የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት በአምስት የማቆያ ቦታዎች ለወራት ታስረው የነበሩ አስር ሺህ ገደማ ሰዎች መልቀቁን አሳውቋል፡፡ መንግስት ታሳሪዎቹ በቆይታቸው የተሃድሶ ስልጠና እንደተሰጣቸውና በጥሩ ሁኔታ እንደተያዙ ቢገልጽም ከእስር የወጡት ሰዎች ግን ድብደባ እና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡
ከመዲናይቱ አዲስ አበባ በስተምዕራብ 350 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ የሚገኘው የጦላይ ወታደራዊ ካምፕ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሙ ተደጋግሞ ይነሳ ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸው በመንግስት ከታመነላቸው 20 ሺህ ታሳሪዎች መካከል አምስት ሺህዎቹ በዚህ ካምፕ ለወራት ቆይተዋል፡፡ ሶስት ወጣት እስረኞች በጦላይ ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜ ለዶይቸ ቨለ በሰጡት ቃለ ምልልስ አጋርተዋል፡፡
ወጣቶቹ እስረኞች በጦላይ ስለነበሩ እስረኞች ብዛት፣ አብረዋቸው ስለታሰሩ ሰዎች እና ስለ ዕድሜ ክልላቸው ይተርካሉ፡፡ ጦላይ ሲደርሱ የገጠማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደነበር ምሳሌ እየጠቀሱ ያስረዳሉ፡፡ ምግብ፣ ውሃ እና ህክምና የመሰሉ መሰረታዊ አቅርቦቶች ላይ ስለነበረው እጥረትም የሚናገሩት አለ፡፡
እስረኞቹ በጦላይ የነበራቸው ቆይታ ምርመራንም ያካተተ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በምርመራ ወቅትም ድብደባን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸምባቸው እንደነበር ይከሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በማቆያ ቦታዎች የታሰሩ ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና እንደተሰጣቸው ደጋግሞ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ሶስቱ ወጣቶች በጦላይ ስለነበረው ስልጠና የሚሰማቸውን አካፍለዋል፡፡
በጦላይ የቆዩ አምስት ሺህ ገደማ እስረኞች ከወራት የእስር ቆይታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት መመረቃቸው ተዘግቧል፡፡ በምረቃው ወቀትም የምስክር ወረቀት መቀበላቸው ተገልጿል፡፡ እስረኞቹ ከፍቺ በኋላ ያላቸውን ስሜት አጋርተዋል፡፡ ወጣቶቹ መታሰራቸው በቀጣይ ህይወታቸው ላይ ምን አንደምታ እንዳለው ዘርዝረዋል፡፡
ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
አዜብ ታደሰ