ

18.02.2015

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐት) ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት የሚያራምዱ ወገኖች መኖራቸውንና ሕገመንግስቱም በተሟላ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን አቶ ስብሃት ነጋ የቀድሞ የህወሃት ሊቀመንበር እማኝነታቸውን ሰጡ፡፡

አቶ ስብሃት ነጋ የካቲት 9 እና 10/2007 ዓ.ም ከወጣው አዲስዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በህወሃት ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት መኖሩን አምነዋል፡፡ «ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት በመንደራችን አለ፡፡ ቢሮክራሲው የጸዳ አይደለም፡፡ እንግዲህ ፓርቲውን የሚመራው መንግስት ነው፡፡ ተወዳዳሪና ቀና የሆነ ቢሮክራሲ ገና አልተገነባም፡፡ ከላይ እስከታች ሕገመንግስቱ በትክክል እየተተገበረ ነው ወይ የሚለው ጎዶሎ አለበት» ብለዋል፡፡

«የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ወይ» በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ስብሃት የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን አረጋግጠው ችግሩን የምንፈታው ሕዝቡን ይዘን ነው ብለዋል፡፡ አይይዘውም «በአስተማማኙ ጎዳና እየተደረገ ያለው ሩጫ ዘገምተኛና እንከን ያለበት ነው፡፡ እንከን ስል ቢሮክራሲው የተሳለጠ ባለመሆኑና የቀናነት ጉድለት ስላለ ሕዝቡ በሚገባ ደረጃ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ የተዛባ አመለካከትና የተንዛዛ አሠራር ይስተዋላል፡፡ ይህ ክፍተት መቀረፍ አለበት፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ስህተቱን ይፋ የሚያደርግና የሚያርም ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ» ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በ1993 ዓ.ም በልዩነት ህወሓትን ጥለው የወጡ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ጉዳይንም በተመለከተ ሟቹ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስን በመደገፍና የእነስዬ አብርሃን ቡድንን በመንቀፍ  በሰጡት አስተያየት መነሻቸው የኤርትራ ጉዳይ ይሁን እንጂ ዋና ዓላማቸው የሥልጣን ጥማት ነው ብለዋል፡፡ «የሥልጣን ጥማቱ ታምቆ የቆየ ነው፡፡ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የመውረሩን ጉዳይ ያለመከታተላችን የሁላችንም ድክመት ነው፡፡ ቀደም ብለን ማወቅ ነበረብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለሰላም አሟጠን ዕድል እንስጥ፣ ዕድሉ ካላዋጣን መዋጋት ማን ይከለክለናል የሚሉ የአመራር አባላት ነበሩ፡፡ እኛ ከኢሳያስ ተሸለን መገኘት አለብን፤  የእኛ ሰዎች ግን እንደ ኢሳያስ ሆኑ፡፡ ነፋስ በኤርትራ መጣ ከተባለ እንዋጋ ነው የሚሉት፡፡ ከወላጆቻቸው በምንም አይለዩም፡፡ ስንወረር ዝም ብላችሁ አያችሁ የሚለውን እንደምክንያት ወስደው ቡድን ፈጠሩ»ብለዋል፡፡

ተወልደ የህወሃት ምክትል ሊቀመንበር እያለ፣ ስዬም የመከላከያ ሚኒስትር እያለ ኤርትራ ነጻነትዋን ስታገኝ የአሰብ ወደብ ጉዳይ አብሮ ያለቀለት ነበር ያሉት አቶ ስብሃት፣ አሁን የአሰብ ጉዳይ እንደልዩነት የሚነሳው ሰበብ እንጂ ጉዳዩ ወንበር ፍለጋ ነው ሲሉ የእነስዬን ቡድን በሥልጣን ጥመኝነት ፈርጀዋል፡፡

ጡረተኛው አቶ ስብሃት በአሁኑ ወቅት እምብዛም እንቅስቃሴ የሌለውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የሠላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡

********************************************************************************

ሚኒስትሮችንና አፈ-ጉባኤዎችን ጨምሮ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በቤተ መንግስት የተገመገሙበት ሰነድ ኢሳት እጅ ገብቷል።

18.02.2015

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግምገማው የተካሄደው እንደተለመደው ባለስልጧናቱ በየተራ አስቀድመው ችግራቸውን እንዲናገሩ በማድረግና የራሱን ችግር በተናገረው አመራር ላይ ሌሎቹ ያላቸውን ተጨማሪ ትችት እንዲያቀርቡ በማድረግ ነው።

በአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ መሪነት በተካሄደው በዚህ ግምገማ  ከ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ  የተገመገሙት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣”የሀሰት የስራ አፈጻጽመ ታቀርቢያለሽ” የተባሉት የሴቶችና የወጣቶች ሚኒስትር ዘነቡ ታደሰ፣”ሳሞራን ትፈራዋለህ”ተብለው የተገመገሙት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ፣”ኮምፒዩተርና ሞባይል ላይ ጥብቅ ትላለህ” የተባሉት አቶ ሬድዋን ሁሴን፣”ከባልደረቦችሽ ጋር ትጋጫለሽ”የተባሉት ወይዘሮ አስቴር ማሞ ፣”ፈሪ ነህ” የተባሉት ዶፐክተር ካሱ ይላላ፣ “ከደባል ሱስ የጸዳህ አይደለህም”የተባሉት  የገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፊያን አህመድ  እና ሌሎች በርካታ ባለስልጣናት ” ሲ” አግኝተዋል።

የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ፣ የትምህርት ሚኒስትር ሽፈራው ሽጉጤ፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ጸጋይ በርሄ፣ የ አማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዓለምነው መኮንን፣አቶ ስዩም መስፍን፣አቶ አርከበ እቁባይ  እና ሌሎች በርካታ ሹመኞች “ቢ” ውጤት ተሰጥቷቸዋል።

እስካሁን ለ ኢሳት በደረሰው ሰነድ በግምገማው “ኤ”ውጤት የተሰጣቸው የ ኢህአዴግ አመራር የህወሀቱ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ብቻ ናቸው። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም “በሶሻል ሚዲያ የግለሰቦችን ታሪክ ለራስህ ገፅታ ግንባታ አውለሀል፣ ስራ ታዘገያለህ” የሚሉና ሌሎችም ደከማ ነጥቦች የተነሱባቸው ቢሆንም፤ ከሌሎቹ አመራሮች በተለየ ሁኔታ “የቀረበብኝን ድክመት”አልቀበልም በማለት ነው ውድቅ ያደረጉት። ሌሎቹ  አመራሮች በሙሉ፤ ከግምገማቸው በሁዋላ፦ “ድክመታችንን ተቀብለናል፤እናሻሽላለን”

ማለታቸውን ተከትሎ ነው “ቢ” እና “ሲ” የተሰጣቸው።  “ሲ”ከተሰጣቸው የኢህአዴግ አመራሮች መካከል ” ኢህአዴግ ገለልተኛ ነው” እያለ የሚናገርለትን ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነት የሚመሩት ፕሮፌሰር መርጋ  በቃና ይገኙበታል። በኢህአዴግ ውስጥ ቀደም ሲል አንድን ነገር “ድርጅቱ ነው ያለው” ሲባል፤ “መለስ ነው ያለው”ማለት እንደሆነ የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ ገሠሰ “የመለስ ትሩፋቶች” በተሰኘው መጽሐፋቸው መግለጻቸው ይታወቃል። ኢሳት እጅ የገባው የግምገማ ሰነድ እንደሚያመለክተው፤  የመለስን ቦታ-አቶ በረከት ስምኦን መያዛቸውን ነው።

አቶ ሬድዋን፤”የሀገሪቱን ገጽታ ለውጪ ሚዲያ ዝግ አድርገኸዋል” ተብለው ሲገመገሙ <<ዝግ ያደረኩት  እኔ ሳልሆን ድርጅቱ ነው” ብለው መልስ የሰጡ ሲሆን ፤ <<ድርጅቱ ማን ነው?>>ተብለው  በአቶ ሀይለማርያም ሲጠየቅ፦<<በረከት>> በማለት መልሰዋል።

Received on Wed Feb 18 2015 - 17:32:50 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved