ሐምሌ ፳፰ ( ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በባህርዳር ሲካሄድ በሰነበተው የዲያስፖራ በአል ላይ የተገኙት ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያ ከባድ የህልውና አደጋ እንደተደቀነባት ተናግረዋል።
የጠባብነትና የትምክህትነት አደጋ ከፊታችን እንዳለ ዛሬ ሳይሆን አስቀድመን አውቀናል ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ ይህ ደግሞ አገራችንን ወደ ማትመለስበት የብሄር ግጭት አደጋና የእርስ በርስ ጦርነት ይከታታል ሲሉ ገልጸዋል። ሁላችንም ይህን ጠባብነትና ትምክት ተረባርበን ካላስቆምነው እስከዛሬ የተጓዝንበትን ሁሉ የሚያበለሽ አደገኛ የሆነ ክስተት መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ሃይለማርያም በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የሚካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የመንግስትን ህልውና እየተፈታተኑ መምጣቱን በይፋ ያመኑ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ባለስልጣን አድርጎአቸዋል። ህወሃት/ ኢህአዴግ በአሮምያ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ በጠባብነት ሲፈርጅ በአማራ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ደግሞ በትምክት የፈርጀዋል። አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጥር የሚወክሉት ሁለቱ ብሄሮች ተቃውሞአቸውን በጋራ እያሰሙ ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊጥሉት ነው ብሎ መናገር መሬት ላይ እየሆነ ያለውን ካለመረዳት ወይም የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቃለሁ በሚል ስም ጭፍጨፋ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን የሚያመለክት ነው ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚካሄደው ተቃውሞ በአርባምንጭና አጎራባች ወረዳዎችም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።