Goolgule.com: በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ አላስተማመነም

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 9 Feb 2016 11:25:18 +0100

የዕርዳታ ሠራተኞች ወደ መስክ እንዳይወጡ ተከለከሉ

security

በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታና ደኅንነት ሁኔታ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አለመሆኑ ተነገረ፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ወደ መስክ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት ተከለከለ፤ የፕሮጀክት ሥራዎች ሊደናቀፉ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ ኢህአዴግ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞችን ወደተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይንቀሳቀሱ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው መሆኑን መረጃው የደረሳቸው ለጎልጉል አስታውቀዋል፡፡

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይ የአማራ ክልልና በምዕራብ ደግሞ የጋምቤላ ክልል አካባቢ ያለው ውጥረት እጅግ እያየለ በመምጣቱ በቦታዎቹ ላይ የሚንቀሳቀሱ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ሊደርስባቸው ስለሚችል ጉዳት ተጠያቂ እንደማይሆን ኢህአዴግ በሰጠው ማሳሰቢያ አስታውቋል፡፡

ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው የዕርዳታ ድርጅቶች መካከል የካቶሊክ ዕርዳታ አገልግሎት አንዱ ሲሆን በውሳኔው ምክንያት ድርጅቱ በተለይ በጋምቤላ የሚያከናውነው ፕሮጀክት ችግር ላይ እንደሚወድቅ ተነግሯል፡፡

ኢህአዴግ ማስጠንቀቂያውን ካስተላለፈ በኋላ በተዋረድ ከአለቆቻቸው ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሠራተኞች ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች እንዳይሄዱ መከልከላቸውን የዜናው አቀባዮች ለጎልጉል አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ እያየለ የመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞና እምቢተኝነት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ለወራት መቀጠሉ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማምጣቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ እና በሌሎች ክፍለኢኮኖሚዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ባለሙያዎች አሳማኝ ግምቶች ይሰጣሉ፡፡

ህወሃት እንደ ጭቃ ጠፍጥፎ የሠራቸው የአማራውና የኦሮሞው ድርጅት አባሎች ለአንድ ብሔር የበላይነት አንገዛም የሚሉ ጥያቄዎች እያነሱ መምጣታቸው በመለስ አዝማችነት ህወሃት ሁሉ ቦታ ከለኮሰው የዘር እሣት ጋር ተዳምሮ የአገሪቱ መጻዒ ዕድል የሚያሳስባቸው ወገኖች ሁኔታው መላ ሊፈለግለት ያሻዋል ይላሉ፡፡

Received on Tue Feb 09 2016 - 05:25:19 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved