Tgindex.BlogSpot.de: ከኦሮሞ ማዕበል ማግስት …

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 23 Feb 2016 16:10:56 +0100

ተስፋይ ገብረኣብ

Friday, February 19, 2016

        በአለማችን ላይ ወጣቶች በአንድ ልብ የተሳተፉበት ያልተሳካ የአብዮት ታሪክ አናውቅም። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። ይህችን እየፃፍኩ ሳለ የማያቋርጥ፣ የተቀናጀ የአመፅ ዜና ከኢትዮ - ኦሮሚያ እየሰማሁ ነበር። ዝምታው ማብቃቱ ግልፅ ነበር። የኦሮሚያ ወጣቶች የስርአቱን ታጣቂ ሃይል በጦርና በጠመንጃ ይፋለሙት ይዘዋል። ከሻሸመኔ ወደ አዲስአበባ መንገድ ተዘግቶአል። ልማደኛዋ ኮፈሌ ጦርሜዳ ሆናለች። ብረት ለበስ ጦር ኮፈሌና ሻሸመኔ ገብቷል። በጥቅሉ ወለጋና ሃረርጌ ፀጥታ የለም። ሱሉልታ ብሶበታል። ጭራሽ ገበሬዎቹ ያስለቀቁትን መሬት መከፋፈል ጀምረዋል። ደራ ነፃ ነው።
 
  አጄ ሃራ ነው። ጅማ መስመር አምቦና ጉደር መንገዱ ዝግ ነው። ሮቤ፣ ጉጂ፣ ቡሌሆራ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጋሼራ፣ አሊ፣ ጃርጋዳ፣ እነዚህ ሁሉ ነፃ የወጡ መንደሮች ናቸው። ወያኔ ወደ ኦሮሚያ ገጠሮች መንገድ አለመዘርጋቱ አሁን ጠቀመ። የፌደራል ፖሊስ መኪናውን ገትሮ በእግር ሲንቀሳቀስ ለኢላማ ተጋለጠ። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጦር ሲተከሉ ብቻ የሚታዩ ጦሮች የፌደራል ፖሊስን ሲጥሉ ታዩ። አሜሪካና ኖርዌይ ዜጎቻቸው በደቡብና በኦሮሚያ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥለዋል። የቱ ተነስቶ የቱ ይተዋል? መንገድ መዝጋት የመሳሰለው የአመፅ ድርጊት ስለተለመደ ዜና መሆኑ ቀርቶአል። አመፁ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው። እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።  
 
ርግጥ ነው፤ ሊነጋ ሲል ሁሉም ያውቃል። አርጅቶ ይወድቃል - ስርአትም እንደ ዛፍ። የመኖር ግዳጁን ይፈፅማል። እንደምንታዘበው ከሆነ ሁለት አይነት የህወሃት አባላት አሉ። የአዲሳባ እና የመቐለ ተብለው ይለያሉ። የመቐለ የህወሃት አባላት ግራ ተጋብተው ዝምብለው በመገረም ይመለከታሉ። ለራሳቸው ምንም የላቸውም። እንደ ግለሰብ የተረፋቸው ሃሜት እና ጥላቻ ብቻ ነው። ባልዋሉበት መታማት ለቁጭቶች ሁሉ ቁጭት ይዳርጋል። የአዲሳባዎቹ ወያኔዎች ከመሬት ሽያጭ በሚገኝ ገንዘብ ሰክረው የሚያደርጉትን አያውቁም። አንዳንዶቹ ከመኪና ማቆሚያቸው ምድር ቤት፤ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው መኝታ ቤታቸው ለመሄድ አሳንሰር ይጠቀማሉ። ዳሩ እንደነበሩ መቆየት የለም። ጊዜው ሲደርስ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል። እና “የመኖር ግዳጁን ወያኔ ፈፀመ?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። በርግጥ፤ እየተንገዳገደም ቢሆን ጥቂት ይጓዝ ይሆናል። ነዳጅ አልቆበት ሳለ በቁልቁለት መንገድ ላይ እንደሚጓዝ መኪና ቁጠሩት።
 
የኦሮሞን ህዝብ አመፅ ማፈን እንደማይቻል ካመንን፤ ወያኔም የመኖር ግዳጁን እንደፈፀመ ከገመገምን ስለ መጪው ዘመን በግልፅ መነጋገር ይገባል። ምክንያቱም የወያኔ መውደቅ ብቻውን ድል አይደለም። የነበረውን ስታነሳ፤ በቦታው ምን ለመተካት አቅደሃል? ወያኔን ከማስወገዱ ባላነሰ ሁኔታ ከባዱ ፈተና መጪውን ዘመን የተሻለ ማድረግ ስለመቻሉ ሆኖ ቆይቶአል። የሚፃፉ ፅሁፎችን ስንታዘብ በጥቅሉ በአማራ እና በኦሮሞ ልሂቃን መካከል ከወዲሁ ሽኩቻ የተጀመረ ይመስላል። ይህ ሽኩቻ ለጊዜው የተሟላ እልባት ማግኘት ባይችል እንኳ፤ የማቀራረቢያ የጋራ ጥርጊያ ካልተበጀለት ወያኔ ቀዳዳዋን በመጠቀም በስልጣን ለመቆየት አንድ የመጨረሻ እድሉን ሊሞክር ይችላል።   
 
ግርማ ካሳ የተባለ ፀሃፊ በቅርቡ “ዘሃበሻ” ድረገፅ ላይ የፃፈው ፅሁፍ ትኩረቴን ለመሳብ በቅቶ ነበር። ፀሃፊው በመጣጥፉ ኦሮሞነት የሚለካበት መንገድ ምን እንደሆነ ይጠይቃል። አብነት ለመስጠትም ስለ ራሱ የዘር ሃረግ እንዲህ ሲል በዝርዝር ገለፀ፣
 
“… እኔ አንድ አያቴ ከቦረና (ኦሮሞ)፣ ሁለተኛ አያቴ ከወለንጭቲ (ኦሮሞ) ነበሩ። ሶስተኛ አያቴ አባታቸው ከሸንኮራ (ሸዋ) የነበሩ ሲሆን፣ እናታቸው ደግሞ የጂማ ኦሮሞ ነበሩ። አራተኛው አያቴ ከጎጃም ናቸው። እንደሚታወቀው ጎጃም አማርኛ ይናገር እንጂ ከኦሮሞ ጋር የተደባለቀ ነው። ወለጋ እንደማለት ነው። እኔ ቢያንስ 5/8ኛ ኦሮሞ ነኝ። ኦሮሞነት በቋንቋ ከሆነ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ አይደለሁም። አፋን ኦሮሞ አለመናገሬ ደግሞ ፈልጌ ያመጣሁት አይደለም። ኦሮሞነት ኦሮሚያ በመወለድ ከሆነ ከኦሮሚያ እምብርት ፊንፊኔ በመወለዴ ኦሮሞ ነኝ…”
 
ግርማ ካሳ 5/8ኛው ኦሮሞ መሆኑን አስረድቶን ሲያበቃ በኢትዮጵያዊነት መጠራት እንደሚፈልግ ገልፆአል። እንደሚመስለኝ ችግር እየተከሰተ ያለው እንደ ግርማ ካሳ ያሉ ወገኖች አርባ ሚሊዮን የሚሆነውን የኦሮሞ ህዝብ “እንደኛ ካላሰብክ፣ እንደኛ ካላመንክ፣ እንደኛ ካልለበስክ!” ሲሉ ደጋግመው መዛታቸው ነው። ዛቻቸውን አሰልቺ የሚያደርገው ደግሞ የማስገደድ አቅማቸው ተረት ሆኖ መቅረቱን አለማወቃቸው ነው። ግልፅ ለማድረግ ያህል ግን “ኦሮሞ ማነው?” ለሚለው ጥያቄ ያነበብኳቸውን የኦነግና የሌሎች ኦሮሞ ነክ ድርጅቶች ሰነዶችን በማጣቀስ በቀላሉ ምላሽ ለመስጠት ልሞክር፣
 
1ኛ) - በእናቱም በአባቱም ከኦሮሞዎች የተወለደ ኦሮሞ ነው። ለአብነት ጢኖ ባሮ፣ ትዝታ በላቸው፣ ቶሌራ አዳባ፣ ህዝቅኤል ጋቢሳ፣ አባጫላ ለታ፣ ሃሰን ሁሴን፣ ሩንዳሳ አሼቴ፣ ወርቅነሽ ቡልቶ፣ በያን አሶባ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ የሺ ቶሎሳ፣ ሌንጮ ባቲ፣ ትእግስት ገሜ፣ ጃዋር መሃመድ፣ ዋሚ ቢራቱ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳ፣  ጃምቦ ጆቴ፣ ገላና ጋሮምሳ፣ ሴና ሰለሞን፣ ጃፈር ዩሱፍ፣ ጄኔራል አለምሸት ደግፌ፣ ሃዊ ተዘራ፣ በቀለ ገርባ፣ ሲፈን ጫላ፣ እያልን ስንቀጥል ከአርባ ሚሊዮን በላይ መመዝገብ ይቻላል።  
 
2ኛ) - በእናቱ ወይም በአባቱ በግማሽ ወይም በእሩብ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ ኦሮሞ ነው። ወይም ‘ኦሮሞ ነኝ’ የማለት መብት አለው። ለአብነት አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ነአምን ዘለቀ፣ ሃይሉ ሻውል፣ ያሬድ ጥበቡ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ነገደ ጎበዜ፣ ጄኔራል ሰአረ መኮንን፣ ዶክተር ትእግስት መንግስቱ ሃይለማርያም፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ግርማ ሰይፉ፣ ቴዲ አፍሮ፣ በዕውቀቱ ስዩም … እነዚህን የመሰሉ በከፊል ኦሮሞዎች ፍላጎታቸው እስከሆነ ድረስ  ኮርተው ኦሮሞ ናቸው።
 
3ኛ) - የኦሮሞ ህዝብ በባህላዊ መንገድ ኦሮሞነትን በአክብሮት የሰጣቸው ግለሰቦች ሁሉ ኦሮሞ ናቸው። ለአብነት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ (ሃዩ)፣ ዶክተር ቦኒ ሆሎኮም (ቃበኔ)፣ ተስፋዬ ገብረአብ (ጋዳ)፣ ዶክተር ትሩማን እና ሌሎችም ሊጠቀሱ ይችላሉ።
 
ከዚህ ውጭ ኦሮሚያ ላይ ስለተወለደ ወይም ኦሮምኛ ቋንቋ አቀላጥፎ ስለቻለ አንድ ግለሰብ ኦሮሞ ሊባል አይችልም። እንደተረዳሁት ከሆነ ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች የOPDOን ባላውቅም ሌሎች ኦሮሞ ነክ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ይስማማሉ። አንድ ግለሰብ “ኦሮሞ ነኝ” ለማለት ከእነዚህ ሶስቱ መንገዶች በቀር ሌላ ቀዳዳ፣ ሌላ መስኮት፣ ሌላ በር፣ ሌላ የዘመድ-በር ወይም ሌላ የዘመድ-መስኮት ያለ አይመስለኝም። ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መመዘኛዎች “የኦሮሚያ ዜጋ” መሆን ግን ይችላሉ። በኦሮሚያ ክልል መሬት ላይ የተወለደ ሁሉ በቀጥታ ኦሮሞ መሆን ባይችልም የኦሮሚያ ዜጋ መሆን ይችላል። ማለትም በኦሮሚያዊ ዜግነት ሲኖር በእናት ቋንቋው የመጠቀም፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ ሃብት የማፍራት መብቱ ያለገደብ ይከበርለታል። እድሉን ካገኘ ደግሞ በሞጋሳ ባህል ኦሮሞ መሆን ይችላል። ከዚህ ባሻገር ከኦሮሚያ ጋር ኩታገጠም የሆኑ አናሳ ብሄረሰቦች ባህላቸውና ቋንቋቸው ተከብሮላቸው የኦሮሚያ አካል መሆን ይችላሉ። በኦሮሚያ ሳይወለዱ የኦሮሚያ ነዋሪ የሆኑ ወይም የተጋቡ ደግሞ በጥያቄያቸው መሰረት የኦሮሚያዊ ዜግነት ሊሰጣቸው ይችላል።
 
ይህ ሊሆን የሚችለው እንግዲህ ኦሮሚያ ነፃነቷን አውጃ ሉአላዊት አገር ከሆነች ነው። ፊንፊኔን ይዛ ኦሮሚያ ነፃነቷን ካወጀች እሱን ተከትሎ ደቡብ ህዝቦችና ኦጋዴንያ ከኦሮሚያ ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስምምነት ሊመጣ ይችላል። እስካሁንም እንዲህ ያለ ርእሰ ጉዳይ አልተነሳም ማለት አይቻልም። 2014 ላይ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ OSA ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቶ ያደረገው ንግግር አግጣጫ ጠቋሚ ነበር። የኦሮሞ ህዝብ ከደቡብ ህዝቦች ጋር የተጋራውን ታሪክና ባህል አንስቶ የተቀናጀ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቦ ነበር። የቤኒሻንጉልና የጋምቤላ ንቅናቄዎች ከኦሮሞ ግንባሮች ጋር ያላቸው ረጅምና ታሪካዊ ትብብርም ስትራቴጂያዊ ነው። ወያኔ ራሱ እንደሚያስወራው ከበጌምድር፣ ከአፋርና ከወሎ ሰፋፊ ውሃገብ መሬቶችን ወስዶ “ሰሜን ኢትዮጵያ” የተባለች አዲስ አገር ለመመስረት ቢንቀሳቀስ (አውራምባ ታይምስ - ቃለመጠይቅ ከአብርሃም ያየህ ጋር)  ኦሮሞ የኢትዮጵያን ግዛት ለማስከበር ወደ አክሱም ይዘምታል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ፅሁፍ ቅዠት መስሎ የሚሰማው ወገን ሊኖር እንደሚችል አውቃለሁ። ቅዠት መስለው ይታዩ የነበሩ በርካታ አጀንዳዎች ሲፈፀሙ ግን አይተናል። በኛው ዘመን፤ በኛው እድሜ አይተናል። 
 
እንግዲህ እዚህ ደረጃ ላይ ገና አልተደረሰም። ከወያኔ የመኖር ግዳጅ ማብቃት በሁዋላ ጉዞው ወደዚያ አግጣጫ መሆኑን ለማሽተት ግን ፖለቲከኛ መሆን አይጠይቅም። ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ሁሉም ዜጋ በአንድ ብሄራዊ ማንነት ሊታወቅ የሚችልባት አንዲት ታላቅ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚቻልበት እድል የተዘጋ አይመስለኝም። በቅድሚያ ግን አደጋ ላይ የወደቀውን የኢትዮጵያ አንድነት እንደነበረ ለማቆየት የኦሮሞ ህዝብ ሚና ወሳኝ መሆኑን ማመን ይገባል። ወሳኝ ስል የአንበሳ ድርሻ ማለቴ ነው።
 
በትክክል የኦሮሞ ህዝብ ከፊቱ ሁለት ምርጫዎች አሉት። እነርሱም “የኦሮሚያን ነፃ ሪፖብሊክ ማወጅ” ወይም “በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ስር የኦሮሚያን ክልል መቀበል” ናቸው። የኦሮሞ ህዝብ ከሁለት አንዱን የመምረጥ ብቃቱን እያረጋገጠ በመሄድ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ሁለት ምርጫዎች ባሻገር ሌላ አማራጭ የለም። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በግልፅ እንዳስቀመጠው “ሌላ አማራጭ አለ” ከተባለ ጦርነት ነው። ጦርነት ከተነሳ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም። የጦርነት አማራጭ ለሁሉም ወገን አደገኛ ነው። ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ጭምር በጣም አደገኛ ነው። እና ጦርነቱን አለማሰብ ይበጃል።
 
የኦሮሞ ህዝብ የሚፈልገውን እንዲመርጥ እድል መስጠት ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል። ለስኮትላንድ ህዝብ የተሰጠው የመምረጥ መብት ለኦሮሞ ህዝብ የማይሰጥበት ምክንያት ምንድነው? በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ማሳመን መቻል አስተማማኝ ሰላም ያስገኛል። “ማነው ኦሮሞ?” በሚለው ጥያቄ ውስጥ “እኔ ኦሮሞ ነኝ” የማለት መብት ያላቸው ወገኖች ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች ያላቸውን በጎ ራእይ ቀረብ ብለው መግለፅ ይችላሉ። መሳይ ከበደ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ በመቀራረብ መፍታት እንደሚቻል ማመኑ፣ እምነቱንም በግልፅ በመፃፉ ምን ያህል ኦሮሞ ደጋፊዎችን እንዳፈራ በቅርቡ ያየነው ነው። መቀራረብ ይቻላል። በአንድነት መኖር ይቻላል። ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል። መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይቻላል።

የኦሮሞ ህዝብ ወደ ሪፈረንደም ከመግባቱ በፊት በመካከሉ ረጅም የሽግግር ጊዜ ሊኖር እንደሚችል ግልፅ ነው። በዚህ የሽግግር ጊዜ እውነተኛው ዴሞክራሲ ከታየ ውጤቱ ተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል። የኦሮሞ ህዝብ የራሱን አገር ያውጃል ብሎ ከመስጋት ይልቅ፤ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ሊቀላቀሉ የሚሹ የአካባቢ አገራት ፍላጎት በርትቶ ሊታይ ይችላል ብሎ ማሰብ የሚቀል ይመስለኛል። ምክንያቱም ፍትህ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት የሰፈነበት ትልቅ ህብረት ውስጥ አካል መሆን የማይመኝ የለም።
Received on Tue Feb 23 2016 - 10:10:57 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved