Goolgule.com: ኢህአዴግ ኅብረ ብሔር ፓርቲ ሲሆን ኤፈርትና ሚድሮክ ይዋሃዳሉ?

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Fri, 1 Apr 2016 17:36:09 +0200

ኢህአዴግ ኅብረ ብሔር ፓርቲ ሲሆን ኤፈርትና ሚድሮክ ይዋሃዳሉ?

“የጥናቱ ውጤት በ2003 ይቀርባል” አቶ መለስ
effort and midroc
 

ኢህአዴግን ወደ ኅብረ ብሔር ፓርቲ የማሸጋገር ሥራ እየተሰራ መሆኑንን ሃይለማርያም ደሳለኝ የአገሪቱን “ምሁራን” ባናገሩበት ወቅት ፍንጭ ሠጥተዋል። የዛሬ ሰባት ዓመት ከመስከረም 5 እስከ 7 ቀን 2001 ዓ.ም ሃዋሳ ተካሂዶ በነበረ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ አቶ መለስ ድርጅታቸው ወደ ብሄራዊ ፓርቲ ወይም አሃዳዊ ፓርቲ ስለመሸጋገሩ እየተጠና መሆኑንን ተናገረው በቀጣዩ ጉባኤ ሪፖርቱ እንደሚቀርብ ቃል ገብተው ነበር። ጥያቄው ዝም ብሎ የቀረበ ሳይሆን ታስቦበትና ከዚህ ቀደም የተሰጠውን መልስ በማስታወስ ነበር። ይህ የሚያሳየው አሃዳዊ ፓርቲ የመሆን ጉዳይ የዛሬ አለመሆኑን ነው።

ከብአዴን እንደሆነ የጠቀሰ አንድ ጉባኤተኛ ጥያቄውን ሲያነሳ ቀደም ሲል ይህ ጉዳይ ተነሥቶ እንደነበር ጠቆመ። በማስከተልም በወቅቱ ጥያቄው ሲነሳ አጥኚ ግብረ ሃይል መሰየሙን አወሳ። አያይዞም “ጉዳዩ የት ደረሰ?” በሚል ማሳሰቢያ መሰል ንግግር ምላሽ ጠየቀ። እንደውም አጥኚው ክፍል ምላሽ ቢሰጥበት ሲል መንገድ አመላከተ። በወቅቱ አቶ ተፈራ ዋልዋም ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጎን ተቀምጠው ለጥያቄው ድጋፍ ሰጥተው እንደነበርም በጉባኤው የተሳተፉ ያስታውሳሉ። ሌሎች ድጋፍ የሰጡም ነበሩ።

አቶ መለስ ድርጅታቸው ኅብረ ብሔር እንዲሆን ለቀረበው ጥያቄ “ይህንኑ ጉዳይ እንዲያጠና የተቋቋመው ሃይል እያጠናው ነው” ሲሉ ነበር የመለሱት። በመልሳቸው ትግበራው የጥያቄውን ያህል ቀላል ጉዳይ እንደማይሆን አልሸሸጉም ነበር። ይህንኑ የአቶ መለስ መልስ ተከትሎ ወዲያውኑ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰነዘሩ። የአሁኑ ብአዴን “ኢህዴን” ተብለህ መጠራት አትችልም ተብሎ ወደ ብአዴን የተከለሰው የእነ አዲሱና በረከት ድርጅት በነሱም ባይሆን በሌሎች አባላቱ በኩል ቅሬታውን አሰምቷል። ከሁሉም በላይ ግን ሚዛን የደፋው የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ኤፈርት ላይ የሚያሰሙት ሹክሹክታ ነበር። ኤፈርትን “ቦዬ” በማለት አጥብቀው የሚጠሉት የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። “ቦዬ” ማለት ያገኘውን ሁሉ የሚያግበሰብስ አሳማ እንደ ማለት ነው።

በሌላ በኩል ኢህአዴግን ኅብረ ብሔር ፓርቲ እንዳይሆን በግንባር ቀደምትነት ቅሬታ የሚያሰማው ህወሃት ነው። በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ ያላቸው እንደሚሉት ህወሃት በሃሳቡ የማይስማማው ኤፈርት የተሰኘው የድርጅቱ የንግድ ኢምፓየር ባካበተው ሃብትና ነጻ አውጪው ግንባር ካለው የቆየ ህልሙ በመነሳት እንደሆነ ይነገራል። ኢህአዴግ ኅብረ ብሔር ፓርቲ ከሆነ በቅድሚያ በግንባሩ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ይከስማሉ። ድርጅቶቹ ከከሰሙ ያላቸው ሃብት ይቀላቀላል። የሁሉም ድርጅቶች የንግድ ተቋማት ተዋህደው ከሁሉም ወገኖች የተውጣጡ የቦርድ አባልት እንዲመሩት ይደረጋል። ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር ብሎ ለሚጠራው ህወሃት ይህ አካሄድ ትክክለኛ የውኅደት አሠራር ቢሆንም እስካሁን ሊዋጥለት ያልቻለ እውነታ ነው፡፡

ከራሱ ከህወሃት አባላት በየጊዜው የሚያፈተልከው የኤፈርት ጉዳይ እስካሁን መልስ ቀርቦበት አያውቅም። ከህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድም ልዩ ጥያቄ የሚነሳው በጀቱ የት ደርሷል? ካፒታሉ በጥሬ ገንዘብና በቁስ ሲተመን በጥቅሉ ምን ያህል ሃብት አለው? ለምን ኦዲት አይደረግም? የኦዲት ሪፖርትስ ለምን አይቀርብበትም? የሚሉና በርካታ የግልጽነት ችግሮች ናቸው። መልስ ግን የለም። የሚገርመው ግን ኤፈርትን በተለያየ የአመራር ደረጃ ይመሩ የነበሩ ከኃላፊነት ሲነሱ ወይም ሲባረሩ፣ ከአገር ሲለቁ ወይም ሥራ ሲለቁ ስለ ድርጅቱ የሚሉት ነገር አለመኖሩ ነው።

ህወሃት በዘመነ ህንፍሽፍሽ ለሁለት ተሰንጠቆ ስለ መበስበስ አደጋ በአደባባይ ሲነገር፣ ሙስና ስልታዊ መምቻ መሳሪያ ሆኖ ሲታወጅና የመለስን ህልውና የተፈታተኑ ናቸው የተባሉትን ሲከረቸሙ፣ አንዱ አባራሪ ሆኖ ሌላው ሲባረር የኤፈርት ጉዳይ ግን ለሁሉም ወገኖች በእኩል ደረጃ ሚስጥርነቱ የተጠበቀ መሆኑ ነው።አባራሪውም ሆነ ተባራሪው ኤፈርት ላይ ዝግ ናቸው። ኦዲት ተደርጎ እንደማያውቅ በገደምዳሜ ከመናገራቸው በቀር እነሱም ሲፈጩና ሲከኩ በነበረበት ወቅት ስለሚያውቁት ሃቅ አያወሩም፤ አያብራሩም፤ አይጽፉም። ከሁለት ዓመት በፊት በድንገት ከኤፈርት ዋና ኃላፊነታቸው ሳይሰናበቱ ካገር ወጥተው ስደትን የተቀላቀሉት የህወሃት ሰው ምንም አለመተንፈሳቸው አግራሞቱን እጅግ የሚያሰፋ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። እናም ይህ እውነት ባለበት ሁኔታ ኢህአዴግን ኅብረ ብሔር ፓርቲ ለማድረግ ታስቧል የሚባለው ቧልት ከመሆን አይዘልም የሚል ስምምነት አለ።

ቀደም ሲል ሲብላሉና በተባራሪ ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች አሁን አሁን አደባባይ መውጣት ጀምረዋል። “ታላቋ ትግራይ” ድንበሯ ኤርትራን ዘልቆ እንደሚገባ አፍቃሪ ህወሃት ድረገጾች ይፋ እያደረጉ ነው። ከኤርትራ በኩል ምላሽ ባይሰጥም “ትግራዋይ” ኤርትራን ጠቅልላ “የታፈረችና የተከበረች ታላቅ አገር” ለመሆን የሌሎችን የመብትና የማንነት ጥያቄ እየጨፈለቀች በመገስገስ ላይ መሆንዋ አሁንም የሃይለማርያምን ቃል ትርጉም አልባ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተቺዎች ይናገራሉ።

አሁን ከፖለቲካው ጡዘት ጋር ተዳምሮ ቦዬ የደረሰበት ደረጃ የድርጅቶችን ውህደት የማይታሰብ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች ሃሳቡን “ጊዜ ወለድ ማደናገሪያ” ይሉታል። ላለፉት 25ዓመታት አገር እየመራ በሽፍትነት ዘመኑ “የትግራይ ነጻ አውጪ” የሚለውን ስሙን ለመቀየር የሚያንቀው ህወሃት፣ ስሙን ፍቆ፣ ሃብቱን አዋህዶ፣ ለአብላጫ ድምጽና ለአብዛኞች ውክልና ለመገዛት ምሎ አሃዳዊ ፓርቲ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ “አሳማን ከተፈጥሮው ህግ ውጪ ዶሮ የማድረግ ያህል ነው” በማለት በሃሳቡ የሚሳለቁ ጥቂት አይደሉም። ምናልባት በእኩይ ሳይንሳዊ “ጥበብ” ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት ዘመን እስኪመጣ ላሁኑ የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡

ለአገራዊ ጉዳይና ለአገሪቱ ታሪካዊ ዳራዎች ደንታ የሌለው ህወሃት፣ አገሪቱን ባህር አልባ ያደረገው ህወሃት፣ ዜጎቹን የሚጨፈጭፈው ህወሃት፣ የኢትዮጵያን ትልቅነትን አጥብቆ የሚጠላው ህወሃት፣ የሚምልባቸውን አርሶ አደሮች የሚበላው ህወሃት፣ ክልሉን እያሰፋ ሌሎችን የሚያቀጭጨው ህወሃት፣ ባህሪውና ፍጥረቱ ሁሉ ብሔራዊ የሚባሉ የአንድነት ማሳያ ታሪኮችን የሚበላው ህወሃት፣ አገሪቱን በጎሳና በብሔር ቆራርጦ ወደ ረመጥነት የቀየረው ህወሃት፣ ህጻናት አረጋዊ ሳይል በአልሞ ተኳሾች የሚገድለው ህወሃት፣ እመራቸዋለሁ ከሚላቸው ዜጎች ይልቅ ለሌሎች ክብር የሚሰጠው ህወሃት፣ በሙስናና በዝርፊያ “እስከ እንጥሉ የገማው” ህወሃት፤ ዓላማው፣ ሃሳቡና ፍጥረቱ ውኅደት አድርጎ ብሔር ተኮር ውጥኑን ሊያስቀይረው አያስችለውም ሲሉ ዜናውን ከጅምሩ ያጣጥሉታል።

እነዚህ ወገኖችን ጨምሮ በርካታ የኦህዴድ አባላት ሚድሮክና ኤፈርት ግንኙነት እንዳላቸው ያምናሉ። የሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ድንገት ሃብታም መሆንና ግብር እንኳን ሳይከፍሉ ኦሮሚያ ላይ እንዲፈነጩ የተፈቀደላቸው ከህወሃት ጋር ባላቸው የንግድ ትሥሥር እንደሆነ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ ያምናሉ። እነዚህ ወገኖች ህወሃት አሃዳዊ ፓርቲ የሚሆነው ኤፈርትን በኦፊሴል ከሚድሮክ ጋር ሲያዋህድ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። አሁን አሁን ኤፈርት ወርቅ ባለበት ሚድሮክን እየተከተለ መሬት መመራቱ የዚሁ የግንኙነቱ ማደግ ውጤት እንደሆነ እነዚሁ ክፍሎች ይናገራሉ።

ከሁሉም በላይ በ2001 ሃዋሳ በተደረገው የኢህአዴግ ጉባኤ በተባለው መሰረት ጉዳዩን እንዲያጠና የተሰየመው ኮሚቴ ጥናቱ ስንት ዓመት የሚፈጅ ሆኖ ነው የጥናቱ ውጤት የማይገለጸው? ከ2001 በፊት የተቋቋመው ኮሚቴ ለመሆኑ አለ? እነማን ናቸው? ጥናቱስ ተካሂዷል? ወይስ ጨበጣ ነው? አቶ መለስ አጥኚው ኮሚቴ የጥናቱን ውጤት በ2003 ኦህዴድ በሚያዘጋጀው የአዳማው ጉባኤ ያቀርባል ብለው ነበር። ዛሬ ድረስ የተሰማ ነገር የለም። ስለ ጉዳዩ የምታውቁ አስተያየታችሁን ላኩልን።

ትግራይን መልሶ ለማቋቋም የተመሠረተው ኤፈርት በስድስት ዘርፎች ማለትም በፋብሪካ ምርት (ማኑፋክቸሪንግ)፣ በአገልግሎት ሰጪ፣ በሸቀጥ ንግድ፣ በግንባታ (ኮንስትራክሽን)፣ በማዕድን ፍለጋ እና በግብርና ሥራ የተሰማሩ የ14 ኩባንያዎች ባለቤት እንደሆነ በድረገጹ ላይ ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ መሰቦ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ አዲግራት የሚገኘው የመድኃኒት ፋብሪካ፣ አልመዳ ጨርቃጨርቅ፣ ጉና፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ ኢዛና የመዓድን ፍለጋ፣ በወልቃይት ጠገዴና በሁመራ ዘመናዊ የግብርና ተግባር የሚያከናውነው ሂወት ዘመናዊ እርሻ “ሜካናይዜሽን”፣ እና ሌሎች ኩባንያዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ሸቀጣቸውን “ለማከፋፈል” በአዲስ አበባ በጥቂት ሠራተኞች የሚንቀሳቀስ የማሰራጫ ቢሮ ሲኖራቸው ፋብሪካዎቹ በትግራይ ውስጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንደከፈቱ ድረገጹ ጨምሮ ይናገራል፡፡ የኤፈርትን ተልዕኮ ምን እንደሆነ ድረገጹ ሲያስረዳም በተለይ በትግራይ ድህነትን በመቀነስ ወይም በማስወገድና ልማትን በማስፋፋት ቀዳሚና ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡

Received on Fri Apr 01 2016 - 11:36:09 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved