• አብዛኛዎቹ የዐማራ ከተሞች ከየት እንደመጡ በማይታወቁ ታጣቂዎች እንደሚጠበቁና ሕዝቡም ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸሙ ነው
• ጎንደር ከተማ በቤት ውስጥ አድማ ተመታለች፤ ትግሬዎችን ከጎንደር ማስወጣት አሁንም ቀጥሏል
• ታች አርማጭሆ ዶጋው በተባለ ቦታ አንድ ኦራል ሙሉ መከላከያ ወድሟል
• ዓለፋና ጣቁሳ የሚወራው ሁሉ የተጋነነ እንደሆነና በዐማራው ሕዝብ ላይ ጫና እንደፈጠረ ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል
• በመቄት በርካታ ወጣቶች ታስረዋል፤ ቆቦ አካባቢ ወታደሮች ላይ ጥቃት ደርሷል
ከሙሉቀን ተስፋው
August 15, 2016 |
ባሕር ዳር፤ በባሕር ዳር ከተማና አካባቢው ከ500 በላይ ሰዎች ታመው ዓባይ ማዶ አዲስ ዓለም ሆስፒታል መተኛታቸውን ከሆስፒታል አካባቢ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በመጠጥ ውኃ መበከል ችግር ‹‹አተት›› ለሚባል በሽታ ተዳርገዋል የተባሉት ሕሙማን አልጋ በመጥፋቱ ምክንያትም ድንኳን ተዘርግቶ ሕክምና ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት መረጃው ወደ ውጭ እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነ የሚናገሩት መረጃ ሰጪዎቻችን የበሽተኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን መጨመሩን ነው የሚገልጹት፡፡ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎችም ሕይወት መጥፋቱን ተናገረዋል፡፡ የውኃው መበረዝ ከባሕር ዳር ከተማ የመጠጥ ውኃ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን ግን በደንብ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ አንዳንድ መረጃ ሰጪዎቻችን እንደሚሉት አንዳሳ እና ዓባይ ማዶ አካባቢ ነው የሚሉ ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ ከከተማው የመጠጥ ውኃ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ገልጸወዋል፡፡ ይህን ያክል የጤና ችግር ስለፈጠረው ጉዳይ የክልሉ ጤና ቢሮ ያወጣው ማስጠንቀቂያም ሆነ መግለጫ እንዳለ ያገኘነው ነገር የለም፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የሚጠጡት ውኃ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በዚሁ አስተያየት ልሰጥ እንወዳለን፡፡
ጎንደር፤ የጎንደር ከተማ ዐማሮች ከትናንት ጀምሮ ቤታቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል፡፡ መሥሪያ ቤትም ሆነ የንግድ ተቋም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ነው ዛሬ በስልክ ያረጋገጥነው፡፡ በጎንደር ከተማ ከሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ሆስፒታል ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጥ የታወቀ ሲሆን ምንም ዓይነት ተሸከርካሪም ሆነ እግረኛ ዝር እንዳላለ ነው የተገለጸው፡፡
በተያያዘም በጎንደር ከተማ የሚገኙ ትግሬዎች ማታ ማታ በቦይንግ አውሮፕላን የማስወጣቱ ሒደት እስካሁን እንደቀጠለ ነው የሚነገረው፡፡ እንደ መረጃ ሰጪዎቻችን ማታ ማታ መብራት እንዲጠፋ ይደረግና አውሮፕላን መጥቶ ትግሬወችን ይወስዳል ብለዋል፡፡ ለምን መብራት እንዲጠፋ አስፈለገ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ምናልባት እንዳይታዩ ካልሆነ በስተቀር እኛ የምናውቀው ጉዳይ የለም›› ብለዋል፡፡
ምዕራብ አርማጭሆ/ ጠገዴ፤ በምዕራብ አርማጭሆ ዶጋው እሚባለው አካባቢ ወደ ጋብላ ሰርገው ሊገቡ የነበረው የትግራይ ወታደሮችን የጫነ አንድ ኦራል ሙሉ ጦር ትናንት ከቀኑ 8፡00 አካባቢ መደምሰሱን ሰምተናል፡፡ በኦራሉ የነበሩ መከላከያዎች አንድም የተረፈ እንደሌለ ነው ከአሽሬ ያገኘነው መረጃ ያመለከተው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በዳንሻ ከተማ ያሉ ትግራይ ተወላጆች ያላቸውን ዶሮ ሁሉ ሳይቀር ጭነው አካባቢያቸውን ለቀው እየሔዱ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ለምን ለቀው እንደሚሔዱ ለጠየቅናቸው ጥያቄ አካባቢውን ከትግሬዎች ነጻ ከሆነ በኋላ የዚህ አካባቢ ዐማራ በሙሉ ግንቦት ሰባት ነው በማለት ለማጥፋት እንዳሰቡ ከመጡት መከላከያዎች ሰምተናል ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ዐማራውን በሙሉ ለመጨረስ መፈለጋቸው ነው እንጅ ዐማራው ከግንቦት ሰባት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንደሌለው ያውቃሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአብራጂራና አብደራፊ ከሕዝቡ ጋር ሲወያዩ ተነግሯቸው ከመጡበት ጉዳይ ጋር የሚመሳሰል ነገር ፈጽሞ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ትግሬዎችን ዐማራው እንዲወጡ ግፊት አላደረግም፤ ዐማራው አሁንም ሆደ ሰፊ እንደሆነ ነው፤ ዐማራው የሚለው ከአገዛዙ ጋር ሆናችሁ አትውጉን ነው ያለው ሲሉ አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አለፋ/ጣቁሳ፤ በደልጊና በቁንዝላ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት ቢኖርም እንደሚወራው ወታደራዊ ግጭት እንደሌለ ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከደልጊና ከቁንዝላ ከተሞች ያገኘናው ሰዎች እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት በነበረው የዐማራ ተጋድሎ ከሁለቱም አካባቢዎች ሦስት ያክል ዐማሮች መስዋት ሆነዋል፡፡ አሁን ላይ ከተማዎቹ ከየት እንደመጡ በማይታወቁ ሰዎች እየተጠበቁ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ ሚሊሻዎች የከተማውን ሕዝብ አማረዋል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በአካባቢው ገበሬው ከፍተኛ ጦርነት ነው የሚባለው ተጨማሪ መከላከያና ፖሊስ መጥቶ ሕዝቡን አደጋ እንዲያደርስበት በር ስለሚከፍት ያልተረጋገጠ መረጃ የሚያስተላልፉ አካለት እንዲያስቡበት ተናግረዋል፡፡
መቄት/ወልደያ፤ ቅዳሜ ምሽት ወደ ወልዲያ ከተማ ከትግራይ ሲመጡ የነበሩ ወታደሮች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱን ዛሬ ከመሸ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የቆሰሉ ወታደሮች ወልደያ ሆስፒታል በወታደሮች ጥበቃ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ብንሰማም ከሆስፒታል ምንጮች ግን ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡ በተያያዘም የሰሜን ወሎዋ መቄት ከተማ ዐማሮች ትናንት ለተጋድሎ መውጣታቸውን ተከትሎ በጋሸናና በመቄት ከተሞች በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡
አጠቃላይ፤ አብዛኛዎቹ የዐማራ ከተሞች ከየት እንደመጡ በማይታወቁ ቅጥረኛ ሚሊሻዎች እንደሚጠበቁ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ሚሊሻዎች ከዐማራ ፖሊሶች ጋር ምንም ስምምነት የሌላቸው ሲሆን ማንኛውንም የማድረግ ስልጣን የፌደራል መንግሥት እንደሰጣቸው ታውቋል፡፡ ሰው ካያቸውም ለምን ታየኛለህ በማለት ከፍተኛ የአካል ጉዳት በየቦታው እያደረሱ እንደሆነ ነው የታወቀው፡፡ ከፍተኛ አበልና ማንኛውም ትጥቅ የተሟላላቸው እነዚህ ሚሊሻዎች ዐማሮችን ማማረራቸውን ገለጸው ሕዝቡን ግን ለበለጠ ትግል ማነሳሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡