DECEMBER 14, 2016
በሱዳን በሰላም ማስከበር ተግባር ተሰማርተው የቆዩት ኮ/ል ሃጎስ ምስግና መገደላቸውን ምንጮች አስታወቁ። በትግራይ ኢሮብ ወረዳ የተወለዱት የቀድሞ የህወሃት ታጋይና የመከላከያ መኮንን ኮ/ል ሃጎስ ሆን ተብሎ ከኌላ በተተኮሰባቸው ጥይት ጭንቅላታቸውን ተመተው መሞታቸው ሲታወቅ፣ ለግድያ ያበቃቸው በጥቂት ከፍተኛ ጄኔራሎች የሚፈፀመውን ሙስና በተለይ በሰላም አስከባሪነት በሚሰማራው ወታደር የሚደርስበት ብዝበዛን በመቃወማቸው እንደሆነ ምንጮች አመልክተዋል። በ1996 ዓ.ም መለስ በመሩት ስብሰባ “ከደርግ በምን ተሻልን?” በማለት እንዲሁም የባድመን ጉዳይ በመቃወም መለስንና የስርአቱን አካሄድ በማውገዛቸው ከሰራዊቱ ተገለውና በቁም እስረኛ እንደቆዩ ምንጮች አስታውሰዋል። በሰላም ማስከበር ለሚሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የተባበሩት መንግስታት ለአንድ ወታደር ወርሃዊ ደመወዝ 1 ሺህ 70 ዶላር ይመድባል። በሱዳን ለአንድ አመት ብቻ እንዲቆይ ሲደረግ በወር 37 ዶላር ብቻ “የኪስ” ተብሎ ይሰጠዋል። ዋናው ገንዘብ አገር ቤት እንደሚከፈል በጄኔራሎች ከተነገረው በኋላ ሰራዊቱ አገር ሲመለስ “ለመከላከያ ሚኒስቴር” በሚል 60 በመቶ ይቆረጣል። የአመት 283 ሺህ ብር ሲሆን፣ 193 ሺህ ብር ገደማ ተቆርጦ ለወታደሩ 90 ሺህ ብር እንደሚከፈለው ይነገረውና ክፍያውም እየተቆራረጠ በተለያየ ወራት እንደሚፈፀም ምንጮች አብራርተዋል። ይህን ብዝበዛ የተቃወሙ የላይቤሪያ ዘማቾች በ97 በፍቼ መስመር መንገድ ዘግተው ፍትሃዊ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከሰራዊቱ ከሚመዘብሩት አንዱ ጄ/ል ዮሃንስ ገ/መስቀል ሲጠቀሱ ቦሌ ቴሌ መድሃኒአለም በ90 ሚሊዮን ብር ህንፃ አስገንብተው እንደሚያከራዩ ከዚህ ቀደም በዝርዝር መገለፁ ይታወቃል። ኮ/ል ሃጎስ ለግድያ ያበቃቸው የእነጄ/ል ዮሃንስን ከፍተኛ ምዝበራ አጥብቀው በመቃወማቸው እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል። በ1993 ጄኔራል በርሄ በቅፅል ስማቸው ሻእቢያ ሆን ተብሎ ከነባለቤታቸው መገደለቻው አይዘነጋም።
አርአያ ተስፋማሪያም