Esat.com: የአቶ ሃይለማርያም ዛቻም ሆነ የሃይማኖት አባቶች ተማጽኖ በኦሮምያ የሚካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ አላስቆመውም

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 25 Feb 2016 14:03:22 +0100

February 25, 2016

የካቲት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአጋዚ ወታደሮች ለተቃውሞ በሚወጡት ወጣቶች ላይ በቀጥታ እንዲተኩሱ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል፣አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም መንግስታቸው የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ በአደባባይ ዝተዋል። የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚወክሉ የሃይማኖት አባቶች፣ በመንግስትና በህዝቡ መካከል መነጋጋር እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ሁሉ ዛቻና ምክር እየተሰጠ ቢሆንም፣ የክልሉ ወጣቶች የሚያቆመን የለም በማለት ዛሬም ትግላቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የቦረና እና የጉጂ ዞኖች የዛሬው ተቃውሞ ማእከል ሆነዋል። በቡሌ ሆራ ከተማ ተማሪዎች ምሽት ላይ በሶስት ኦራል መኪኖች ተጭነው ከመጡ የአጋዚ ወታደሮች ጋር ተፋጠው አርፍደዋል።ወታደሮቹ ተማሪዎች ከግቢያቸው እንዳይወጡ ሲያስጠነቅቁ ቢያረፍዱም ተማሪዎች ግን ማን ነው የሚያቆመን በማለት ትእዛዙን ጥሰው ወደ አደባባይ ወጥተዋል። የአጋዚ ወታደሮችም መትረጊስ ሳይቀር በመተኮስ የተማሪዎችን ሰልፍ ለመበትን ሙከራ አድርገዋል። ተቃውሞው ከሰአት በሁዋላም ቀጠለ ሲሆን ፣ በርካታ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በያቤሎ ከተማም እንዲሁ ከጧቱ ሁለት ሰአት እስከ ቀኑ ስድስት ሰአት ድረስ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። በዚህ ተቃውሞ የአጋዚ ወታደሮች ምንም እርምጃ አለመውሰዳቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል።

በጉጂ ዞን ቀርጫ ከተማ ደግሞ ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ያሉ ተማሪዎች ትናንት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በዚሁ ዞን መልካ ሰዳ ወረዳ ሃሎ ከተማ የከተማው ህዝብ ነቅሎ በመውጣት የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል።

በምእራብ ሃረርጌ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በምእራብ ወለጋ ሃይራ ከተማ ዛሬ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ አርፍዷል። የአጋዚ ወታደሮች በሚወስዱት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እስካሁን ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል። እንደ የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ ሊግ መግለጫ ደግሞ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺ ያልፋል።

በደቡብ ክልል በሚካሄደው የኩራዝ ልማት ድርጅት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ፣ በአካባቢው የሚታየው ግድያ እየጨመረ በመምጣቱ ስራቸውን አቋርጠው ወደተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱ ነው። ሰራተኞች እንዳሉት በኦሮምያ የተነሳው ተቃውሞ እንደገና ካገረሸ በሁዋላ፣ የድርጅቱ በርካታ ትራክተሮች ተቃጥለዋል። ጥቃቱን የሚያደርሱት እነማን እንደሆኑ ግን የታወቀ ነገር የለም።

በሌላ በኩል የዶ/ር መረራ ፓርቲ በሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ አመራር አባላት ላይ በደህንነት ሀይሎች የሚደረገው ክትትልና ማዋከብ ተጠናክሮ ቀጥሎአል።

መንግስት ኦፌኮ በውጭ ሀገር ከሚንቀሳቀሱ ሀይላት ጋር ግንባር በመፍጠር በኦሮሚያ ትርምስ እንዲፈጠር አድርጎአል በሚል በግልጽ ክስ ሲያቀርብበት የቆየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከጥርጣሬ ባለፈ እርምጃ ወደመውሰድ እየተሸጋገረ ነው።

የመድረክ አባል የሆነው ኦፌኮ በአዲስአበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከመድረክ ጋር ቢንቀሳቀስም ተከልክሎአል። የተከለከለበት ዋንኛ ምክንያትም የኦሮሚያን ችግር ወደአዲስአበባ ለማሸጋገር እየሰራችሁ መሆኑን ደርሰንበታል በሚል ነው። የፖርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ነገአ በደህንነት ሀይሎች የቁም እስር ውስጥ ከገቡ አንድ ወር ያለፋቸው ሲሆን፣ የሌሎቹንም አመራሮች እንቅስቃሴ በደህንነት ሀይሎች ቁጥጥር ስር ወድቆአል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በሰጡት አስተያየት እነዶ/ር መረራ በቅርቡ የመታሰራቸው ጉዳይ የማይቀር ነው። ኢህአዴግ የኦሮሚያን ችግር ኦፌኮ እጁ እንደሌለበት አሳምሮ ያውቃል ያሉት ምንጮች፣ ጠ/ ሚኒስትሩ እርምጃ እንወስዳለን ባሉት መሰረት ኦፌኮን ጭዳ በማድረግ የተቃውሞውን እንቅስቃሴ ህዝባዊ መሰረት ለማሳጣት መሞከራቸው የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል።

የደህንነት ወከባ በመጠንከሩ ምክንያት የፖርቲው አባላት ከጽ/ ቤቱ የራቁበት ሁኔታ መፈጠሩም ታውቆአል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በህዝባዊ አመጹ ጀርባ ሻእቢያና የውጭ ሃይሎች አሉበት ያሉ ሲሆን፣ መንግስታቸው የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ መዛታቸውም ይታወቃል።

የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ባልተለመዱ መልኩ ወደ አደባባይ በመውጣት የሰላም መፍትሄ እንዲፈለግ ተማጽነዋል። የሃይማኖት አባቶቹ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከማውገዝ ቢቆጠቡም፣ ግድያው ቆሞ የሽምግልና ጥረት ይጀመር ብለዋል። የአለማቀፍ መንግስታት እስካሁን በህወሃት /ኢህአዴግ መንግስት ላይ እርምጃ አልወሰዱም። የአውሮፓ ህብረት የፓርላም አባላት ጠንካራ ውሳኔ ቢያስተላልፉም እስካሁን በተጨባጭ የወሰዱት እርምጃ ስለመኖርና አለመኖሩ የገለጹት ነገር የለም። የገዢው ፓርቲ ዋነኛ ደጋፊ ተደርጎ የሚታየው የአሜሪካ መንግስት ” ጉዳዩ አሳስቦኛል” የሚል መግለጫ ከማውጣት ውጭ፣ መንግስትን ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የሚያድርግ እርምጃ አልወሰደም።

Received on Thu Feb 25 2016 - 08:03:22 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved