August 12, 2016
ዜናው ተመልከቱት፡
http://video.ethsat.com/?p=27078
ESAT Meade esat Aug. 12, 2016 Ethiopia
http://video.ethsat.com/?p=27072
ነሃሴ ፮ ( ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተቃውሞ እየተናጡ ባሉት የአማራ እና የኦሮምያ ክልሎች ዙሪያ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የክልል ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም የፌደራል ባለስልጣናት የቪዲዩ ኮንፈረንስ እያደረጉ ነው፤ ስብሰባው መፍትሄ ማመንጨት አልቻለም።
በቪዲዩ ኮንፈረንሱ ላይ የአማራ ፤ ኦሮምያ እና ትግራይ አመራሮች ፤ ቀን ላይ ካቢኒያቸውን ሰብስበው ሲጨርሱ ምሽት ከጠቅላይ ሚንስትሩ እና አማካሪዎቻቸው ጋር በቪዲዩ ኮንፈረንስ እየተነጋገሩ ነው።
“በኢህአዴግ ዘመን ታሪክ ውስጥ ከምርጫ 97 በኃላ እጅግ አሰጨናቂው ምዕራፍ በተባለበት በዚህ ወቅት፣ የአመራረሩ ሞገስ መገፈፉን” ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው ምንጫችን ይገልጻል።
ለውሳኔ ያስቸገረው የሙስሊሞች የድምፃችን ይሰማ ጥያቄ ፤ የኦሮምያ ማስተር ፕላን፤ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ፤ ከህውሃት ጋር የተፈጠረው ግብግብ በተለይም በትግራይ እና አማራ ክልል አመራሮች መካከል የለየለት መካረር ውስጥ መግባት አጀንዳ ሁኖ እየቀረበ ውይይት እየተካሄደበት ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ የአማራ እና የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ያስተላለፉትን እርምጃ የመውሰድ ውሳኔ ህዝቡ ከምንም ባለመቁጠር ወደ አደባባይ መውጣቱን ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ የሁለቱ ክልል ባለስልጣናት ጸጸት ውስጥ ሲገቡ ፣ ህውሃት ደግሞ በእርምጃው መኩራቱን ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ‹‹ የተቃውሞ አቅጣጫዎች መባባስ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ህልውናችን አደጋ ውስጥ ነው “ ሲሉ መናገራቸው፣ የኢህአዴግ የ50 ዓመታት ኢትዮጵያን የመምራት ራዕይ እየተነነ በመምጣት ደረጃ ላይ መሆኑን አመላካች ሆኗል ሲል ምንጫችን ይገልጻል።
ከትግራይ ክልል ተወክለው የተገኙ አመራሮች አጀንዳውን እንደሚቀበሉ ተናግረው፣ ለችግሩ መፈጠር ዋናው ምክንያት “ ለህዝቡ ቁርጥ ያለ መልስ አለመሰጠቱ እና በአማራ ክልል የሚታየው የአመራር ችግር ነው” የሚል ሃሳብ በመሰንዘር፣ በአጀንዳነት እንዲያዝላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ፣ ቤቱ ተመካክሮ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ይተላለፍልን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በጥቂያቸው መሰረትም ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ተደርጎበታል።
የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አባይ ፅሃዬ ፣ “የብጥብጡ መንስኤ የህውሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮች ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት ማነስ ፤ የአማራ ክልል ደህንነት የአማራ ብሄርተኛነት ይለምልም በሚል የሚያራምዱት አጀንዳ እና የብአዴን ቸልተኝነት ፤ እንዲሁም የክልሉ የደህንነት ሃይል ለተቃውሞው ድጋፍ ሰጭ ሆኖ መታየቱ ነው” የሚል የብአዴን አመራሮችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከህውሃት የቀረበውን ነቀፌታ ተከትሎ በሰጡት መልስ “ ይህ ጉዳይ ኃላፊነትን እዳለመወጣት ባይታይ ጥሩ ነው” ብለዋል። ለተቃውሞ በወጡት ላይ ማንኛውም እርምጃ እንዲወሰድ በአደባባይ ትእዛዝ ያስተላለፍነው እኔ ፣ ሙክታር እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ነን ሲሉ ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ገዱ “ ሆስፒታሎች፣ የግል እና የመንግስት ክሊኒኮች ባህር ዳር ላይ በሬሳ እና በቁስለኛ የተሞሉት እኮ፣ ይህ እንደመንግስት ሁላችንም ባንደግፈውም፣ ለፖለቲካ ደህንነት ሲባል የተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ በተወሰደ እርምጃ ነው፡፡ አሁን ትኩረት ማድረግ ያለብን የሀገሪቱን ሰንደቅዓላማ እስከመቀየር የሚደርስ ህዝበ እየተበራከተ መምጣቱን፣ በርካታ ህዝበ ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዩች መኖራቸውን በማንሳት መነጋገር ነው” ካሉ በሁዋላ ፣ አሁን የተያዘው እና በመራመድ ላይ ያለው አጀንዳ መንግስት ለማስቀየር የሚያስችል ጠንካራ ሃሳብ ባይዝም ግን ፖለቲካዊ ኪሳራውን በአማራ ፤ በኦሮምያ እና በትግራይ ክልሎች ላይ አድርሷልና እንዴት እንከላከለው የሚለው ዋና ጉዳይ መሆን አለበት ሲሉ አክለዋል።
የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ ሲመልሱ ደግሞ “ ወልቃይት ማንነቱ አማራ ነው፣ ክልሉ ደግሞ ትግራይ ነው “ ያሉ ሲሆን፣ ይህንን ህዝብ የማስተባበር ኃላፊነት ፤ የመምራት እና የማረጋጋት ውሳኔ የቤቱ ነው፤ እኔም በግሌ ያንን አስፈፅማለሁ” ሲሉ ቃላቸውን ሰጠዋል፡፡
በትግራይ ክልል በኩል በወልቃይት ጉዳይ ላይ አስራ አራት ነጥቦችን የያዙ የውሳኔ ሃሳቦች ቀርበዋል። በዋናነት ‹‹ወልቃት በትግራይ ክልል ስር እንዲቆይ የአማራ ክልል ውሳኔ ማሳለፉን ›› የሚገልፅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ማዕከላዊ ኮሚቴው እንዲወያዩበት፣ የአማራ ክልል ም/ቤት ደግሞ በአሰቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ እንዲያፀድቀው የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል። አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ፡ ካሳ ተክለብርሃን፤ ብናልፍ አንዱዓለም ፤ አለምነው መኮንን ፤ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ፤ አቶ ሞክታር ከድር ለውሳኔ ሃሳቡ ድጋፍ የሰጡ ሲሆን፣ ወልቃይትን ህዝበ ውሳኔ በማስደረግ ወደ አማራ ክልል መከለል ያለምንም ጥርጥር የፖለቲካ ኪሳራ የሚያመጣ እና ቀሪ ቦታዎች ማለትም አላማጣ ፤ ኮረም ፤ ራያ አዞቦ ፤ እና ሌሎችም ስድስት ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ተመሳሳይ ጥያቄ እንዲያቀርቡ መቀስቀስ ነው የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
ውይይቱ እስከ ሌሊቱ እኩሌታ የዘለቀ ሲሆን ዛሬ እየተካሄደ ባለው ውይይት ምላሽ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሌላው አስተያየት የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በአማራ እና ኦሮምያ ሁከቱ እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ የሃይል መበታትን ስለገጠመን ሙሉ ወረዳዎችን መቆጣጠር የሚያስችል በቂ ሃይል የለንም ብለዋል። አቶ ሲራጅ “ ድንበሩን ባዶ አድርገን መሃሉን ለመቆጣጠር ያለን አቅምስ ምን ያህል ነው፣ በዚህ ሰዓት የድንበር ጠላቶቻችን ቢነሱስ መሃል አገር እንዳይገኙ ምንስ ልንፈይድ እንችላለን?” ሲሉ አስተያየታቸውን በጥያቄ ደምድመዋል፡፡
በሌላ በኩል በመላ ሃገሪቱ እየታየ ካለው ተቃውሞ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ፤ ችግሩን ለመቆጣጠር ድንበር ላይ ያሉ ሃይላትን ለማሰማራት እንደሚገደድ እና በአሁኑ ስዓት ፀጥታውን ለማስከበር የፖሊስ ሃይል አቅም እንደሌለው የፊደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የፊደራል ፖሊስ የፀጥታውን ሁኔታ አስመልከቶ ከመከላከያ ሚንስትር ጋር አቀናብሮ ባቀረበው ሪፖርት እንደገለፀው በአሁኑ ስዓት በየክልሎች እየተዛመተ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመመከት የሚያስችል ሁሉንም ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል እና በየአካበቢው ያሉ ሚነሻዎች እና ፖሊሶች ሰላሙን ለማምጣት አቅም እንደሌላቸው ከጠቀሰ በሁዋላ ፤ አመፁን ለማስፈን አሁን አጥፊዎችን ከመቅጣት ይልቅ ወደ መምክር እና መደራደር ምዕራፍ መኬዱ የሀገሪቱን ፀጥታ ይበልጥ የሚያደፈርሰው በመሆኑ አልደግፈውም ብሎአል።
ከአሮምያ ልምድ በመነሳት የአማራ ክልልም በፊደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሰራዊት ጦር አሰተዳደር ስር እንዲቆይ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጠይቆ ፈቃድ አግኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት የአማራ እና የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች ምንም አይነት ውሳኔ አያስተላልፉም ። ለሽፋን ብቻ የሚንቀሳቀስ ሃይል ግን ይኖራል ተብሎአል።
በተያያዘ ዜና ገዢው ፓርቲ ወታደሮችን ከካምፕ እያወጣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያሰማራ ነው
በመላው አገሪቱ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማኮላሸት የሰው ሃይል እጥረት ያጋጠመው ገዢው ፓርቲ ፣ ድንበር አካባቢ የሰፈሩትን እንዲሁም በተለያዩ የጦር ግንባሮች የሚገኙ የሰራዊቱ አባላትን እያወጣ በኦሮምያ ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች በብዛት እያሰማራ ነው።
በአገሪቱ የሚታየው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ ፓርቲው ተቃውሞው ለተከታታይ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ መከላከያ ሰራዊቱ ስርዓቱን መጠበቅ እንዳለበት ግልጽ መመሪያ እየተሰጠውና ለግዳጅ እንዲሰማራ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ነው።
የአጋዚ እና የፌደራል ፖሊሶች በመላው አገሪቱ በአንድ ጊዜ ሊነሳ ይችላል የተባለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር አይችሉም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው ፓርቲው፣ ሰራዊቱ ከሁለት ሊከፈል ይችላል የሚል ፍርሃት እንዳለውም ታውቋል። የአጋዚ ወታደሮች በከተሞች አድማ በመበተን ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው ከህዝብ ጎን አይቆሙም የሚል እምነት ያሳደረው ገዢው ፓርቲ፣ መሃል አገር የሚካሄዱ ተቃውሞዎችን ተቆጣጥረው የማያውቁት ልምድ የሌላቸውን ወታደሮች ወደ ከተማ ማስገባቱ፣ ወታደሮቹ ምናልባት ከህዝቡ ጎን ቢሰለፉ እና ጥቃት ቢፈጽሙ እንዴት መቆጣጠር ይችላል የሚል ጥያቄ አንስቷል። ለወታደሮች የአንድ ሳምንት የአድማ ብተና የለብለብ ስልጠና በመስጠት አደጋውን መቆጣጠር ይሻላል የሚል አማራጭ ለመከተል መወኑም ታውቋል።
በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች አንዳንድ የሰራዊቱ አባላት ከህዝብ ጎን ቆመው እርምጃ ሲወስዱ መታየታቸው ገዢውን ፓርቲ ያስጨነቀ ጉዳይ ሆኗል። በባህርዳር በፖሊስ ሃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት አምስት ፖሊሶች ህይወታቸው አልፏል።
በጎንደር በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይም በህዝብ ላይ እንዲተኩስ ያስገደዱት የፖሊስ አባል፣ “ ህዝብ ላይ አልተኩስም” በማለቱና በእምቢተኛነት በመጥናቱ በፌደራል ፖሊስ አዛዥ እርምጃ እንደተወሰደበት ታውቋል፡፡
ዛሬ በመተማ ከተማ አንድ ፖሊስ የጥበቃ ሃላፊውን በተኛበት ገድሎ አምልጧል። የሌሎች ብሄር ተወላጆች የሰራዊት አባላትን በህወሃት ታማኝ ወታደሮች ለመተካት ዛሬ በርካታ ፌደራል ወታደሮች ወደ አካባቢው ተጉዘዋል።
ይህን ዜና እያጠናከርን ባለንበት ወቅት በኢትዮ ኤርትራ ድንበር የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ መሃል ጎጃም ማምራት ጀምረዋል።
ብጥብጥ ይነሳባቸዋል እና ሰፊ የጦር መሳሪያ ይዞታ አላቸው ተብለው ወደ ተገመቱት ፤ ዳሞት ፤ ፈረሰ ቤት ፤ ፍኖተ ሰላም ፤ ሸበል በረታ ፤ ደባይ ጥላት ግን ፤ ይልማና ዴንሳ ፤ፍኖተ ሰላም እና ፈረሰ ቤት በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በወታደራዊ ካምፖች እየሰፈሩ ነው፡፡
በሌላ በኩል በሃገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ የዲሽ እና የኤል ኤን ቢ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ ነው፡፡
ህዝቡ ከመንግስት ሚዲያዎች ይልቅ ፊቱን ወደ ኢሳት ያዞረ ሲሆን በመላ አገሪቱ የአል ኤን ቢ ዋጋ ከነበረበት በአራት እጥፍ እና የዲሽዋጋም በሁለት እጥፍ መጨመሩን ኗሪዎች ተናግረዋል፡፡
******************************************************************************************
በምስራቅ ሃረርጌ ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሎ በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳረጉ።
August 12, 2016
ኢሳት (ነሃሴ 6 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ከሳምንት በፊት ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለሁለተኛ ሳምንት መቀጠሉንና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ተገለጸ።
ህጻናቶች ሳይቀሩ ለእስር መዳረጋቸውን የሚናገሩት የዞኑ ነዋሪዎች በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ከእስር እንዲፈቱና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚስወዱት ዕርምጃ እንዲቆም በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሎ የሚገኘው ይህንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ በጸጥታ ሃይሎች ከባድ የአካል ድብደባ የደረሰባቸው እንዳሉም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በሳምንቱ መገባደጃ በዚሁ ዞን ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች መገደላቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የሃረሪ ክልል ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ጀማል አህመዴ በክልሉ ድሬ ጠያራ ወረዳ በሚገኙ ሶስት አካባቢዎች ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ሃላፊው ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ጉዳዩ ወደ ህግ አካላት መመራቱን አክለው ተናግረዋል።
የምስራቅ ሃረርጌ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
የኮምቦልቻ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ስር በሚገኙት የቀርሳ፣ ፋዲስና ሜታ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ፣ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለመቆጣጠር እርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከቀናት በፊት በኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የተካሄዱ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከ100 በላይ ሰዎችን እንደገደሉ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግድያው በገለልተኛ አካል ማጠራት እንዲካሄድበት ጠይቋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ሃሙስ ገልጿል።