Goolgule.com: የዶ/ር መረራ እስር፤ ህወሃትና ምዕራባውያን ፖለቲከኞች

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 7 Dec 2016 18:43:39 +0100

የዶ/ር መረራ እስር፤ ህወሃትና ምዕራባውያን ፖለቲከኞች

"[ህወሃት] ይበልጥ አምባገነናዊ ወደሆነ አስተዳደር እያመራ ነው"
mereragudina-al-jazeera
 

ከአውሮጳ ስብሰባ ወደአገራቸው ሲመለሱ የታፈኑትና በኋላ መታሰራቸው የተሰማው ዶ/ር መረራ ጉዲና የአሜሪካና የአውሮጳ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ጉዳይ የከረረ አቋም እንዲወስዱ እያደረጋቸው መሆኑ ተሰምቷል፡፡ [ህወሃት] “ይበልጥ አምባገነናዊ ወደሆነ አስተዳደር እያመራ” ሲሉ አንድ የአሜሪካ ሴናተር ተችተዋል፡፡

ana-gomes-euractiv

አና ጎሜዝ (ፎቶ EURACTIV)

መታሰራቸውን እንደሰሙ “I am very upset with this” ያሉት የአውሮጳ ፓርላማ አባል አና ጎሜዝ የዶ/ር መረራ እስር በጣም እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ ለስቃይና እንግልት እንደሚዳረጉ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም “በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በጣም ጥብቅ የሆኑ አካሄዶች ከአውሮጳ ኅብረት በኩል ሊደረግ ይገባል” የሚል ማሳሰቢም ሰጥተዋል፡፡ (ሙሉው ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል)፡፡

በመቀጠል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ይህንን መግለጫ አወጣ፤ “የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ መንግሥት መታሠራቸውን ሰምተናል፡፡ ዘገባው አሳስቦናል፡፡ መንግሥቱ በዶክተር መረራ ላይ ያለውን ማንኛውንም ክሥ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ በፅኑ እናበረታታለን፡፡ የመታሠራቸው ነገር እውነት ከሆነ አድራጎቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ድምፆችን ለማፈን የሚጣሉት ገደቦች እየተጠናከሩ ለመምጣታቸው አንድ ተጨማሪ ማሳያ ነው የሚሆነው፤ በግልፅ ለመናገር ደግሞ ኢትዮጵያ ያወጀችው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ምናልባት (ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት እና የኢትዮጵያውንን ሕገመንግሥታዊ መብቶቻቸውን ለመካድ የታቀደ ነው እንድንል ያደርገናል፡፡ ይህ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ ጊዜ ከተሰጠው የፖለቲካ ተሃድሶ ተስፋ ጋር የሚጻረር ነው፡፡)” (መግለጫው እዚህ ላይ ይገኛል)

ben cardin

ሴናተር ቤን ካርዲን

“የዶ/ር መረራ ጉዲና እስር በመንግስቱ ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ የፖሊቲካ ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ ነው። በመሆኑም በአስቸኳይ መለቀቅ አለባቸው” በማለት የጠየቁት በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ አንጋፋ አባል የሆኑት ሴናተር ቤን ካርዲን ናቸው፡፡ ሴናተሩ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የታሰሩት የተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ የጠየቁበትን ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥተዋል

የምክር ቤት አባሉ አክለውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና የሲቪል ማኅበረሰብ ታጋዮችንም እንዲፈታ፣ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድና እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎትና አቅርቦቶች ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ፤ ሲሉ ጠይቀዋል። (የሴናተሩ መግለጫ እዚህ ላይ ይገኛል)

chris coons

ሴናተር ክሪስ ኩንስ

በመቀጠልም በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሴናተር ክሪስ ኩንስ ከዶ/ር መረራ መታሰር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ ያሳሰባቸው መሆኑን በመጥቀስ ይህንን ብለዋል፤ “ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ይበልጥ አምባገነናዊ ወደሆነ አስተዳደር እያመራ ያለበትን አዝማሚያ የሚጠቁም ሌላ አዋኪ ምልክት ነው። ውስብስቡን ውስጣዊ የፖለቲካና የክልል አወቃቀር፤ እንዲሁም ከባድ ሊሰኙ የሚችሉትን ታሪካዊ ገጠመኞቻቸውን እገነዘባለሁ። ይሁንና መንግሥቱ በቅርቡ የወሰዳቸው የኃይል እርምጃዎች ግን ዘለቄታ ላለው ዲሞክራሲ ተጨባጭ አደጋዎች ናቸው” ብለዋል። (ህወሃት ላለፉት 25 ዓመታት አምባገነናዊ ሥርዓት ያላራመደ በሚምስል የተናገሩት) ሴናተሩ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉና በመናገር ነጻነት፣ በመያዶች፣ እና በሌሎች መብቶች ዙሪ በህዝቡ ላይ የተጣለው ገደብ ይበልጥ አምባገነናዊ ወደሆነ አዝማሚያ የሚወስድ መሆኑን ያላቸውን ሥጋት ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለምልልስ አስታውቀዋል፡፡ (እዚህ ላይ ይገኛል)

የተለያዩ ዓለምአቀፍ ሚዲያ ስለ ዶ/ር መረራ መታሰር በስፋት ዘግበዋል ቢቢሲአልጃዚራኤኤፍፒ ከFrance 24ዋሽንግተን ፖስት፣ ሌሎችም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ግፍና በደል ከመረራ እስር ጋር አያይዘው ዘግበዋል፡፡

የዶ/ር መረራ ጉዲናን መታሠርና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ በአሜሪካ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች በህወሃት ላይ ይህንን መሰሉን አቋም መውሰድ ከኦባማ የሥልጣን መልቀቅ ጋር የሚያይዙ ወገኖች አና ጎሜዝ በመግለጫቸው እንደተናገሩት ጥብቅ አቋም በኢህአዴግ ላይ የሚወሰድበት ሁኔታ ከተፈጠረ አሜሪካም ይህንኑ መስመር ልትወስድ ትችላለች የሚል አስቴየት ይሰጣሉ፡፡ ከቢል ክሊንተን የሥልጣን ዘመን ጀምሮ አሁን ደግሞ በኦባማ አስተዳደር የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ከአድዋ ወያኔ ባልተናነሰ መልኩ ለህወሃት ግልጽ ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩት እንደነ ሱዛን ራይስ የመሳሰሉ ባለሥልጣናት የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው “መጪውን ጊዜ ለኢህአዴግ ብሩህ” አያደርገውም የሚለውን ተስፋ የሚጋሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ (የዶ/ር መረራ ፎቶ: Simona Foltyn)

Received on Wed Dec 07 2016 - 12:43:38 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved