Ethsat.com: አባይ ጸሃዬ ከኤርትራ ጋር ወደጦርነት አንገባም አሉ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 23 Jul 2016 12:45:47 +0200

ኢሳት (ሃምሌ 15 ፥ 2008)

July 23, 2016

ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ እንግባ እያሉ የሚገፋፉን ጦርነቱ ውስጥ የማይገቡ፣ ሌላው እንዲሞት የሚፈልጉ ወገኖች ናቸው ሲሉ አቶ አባይ ጸሃዬ ገልጹ።

የህወሃት መስራችና አሁንም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አባይ ጸሃዬ የህወሃት ደጋፊ ከሆነው አይጋፎረም ጋር ሰሞኑን ባደረጉት በዚህ ቃለምልልስ ሻዕቢያም ሆነ በርሱ የሚደገፉ ሃይሎች ሲተነኩሱን አጸፋ ምላሽ እንሰጣለን፣ ከዚያ በላይ ግን ልማታችንን የሚያደናቅፍ ጦርነት ውስጥ አንገባም, ህዝብም ልጆቻችንን አንገብርም በማለት ይቃወመናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ወደ ጦርነት እንግባ የሚለን ጦርነት ቢከሰት ጦርነቱ የማይመለከታቸው ወይንም የማይሳተፉ ናቸው ሲሉም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በቅርቡ ሰኔ 5 ፥ 2008 በጾረና ግንባር ከኤርትራ ጋር የአንድ ቀን ውጊያ ከተደረገ በኋላ በመንግስት ባለስልጣናትና በመንግስት ደጋፊዎች መካከል የአቋም መለሳለስ በመታየት ላይ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ በህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች እንዲሁም ባለስልጣናት የሚሰጡ መግለጫዎች ሻዕቢያ በራሱ ጊዜ ይወድቃል ጦርነት ውስጥ አንገባም የሚል መሆኑን መረዳት ተችሏል።

የኤርትራ መንግስት ቢወገድ የማናውቀውን መጨረሻ ያስከትላል በማለትም፣ ጦርነት ውስጥ  የማይገባበትን ምክንያት በማስረዳት ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ተችሏል።

በፆረና ግንባር ሰኔ 5 ቀን ለአንድ ቀን በተካሄደው ውጊያ መንግስት ጉዳት እንደደረሰበት በይፋ ማመኑ ሲታወስ፣ የኤርትራ መንግስትም 200 ወታደሮች ገደልኩ ማለቱ አይዘነጋም። በህዝቡ በኩል በማህበራዊ መድረክና በሚዲያዎች ለጦርነቱ የተሰጠው ምላሽ የመንግስት ባለስልጣናትን ያስደሰተ ሆኖ አልተገኘም።

Received on Sat Jul 23 2016 - 05:24:51 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved