Dec. 06, 2016
Watch this.
ESAT Daily News DC Tue 06 December 2016
ESAT Daily News Amsterdam December 06,2016
http://ethsat.com/2016/12/esat-daily-news-amsterdam-december-062016/
ኅዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር በነጻነት ሃይሎች እና በአገዛዙ ወታደሮች መካከል የሚካሄደው ውጊያ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ያልጠበቀው ጉዳት የደረሰበት አገዛዙ የአርሶአደሮችን ቤቶችን በማቃጠል የበቀል እርምጃ እየወሰደ ነው።
በወገራ ወረዳ በእንቃሽ ከትናንት በስቲያ ከ10 በላይ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን፣ ዛሬ ማክሰኞ ደግሞ በጃኖራ አቶ መስፍን የተባሉ ታጋይ ሁለት ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ሲሆን፣ ከጠዋት እስካሁን የተኩስ ለውውጥ እየተካሄደ ነው።
ባለፉት ሳምንታት በተደረገው ውጊያ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው ጉዳት በመከላከያ ላይ መሆኑን የሚገልጹት የአካባቢው ምንጮች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች አስከሬን ዛሬ መቀበሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል በቋራ ወረዳ በርካታ ዜጎች መሳሪያ አስረክቡ እየተባሉ እየተደበደቡና እየታሰሩ ነው ።
በሰሜን ጎንደር ዞን በ ቋራ ወረዳ በሊገበር ቀበሌ የሚገኙ በርካታ አርሶአደሮች በአካባቢው በተሰማሩት ታጣቂዎች ክፉኛ መደብደባቸውን ፣ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ጫካ መግባታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ድብደባውንና እስራቱን ለማምለጥ ጫካ የገቡ አርሶአደሮች ሚስቶች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ፣ በታጣቂዎች ተገደው መደፈራቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
ዋና ሃይሌ እና ደረበ ደማስ የተባሉት አርሶአደሮች በድብደባ ብዛት እጃቸው ከጥቅም ውጭ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ሌላ አርሶአደር ሽፍታ አብልታችሁዋል በመባላቸው ባልና ሚስቱ ታስረው፣ አምስት ልጆቻቸው ለችግር ተደርገዋል። አገዛዙ ራሱ ያስታጠቃቸውን ሚሊሺያዎች ሳይቀር መሳሪያቸውን መግፈፍ መጀመሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ህብረተሰቡ ለታጣቂዎች በግዳጅ ምግብ እንዲያቀርብ እየተደረገ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
መሳሪያ የማስፈታቱ እንቅስቃሴ በሌሎችም የክልሉ ዞኖች እየተካሄደ ሲሆን፣ የጦር መሳሪያ እንደሌላቸው የገለጹ አርሶአደሮች እስር ቤቶችን እያጨናነቁ ነው።
በሰሜን ጎንደር በአገዛዙ ወታደሮችና በነጻነት ሃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ አገዛዙ መሳሪያ የማስፈታቱን እንቅስቃሴ አጠንክሮ እንዲገፋበት አድርጎታል።