(ዘ-ሐበሻ) ሕወሓት የሚመራው የኢትዮጵያ ገዢ በኢትዮጵያ የተከሰተውን እና 15 ሚሊዮን ሕዝብን ለረሃብ ያጋለጠውን አደጋ ለመሸፋፈን ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋዳ ሥራዎችን ከመስራት በተጨማሪ መረጃዎች እንዳይወጡ እስከማፈን ደረጃ መድረሱን ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት; የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስተርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በአንድ ላይ ተቀናጅተው እየሰሩት የሚገኘው የመረጃዎችን የማፈን ሥራ ታች ድረስ ወርዶ እስከ ፓርቲ አባላትና “ደጋፊ” የተባሉ ሰዎች ጭምር እንዲሰራበት እየተደረገ ነው:: “ረሃቡን አስታከው ለውጭ መንግስታት ሊያሳጡን የሚሞክሩትን መታገል አለብን” በሚል እነዚህ ሶስት መስሪያ ቤቶች ባወጡት መመሪያ መሠረት የውጭ ጋዜጠኞችም ሆነ የረድኤት ድርጅቶች ረሃቡ ወዳለበት ቦታ ሄደው ፎቶ እንዳያነሱ; ቭዲዮ እንዳይቀርጹ; ማንኛውንም ቃለምልልስ እንዳያደረጉ ተከልክሏል:: በተለይ ቢቢሲ በቅርቡ በኢትዮጵያ በአንድ ትንሽ ክልል ስፍራ ብቻ በቀን 2 ህፃናት በረሃቡ እየሞቱ እንደሆነ መዘገቡን ተከትሎ አለም አቀፍ ሚዲያዎች እና የአፍቃሬ ሕወሓት መንግስት ደጋፊ የሆኑ ሃገራት ሳይቀር ከዚህ ቀደም “ልማታዊ መንግስት” እያሉ ሲያሞካሹ የነበረውን አፋቸውን በመጠራረግ ረሃቡን እና መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ እንደገና እየመረመሩ እንደሚገኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ::
እንደ ዘ-ሐበሻ ምንጮች ዘገባ በቅርቡ በቢቢሲ የቀረበችውን እናት የአማራ ክልል ጋዜጠኞች አስገድደው ቃለምልልስ ያደረጓት ሲሆን በቅርቡም በመንግስት ሚዲያዎች ላይ “አልራበኝም” ዓይነት ንግግር በማስደረግ የቢቢሲን ዘገባ ለማስተባበል ሥራ እየተሰራ ይገኛል::
ከሥስቱ መስሪያ ቤቶች በተላለፈው መመሪያ መሠረት የመንግስት ሃላፊዎች ከላይ እስከታች በየሶሻል ሚዲያው በመውጣት ችግሩን መንግስት ተቆጣጥሮታል እያሉ መጻፍ እና መናገር አለባቸው:: “ተቃዋሚዎች የመንግስታችንን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ሆን ብለው የሚያደርጉት ሤራ ነው” እያሉም በውጭ ያሉ ኤምባሲዎችና ተላላኪዎች እንዲያነገሩ ትዕዛዝ ከመተላለፉም በላይ መንግስትን ይደግፋሉ ለተባሉ የውጭ ጋዜጠኞች ወደ ሃገር ቤት እንዲገቡና መልካሙን ነገር ብቻ እንዲዘግቡ ኢምባሲዎች መሥራት እንዳለባቸውም የወጣው መመሪያ ሲያመለክት ስለመንግስት መጥፎ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ የተባሉ ጋዜጠኞች ግን ረሃቡ ወዳለበት ቦታ እንዳይሄዱ/ ምስል መቅረጽና ቃለምልልስ ማድረግ እንዳይችሉ የኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ፈቃድ እንዳይሰጥ ት ዕዛዝ ወርዷል::
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት 15 ሚሊዮን ሕዝብ በመራቡ የተነሳ በወዳጅ ሃገሮቹ ሳይቀር በመጥፎ አይን እየታየመምጣቱ በስርዓቱ ውስጥ “ገጽታችን ተበላሸ” በሚል ራሱን የቻለ ሽብር ፈጥሯል::