(ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት አመራሮች እና ካድሬዎች በመቀሌ ምስጢራዊ ስብሰባ አድርገው ሳይስማሙ መለያየታቸው ተሰማ:: በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ሕዝባዊ ማዕበል ሊያጠፋን ይችላል በሚል ስብሰባ የተቀመጡት የሕወሓት አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትርነት አስቀምጠው የሚዘውሩት ኃይለማርያም ደሳለኝን “ጠቅላይ ሚኒስትርም አይመስልም; ብዙም ተደማጭነት የለውም” በሚል ክርክር አንስተው ተወያይተውበታል::
የጭንቅ ቀን ሲመጣ ሕወሓት እንዲህ ያለውን ምስጢራዊ ስብሰባ ማድረጉ የተለመደ ነው የሚሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ከዚህ ቀደም መለስ ዜናዊ መሞቱ ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ በኋላ ሌሎች የኢሕ አዴግ አባል ድርጅቶችን ሳያካትቱ “ሕወሓትና ስልጣን ከመለስ በኋላ” የሚል ምስጢራዊ ስብሰባ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አሁንም በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሳው የሕዝብ አመጽ ስልጣናችንን ሊያሳጣን ይችላል በሚል ሙሉቀን የፈጀ ስብሰባ ለሁለት ቀናት ማድረጋቸውን ገልጸውልናል::
እንደምንጮቻችን ገለጻ “ኃይለማርያም ደሳለኝ በሕዝብ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቆጠር አይደለም; ለሕወሓትም ቆራጥነት የለውም:: በቴሌቭዥን እንኳ ወጥቶ ሕዝብ ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይወጣ ቢያስጠነቅቅም የሚሰማው የለም:: ” የሚሉ አስተያየቶች ከሕወሓት አባላት ተነስቶ ነበር:: አንዳንድ አባላት እንደውም ኃይለማርያምን አንስቶ ሌላ የሕወሓት ሰው በማስቀመጥ ስልጣናችንን ማስቀጠል አለብን የሚል ጥያቄ አንስተው ብዙ ተወያይተውበታል:: “ኃይለማርያም ለሕወሓት ታማኝ ቢሆንም የአመራር ብቃቱ አናሳ ነውና ከስልጣኑ ማንሳት የለብንም:: ከሕወሓት የሚሰጠውን ትዕዛዝ በተለይ የኦህዴድና ብአዴኖች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው በተረጋገጠ መልኩ ይቀጥል” የሚሉ የሕወሓት አባላትም ነበሩ:: “በዚህ ወቅት ኃይለማርያምን አንስቶ የሕወሓት ሰውን ማስቀመጡ ከብዙ አቅጣጫዎች ለሕወሓት ጉዳት አለው” የሚሉም ነበሩ ያሉት ምንጮቻችን በዚህ ጉዳይ ሳይግባቡ መለያየታቸውን እና እንዴት ብአዴንን ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ከሌሎች የተቃዋሚ ኃይሎች መለየት ይቻላል በሚለው ላይ እንስራ በሚለው ላይ እናተኩር በሚለው ላይ እንሥራ በሚለው እንደተስማሙ ገልጸውልናል::
በአሁኑ ወቅት ለሕወሓት ስጋት ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይሆን ብአዴን ነው የሚሉ አመራሮች እንደነበሩ የገለጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ብ አዴንን አከርካሪውን መትቶ ከላይ እስከታች ያለውን አመራር መፐወዝና ታዛዥነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል በሚለው ላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተስማምተዋል ብለዋል::