Ethsat.com: የህወሃት/ኢህአዴግ የስልጣን መሰረት ተናግቷል ተባለ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 11 Aug 2016 00:00:24 +0200
የህወሃት/ኢህአዴግ የስልጣን መሰረት ተናግቷል ተባለ

August 10, 2016

ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት መንበረ-ስልጣኑን ላይ ከተቆናጠጠ ከ25 ዓመት ወዲህ በቅርቡ ያጋጠመውን አይነት ህዝባዊ ተቃውሞ አጋጥሞት እንደማያውቅና፣ ይህ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተገለጸ።

የወቅቱን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ አስመልክቶ የምስራቅ አፍሪካ ተማራማሪ የሆኑት ሬኔ ላፎትን ለዣጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወጀብ ውስጥ የምትጓዝ አውሮፕላን ትመስላለች” ሲሉ ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ቀውስ ደረጃን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአፈና ድርጊቱን አጠናክሮ ቢቀጥልም፣ በአማራና ኦሮሚያ ተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ግን የበለጠ እያንሰራራና እየተጠናከረ እንደሆነ የገለጹት ላፎርት “የተፈጠረው ቀውስ ከ25 አመት በፊት የነገሰውን የኢትዮጵያ መንግስት መሰረቱን አናግቶታል” ሲሉ ሚስተር ላፎርት አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎት የተለያየ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ሬኔ ላፎርት፣ ህዝቡ አሁን በስልጣን ላይ ላሉት የኢትዮጵያ መሪዎች ያላቸው ተቃውሞ ለህዝባዊ እምቢተኝነትና ለህዝቦች ትብብር መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል ብለዋል።

አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ትውልዳቸው ከወላይታ ብሄረሰብ ቢሆንም፣ የወታደራዊና ጸጥታ ሃይሉን እንዲሁም ኢኮኖሚውን በሚቆጣጠሩ ከትግራይ በመጡ ሰዎች እንደተከበቡ የገለጸው አዣጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሃይለማሪያም ደሳለኝን ውሳኔ ሰጪነት አቅም በጥርጣሬ አይቶታል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያን ያናገረው ይኸው የዜና አውታር፣ በአናሳ ጎሳ የሚመራ የኢትዮጵያ መንግስት በብዙሃን ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረ እንደሆነ መናገራቸውን አስፍሯል። “መንግስት ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር ምንም አይነት መሰረታዊ ንግግር አላደረገም ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ የህዝቡ ንዴት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ወደኋላ መመለስም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል” ሲሉ አዣጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለዘጠኝ ወራት ህዝባዊ ተቃውሞውን ሲያካሄዱ እንደቆዩ የተናገሩት ዶ/ር መረራ በበኩላቸው፣ ህዝባዊ ተቃውሞው እንደማይበርድ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል። “የተያያዝነው ህዝባዊ አመጽ ነው” ማለታቸውም ታውቋል።

ህዝባዊ ተቃውሞውን አስመልክቶ የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማት አስተያየት ያሰፈረው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ “የኢትዮጵያ መሪዎች የመለስ ራዕይ ጠፍቶባቸዋል፣ የመደነባበር ባህሪይ ይታይባቸዋል” ማለታቸውን አስፍሯል። ስማቸው ያልተገለጸው እኚሁ ዲፕሎማት፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ መሪዎቹ በህዝቦቻቸው ላይ ምንም አይነት እምነት አይጣልባቸውም ሲሉም ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።

Received on Wed Aug 10 2016 - 16:39:30 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved