አሜሪካ ባልተለመደ ሁኔታ ኢህአዴግን ከመውቀስ አልፋ እያስጠነቀቀች ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ የጉዞ ማዕቀቡ እንዲነሳለት እየወተወተ ስለመሆኑ በተለያዩ መገናኛዎች ተደምጧል። የጎልጉል መረጃ አቀባይ የዲፕሎማሲ ምንጮች እንዳሉት አሜሪካ ለኢህአዴግ ጥያቄ መልሷ “ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም” የሚል ሆኗል። እነዚሁ ክፍሎች እንደሚሉት ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት የዴሞክራሲ፣ የሠብዓዊ መብቶችና የሥራ ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪ የሚመራ ልዑክ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ የአራት ቀን የስራ ቆይታ ባደረገበት ወቅት “በግልጽ ተወያይተናል” የሚል መግለጫ ቢሰጥም፣ እንደሚባለው ስምምነት ላይ አልተደረሰም። ለቪኦኤ አማርኛው ክፍል ብቻ መግለጫ የሰጡት ቶም ማሊኖዊስኪ “ለለውጥ የተገባውን ቃል ተግባራዊ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሃላፊነት” እንደሆነ መናገራቸው የተደረሰና የተቆረጠ ስምምነት አለመኖሩን ነው።
ረዳት ሚኒስትሩ እንዳሉት “በኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ ሥርዓቱን ለዝነተ ዓለም ለማፅናት በሚደረግ ትግል ወይንም ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በሚወሰድ እርምጃም ሊሆን አይገባም” ማለታቸውንና “ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ሥልጣን ማስረከብ ደረጃ ሊደረስ ይችላል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን በማሳያነት የሚጠቅሱ ክፍሎች ተቃዋሚው ጎራና ኢህአዴግ ተያይዘው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲገቡ አሜሪካ አሁን ላይ የደረሰችበት እምነት ነው። ለዚህም ይመስላል ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠችው።
በውይይቱ ወቅት ለአሜሪካው የልዑካን ቡድን ህወሃት/ኢህአዴግ የጉዞ ማዕቀቡ እንዲነሳለት “በወዳጅነታችን ይሁንባችሁ” ዓይነት ውትወታ ማቅረቡን የጠቆሙት ዲፕሎማት ምንጮች “አሜሪካ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ነገር አላማረኝም” በሚል ለጊዜው ውሳኔዋን ለመቀልበስ ቃል እንደማትገባ ማስታወቋን አመልክተዋል።
የጉዞ ማዕቀቡ ነባር ኢንቨስተሮችን ያስበረገገ፣ አዲስ የሚመጡትን የገታ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ “የአገሪቱን ገጽታ ያበላሸ” እንደሆነ ለቶም ማሊኖውስኪ ቡድን ተገልጾለታል። እንደ መረጃ ሰዎቹ አገላለጽ አሁን ከቻይና፣ ከአረብ አገራትና ከአፍሪካ ባለሃብቶች ጋር የኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚደረግ የሚጠቁሙ የዜና ዘገባዎችን ኢህአዴግ በስፋት የሚያሰራጨው ይኽው “ጠፋ” የተባለውን መልካም ገጽታ ለመመለስ ነው፤ የግልገል ጊቤ ሦስት ምረቃና ከዚያ ጋር አብሮ የተነገረው ፕሮፓጋንዳ የዚሁ ዘመቻ አካል አድርገው ይጠቅሱታል። ጥረቱ ቢደረግም የሚፈለገውን ለውጥ ባለማምጣቱ፣ ገንዘባቸውን እየያዙ የሚወጡ ባለሃብቶች በመበራከታቸው፣ አንዱ የምንዛሬ ምንጭ የሆነውን የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (ኤፍ.ዲ.አይ) እየጎዳው በመሆኑ፣ የቱሪዝም ፍሰቱ በመስተጓጎሉ አሜሪካ ማዕቀቡን እንድታነሳ መወትወት ግድ ሆኗል። ምክንያቱም የአሜሪካ የጉዞ ማዕቀብ አሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን አውሮጳና የሩቅ ምስራቅ አገራት በቀጥታ የሚተገብሩትና ለአገራቸው ሕዝብ እንደማስረጃ የሚያቀርቡት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
“ሰዎቹ” ይላሉ የጎልጉል መረጃ አቀባይ አሜሪካኖቹ ማለታቸው ነው “ሰዎቹ ተንኮል ሲያስቡ የት ጋር ሄደው ቆጣሪውን እንደሚነኩት ያውቃሉ” ሲሉ የአሜሪካኖቹን አካሄድ የተጠና እንደሆነ ያስረዳሉ። ቶም ማሊኖውስኪ “(የኢህአዴግ ሰዎች) ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብለን እናምናለን” ማለታቸው፣ “ቁልፍ የፖለቲካ መሪዎችን መፍታትና ሚዲያውን ነጻ መልቀቀ ግድ ነው” ሲሉ በተለመደው “የነጮቹ ቋንቋ” መናገራቸው ቅድመ ሁኔታ ስለመኖሩ አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል። አያየዘውም አሜሪካ አሁን እየተኬደበት ያለው የችግር አፈታት ሂደት “አኩራፊዎችን ከማብዛት የዘለለ ውጤት እያመጣም የሚል አቋም አላት” ሲሉ ቶም ማሊኖውስኪ መናገራቸውን ያስታውሳሉ። እናም ኢህአዴግ ከገባበት ውስጣዊና ውጫዊ አጣብቂኝ ይወጣ ዘንድ የተነገረውን ማድረግ ግድ ነው።
“እንደ ወዳጅ መክረናል … ምክንያቱም … ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ቢፈጠር ሙሉ ምስራቅ አፍሪቃ ምን ሊከተል እንደሚችል ስለምናውቅ … “ በማለት አገሪቱን እሳት ላይ ተቀምጦ እንደሚንተከተክ ማሰሮ የመሰሉትና ማስሮው እንዳይገነፍል ብቸኛው አማራጭ ክዳኑን መክፈት እንደሆነ ያመለክቱት ቶም ማሊኖውስኪ፣ “ተስፋ አለን ይሰሙናል፣ መልካም ነገር እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢኮኖሚው በድርብ አኻዝ እያደገ ነው፤ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል፤ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የምትመች አገር ናት፤ ኤምባሲዎቻችን የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ነው የሚሠሩት፤ ወዘተ በማለት ህወሃት/ኢህአዴግ የውጭ ባለሃብቶችን ለማማለል የተጠቀመበት ሥልት አገሪቱ ውስጥ ከፈነዳው ነውጥ አኳያ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በርካታ የንግድ ተቋማት፣ የእርሻ ቦታዎች፣ … ከወደሙ በኋላ ተመሳሳይ ኢንቨስትመንት ለማድረግ የሚመጡ ባለሃብቶች የመኖራቸው ጉዳይ አስተማማኝ አልሆነም፡፡ በነሐሴ ወር ከገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጠው ዘገባ መሠረት የአገሪቱ ዕዳ 20.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
በአሻባሪነት ስም የሚደረገው ማስፈራሪያ ጊዜው ያለፈበት ይመስላል፡፡ የህወሃትና የአልሸባብ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል አርባ ምንጭ የሰው-አልባ አሮፕላን ማረፊያ (ድሮን ቤዝ) ማቋቋም ደርሳ የነበረችው አሜሪካ ፕሮጀክቷን ያጠናቀቀች ይመስላል፡፡ “ሶማሊያ ውስጥ … በኮንዶም አንዋጋም!” እያለ የሚያምታታ መለስ የሌለው ህወሃት/ኢህአዴግ ቁንጮውን ብቻ ሳይሆን ከበረሃ ጀምሮ ሲያግዙት የነበሩትን “ነጭ ወያኔዎችም” እያጣ ነው፡፡
የቶም ማሊኖውስኪ ንግግር አሜሪካ ለኢህአዴግ ጀርባዋን እየሰጠች ያለ ቢያስመስልም ንግግሩ ከኦባማ ሌጋሲ ጋር እንዲጠቀስ የተነገረም ሊሆን ይችላል፡፡ የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ “ዴሞክራሲያዊ” በማለት በሕዝብ የተሳለቁት ኦባማ በሥልጣን ዘመናቸው አንዳች ሳይፈጽሙ ቆይተው አሁን በስተመጨረሻው ይህንን ብለን ነበር ለማለት ለታሪካቸውና ለአስተዳደራቸው አስበው የፈጸሙትም ይሆናል፡፡ ሆኖም እንደ ማሊኖውስኪ ንግግር ኳሱ ያለው በአሜሪካ ዘንድ ሳይሆን በራሱ በህወሃት/ኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ አሜሪካ ከጸጥታና ደኅንነት በስተቀር ከኢትዮጵያ ጋር ይህ ነው የሚባል የኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት የሌላት ከመሆኑ አንጻር ጀርባዋን መስጠቷ በኢህአዴግ ላይ ጉዳቱን ያከርረዋል፡፡
ከአፍሪካ ጋር የተለካ አዲስ ሽርክና እንጀምራለን የሚል አቋም ለመውሰድ እየተዘጋጀ ያለው መጪው የትራምፕ አስተዳደር ለህወሃት/ኢህአዴግ የሚመች አይሆንም የሚለው ግምት ሰፋ ያለ ነው፡፡ የውትወታ (ሎቢ) ቢሮዎችን እዘጋለሁ እያሉ የሚዝቱት ትራምፕ ካቢኔያቸውን በወትዋቾች ድጋፍ እያቋቋሙ ያሉ ቢሆኑም የተናገሩትን የሚፈጽሙ ከሆነ በውትወታ በርካታ ተግባራትን በመፈጸም ለሚታወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ብዙ በሮችን ሊያዘጋበት ይችላል፡፡ ከኦባማ ሥልጣን መልቀቅ ጋር በርካታ “ነጭ ወያኔዎችን” ለሚያጣው፤ በዚህ ከተቀጠለ “ሥልጣን ማስረከብ ደረጃ ሊደረስ ይችላል” ለተባለለትና በግፍ ያሰራቸውን “የተሃድሶ ሠልጣኞች” እያለ የመፍታት ጭንቀት ውስጥ ለገባው ህወሃት/ኢህአዴግ “መጪው ጊዜ” ከውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጪም “ብሩህ” አይመስልም፡፡ (ፎቶ: በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ)