Goolgule.com: የሰሜን ምዕራብ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ነገ… ወታደራዊ እርምጃ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam.1_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 23 Aug 2016 20:06:50 +0200

የሰሜን ምዕራብ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ነገ…

ወታደራዊ እርምጃ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ
oromo-amhara-protests

* ኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል

* ከገዳዮች ቁጥር በላይ ለመሞት የተዘጋጀዉ ህዝብ ይበልጣል

እንደ መግቢያ

የኢትዮጵያን ነገረ-ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ የአገር ውስጥና የምዕራቡ አለም ምሁራን የድህረ-መለስ ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ያደርጋል ብለው በተስፋ ቢጠብቁም ከታሰበው በተቃራኒ መንገድ ሲጓዝ እየታየ ነው። ተራማጅ የፖለቲካ ሀሳብ ያረጠበት ድርጅት አፈናና ግድያ መገለጫው ሆኗል። የአገዛዙን ምሰሶ ለማጥበቅ ሲባል ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ የሌላቸውን የፖለቲካ ሹመቶች በመንግስታዊ መዋቅር ከመሰግሰግ ጀምሮ በፓርቲና በመንግስት መካከል ፍጹም ልዩነት የለሽ አሰራሮችን አጠንክሮ መጓዝን መፍትሄ አድርጎ ይዞታል።

በአራት ነጥብ ግትር አቋም የታጠረው ኢህአዴግ፤ የፖለቲካ ተቋማት የፖለቲካ ብዝሃነትን እንዲያስተናግዱ ምቹ መደላድል ከመፍጠር ይልቅ የአንድ ፓርቲ ፍጹም የበላይነት የሚንጸባረቅባቸው ተቋማት እንዲሆኑ አድርጓል። የዲሞክራሲ ስርዓት የግድ የሚለውን የፖለቲካ ብዙሃነት በኢትዩጵያ የፖለቲካ ተቋማት ላይ የቀበረው ኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታል። ለድርጎ ሰፋሪዎቹና አይዞህ ባዩ የምዕራቡ አለም መንግስታት አፍ ማዘጊያ አስመሳይ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በመፍጠር በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስም ቀለብ በመስፈር የፖለቲካ አደባባዩን ለማፈን ቢተጋም የሀገሪቱ ፖለቲካዊ እውነት በሰፊው ህዝብ ላይ ከመንጸባረቅ ወደ ኋላ አላለም።

የዲሞክራሲ ተቋማት የገዥው ፓርቲ ምርኩዝ ከመሆን አልፈው የአድርባይነት ጉምቱ ምሳሌ ሆነዋል። በሀገሪቱ የሙስና መበራከት ዜጎች “መንግስት” በሚባለው አካል እምነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል። የፖለቲካ ነፃነት፣ የማህበራዊ ፍትህና ሌሎች ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎችን ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ማስተናገድ የተሳነው የበርኸኞቹ ስብስብ ለህዝባዊ ጥያቄዎች እስር፣ እንግልት፣ ስቅየትና፣ ግድያን እንደ ብቸኛ መፍትሄ አድርጎ ይዞታል። የኢህአዴግ ማንአህሎኝ ባይነት እርምጃዎች አገሪቱ ልትወጣው ወደማትችለው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ይገኛል።

በበርኸኞቹ የፖለቲካ መሀንዲስነት የሚዘወረው ኢህአዴግ ለህዝባዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ወታደራዊ የኃይል አማራጭን እንደ መፍትሄ ሲወስድ እየታየ ነው። ከዚህ አደገኛ ተግባር ተነስተን፤ በርኸኞቹ በሩብ ክፍለ ዘመን የአገዛዝ ጉዟችው ውስጥ የሲቪል አስተዳደር ጥበብን ከመላመድ ይልቅ ወታደራዊ ባህሪያቸው እየፋፋ እንደመጣ መረዳት ይቻላል። በድህረ-መለስ አራት የአገዛዝ አመታት ውስጥ ኢህአዴግ በአያሌው የተፈተነበት ዓመት ቢኖር እያገባደድነው ያለው 2008 ዓ.ም በቀዳሚነት ይጠቀሳል።eprdf

አስር የጭንቅ ወራት ያስቆጠረው የኦሮሞ ተቃውሞ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገሪቱ የሰሜን ምዕራብ አካባቢ የማንነት ጥያቄን አስታኮ የተነሳው ብረት አከል ህዝባዊ እምቢተኝነት የኢትዮጵያን ነገ እንድንፈራው አድርጎናል። የችግሩን አሳሳቢነት የሚያጎላው ደግሞ ገዥው ፓርቲ ለችግሩ እውቅና በመስጠት ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ወታደራዊ የኃይል እርምጃዎችን የሙጥኝ ብሎ መያዙ ነው። ለወታደራዊ የኃይል እርምጃዎች የማይንበረከክ ባለ ብረት ህዝብ፣ ቁሞ መሞትን ምርጫው አለማድረጉ ደግሞ ሀገሪቱ ወደ አዝጋሚ ጦርነት እየተጓዘች ያለች አስመስሏታል።

የሰሜን ምዕራብ ፖለቲካ

በዚህች ጽሁፍ ‹ሰሜን ምዕራብ› እያልን የምንጠራው አካባቢ በመደበኛው የመልከዓ-ምድር ስያሜ ሳይሆን ውስንነት ባለው መልኩ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃምን እንዲሁም የሰሜንና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎችን ይሆናል። በዋናነት የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄን አስታኮ እየታየ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ማዕከል የሆነውን ጎንደር ከተማና አካባቢውን ይመለከታል።

በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ብዙ እየተባለለት ያለውን የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ፤ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡትን አቤቱታና ሌሎች መሰረታዊ ቅሬታዎችን በተመለከተ በጣም አቃለልከው ካልተባልኩ በሚቀጥለው አንቀጽ ማጠቃለል ይቻል ይመስለኛል።

በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ የትግራይ ወሰን ተከዜ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያትታሉ። ከመካከለኛው ዘመን እስከ 21ኛውክፍል ዘመን ድረስ ኢትዮጵያን በተለይም ሰሜኑን አካባቢ ባጠኑ የታሪክ ተመራማሪዎችና የታሪክ ፀሐፍት የትግራይ ወሰን ተከዜን ተሻግሮ እንደማያውቅ ይገልፃሉ። የወልቃይት  መልከዓ-ምድር በሰሜን ተከዜ (ኤርትራ)፣ በደቡብ ጠገዴ (ጠገዴ በአማራ ክልል ስር ያለ ወረዳ ሲሆን፤ ጸገዴ ደግሞ በትግራይ ክልል ስር ያለ ወረዳ መሆኑንና በሁለቱም ወረዳዎች የሚኖረው ነባር ህዝብ ከታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የኢኮኖሚ ትስስርና መልከዓ-ምድር አኳያ ምንም አይነት ልዩነት የሌለው መሆኑን ይልቁንስ ልዩነቱ ድህረ-ደርግን ተከትሎ ‹ጠ› እና ‹ጸ› በሚሉ ፊደላት ብቻ ልዩነት ለመፍጠር እንደተሞከረ ያስታውሷል)፣ በምስራቅ የተከዜ ወንዝን (ትግራይ) በምዕራብ አርማጭሆና ሱዳን ወልቃይትን ያዋስኑታል። ወልቃይት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ወገራ አውራጃ፣ በደርግ ግዜ ደግሞ በጎንደር ክፍለ ሀገር በወገራ አዉራጃ ይተዳደር የነበረ አካባቢ ነዉ። ይሁንና በዘመነ ኢህአዴግ ያለ ወልቃይት ነባር ህዝብ ፍላጎት የህዝቡን ማንነት በሚጨፈልቅ መልኩ በትግራይ ክልል፣ በምዕራብ ትግራይ ዞን ተከልሎ ይገኛል። የወልቃይት ነባር ህዝብ የራሱ የሆነ የአማርኛ ዘይቤ ያለው ሲሆን፣ የትግርኛ ቋንቋም ከገበያ ትስስር ጋራ በተያያዘ በተጨማሪነት ይናገራል። ከሱዳን በሚዋሰንበት የምዕራብ ወልቃይት አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የሱዳን አረብኛ ለመግቢያነት ይጠቀማሉ። የወልቃይት ነባር ህዝብ በቀደመው ጊዜ ባህላዊ ዘፈኑ፣ ጭፈራውና ዳንኪራው፣ የሃዘን እንጉርጉሮ፣ ቀረርቶውና ሽለላው ከትግራይ ባህላዊ ሁነት ይልቅ ለጎንደር ባህል ይበልጥ ቅርብ ነበር/ነው። ይሁንና አዲሱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የወልቃይት ነባር ህዝብ የሚናገረው አማርኛ ቋንቋና የአካባቢውን ባህላዊ ማንነት በሚጨፈልቅ መልኩ በሰፈራ ፕሮግራም አካባቢውን በተቆጣጠሩት የትግራይ ብሄርተኞች ሊዋጥ ችሏል።

welkait-tsegede“ለዘመናት የወልቃይት ህዝብ (ገበሬ) ሲያርሰው የነበረ መሬት ተነጥቆ ለትግራይ እርሻ ድርጅት ተሰጥቷል። ህዝቡ እኛ የት እንውደቅ ተብሎ አቤቱታ እንኳን ቢያቀርብም የትግራይ ክልል በየአመቱ ለምዕራባዊ ዞን እያለ አዳዲስ የመሬት አዋጅ በማውጣት ለትግራይ ተወላጅ በወልቃይት መሬት ባላባት  ሆነው እንዲያስተዳድሩት ሲደረግ የወልቃይት ህዝብ ግን ከመሬቱ እንዲነሳና እንዲሰደድ የተለያዩ እርምጃ ተወስደዋል። የዚህ ሰለባ የሆኑት የወልቃይት ተወላጆች ለአብነት፡- በአማራ ክልል በሶረቃ፤ አብራሃጅራ፤ አብደራፊ፤ መተማ፤ ቋራ፤ ሽህዲ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እና በጋምቤላ ክልል ተሰደው ይገኛሉ። በሰፈራ የወጡት የትግራይ ተወላጆች ግን ከሁለት ሄክታር አልፈው የሃምሳና የአንድ መቶ ሄክታር ባለቤቶች ሆነው ይታያሉ። በአጠቃላይ በአካባቢያችን አልምተን እንዳንጠቀም አድልዎ ተፈጽሞብናል። … ልጆቻችን በቋንቋቸው እንዳይማሩ ተደርጓል። … የአካባቢያችን ጥንታዊ የሀገር፤ የወል እና የጋራ ስሞች ማለትም የወረዳ፤ ከተማ፤ መንደር፤ ወንዝ ጋራ ሸንተረር በትግረኛ ስም ተሰይመዋል”።

ከላይ የተመለከተው አንቀጽ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ካቀረቡት ባለ ስምንት ገጽ አቤቱታ ተቀንጭቦ የቀረበ ነው። ይህች አንቀጽ የወልቃይትን ህዝብ የባህልና ማንነት ቅሬታዎችን እንዲሁም የኢኮኖሚ መገለልን ይበልጥ የምትገልጽ ነች። ከዚህ በላይ ለተመለከቱት የባህልና ማንነት ቅሬታዎች አሁንም የኢኮኖሚ መገለል የተጋለጡት ወልቃይቴዎች ለሁለት አስርት ዓመታት የማንነት ጥያቄውን በያዝ ለቀቅ፤ ከረር ላላ ባለ መልኩ ጥያቄውን ሲያገላብጡት ቆይተው ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ የማንነት ጥያቄውን የሚያስተባብሩ የኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አቤቱታቸውን አሰምተዋል። የማንነት ጥያቄው ወደ አፈሙዝ ቋንቋ ከመቀየሩ በፊት ጥያቄውን በተመለከተ ወልቃይቴዎች በሰላማዊ መንገድ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ከሽንፋ እስከ ጎንደር ድረስ ባሉ ከተሞች በተለያዩ ግዜያት አድርገዋል።

ለምን አሁን?

የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ወደ ፊት ጎልቶ እንዲወጣ ያደረጉት ውስጣዊና ውጫዊ ገፊ ምክንያቶችን በቢሆን እድል ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል። ከውስጣዊ ግፊት አኳያ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለዉ የቢሆን እድል ነባሩ የወልቃይት ህዝብ ከባህልና ማንነት ጋር በተያያዘ የሚያቀርባቸው ቅሬታዎችና የኢኮኖሚ መገለሎች እንዲሁም ያለፉት ሁለት አስርታት ተደማሪ ቅሬታዎችንና ብሶቶችን እየሰሙና እያዩ ያደጉት የአዲሱ ትውልድ አባላት የማንነት ጥያቄው ገፍቶ እንዲወጣ ተጽእኖ አሳድሯል ማለት ይቻላል።

ለወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጎልቶ መውጣት ውጫዊ ገፊ ምክንያቶችን ደግሞ በሦስት የቢሆን እድሎች ለይተን ማየት እንችላለን።

የቢሆን ዕድል አንድ፡- የዘውግ ፖለቲካን ዋነኛ የሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋጽዖ እንዲሆን በትጋት እየሰራ ያለው ኢህአዴግ፤ የማንነት አረጋጋጭ ጥያቄዎችን መልስ ሰጥቼ ጨርሻለሁ ቢልም፤ በዘመነኛ አጥኝዎች አጠራር ከዘውግ ብሄርተኝነት አነስ ያሉ የትህተ-ብሄርተኝነት ጥያቄዎች ይነሱበት ጀምረዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ከመሰረቱ የተበላሸው የፌዴራሊዝም ቅርጽ የወለዳቸው እንደሆኑ የሥርዓቱ ተቺዎች እምነት ነው። ከረፈደ የሚቀሰቀሱ የማንነት ጥያቄዎች የበዙበት ኢህአዴግ፤ ምንም እንኳ ጥያቄዎቹ የቆዩ ቢሆንም በድህረ መለስ የአገዛዝ ዘመኑ ሁለት የማንነት ጥያቄዎችን አስተናግዷል። የቅማንትና የቁጫ ማንነት አረጋጋጭ ጥያቄዎች ፌደሬሽን ምክር ቤት ደርሰዉ የቁጫ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር፤ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ግን በፌደሬሽን ምክር ቤት መሪነት የአማራ ክልል ምክር ቤት መጋቢት 2007 ዓ.ም የይሁንታ ውሳኔ ሰጥቶበታል።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ባቀረቡት የድንበር ማካለል/ወሰን ልክ ባይሆንም የቅማንት ብሄረሰብ በልዩ ወረዳ ስር አርባ ሁለት የገጠር ቀበሌዎችን በማቀፍ እንዲከለል የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔውን አሳልፏል። ይህ ውሳኔ ለወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትና አማራነታችን ይከበር ለሚሉ ወልቃይቴዎች የማንነት ጥያቄውን እንዲያቀጣጥሉት በር ከፍቶላቸዋል። የቅማንት ብሄረሰብና የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ አቀራረብ ሞዴል የተለየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የዘውግ ፖለቲካ እስከተራመደ ድረስ፤ የማንነት ጥያቄዎች ማቅረብ ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑንና ከረፈደም ቢሆን የማንነት ጥያቄዎችን ምላሽ እንደሚያገኙ የተማመኑት የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የማንነት ጥያቄዉን በአዲስ ጉልበት እንዲጀምሩት ምክንያት እንደሆናቸው በቀዳሚ የቢሆን እድል ማስቀመጥ ይቻላል።

የቢሆን ዕድል ሁለት፡- በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ስር እንደ አብርሃጅራ፤ አብደራፊ፤ ጠገዴ የተሰኙ ወረዳዎች ስር ካሉት የገጠር ቀበሌዎች የተወሰኑትን በተለይም ምዕራብ አርማጭሆ አካባቢ ያሉትን የገጠር ቀበሌዎች ወደ ትግራይ ክልል ለመደባለቅ የሚደረገው የክልሉ መንግስት እንቅስቃሴ በአካባቢው ህብረተሰብ እምቢተኝነት ዛሬም ድረስ ሊሳካ አልቻለም። አካባቢውም ውጥረት የነገሰበትና በየጊዜው ከንብረት መውደም አልፎ እስከ ህይወት መጥፋት የሚደርስ ግጭት በተደጋጋሚ እየተከሰተ በመንግስት ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ግጭቶችን “የማብረድ” ስራ ሲሰራ ቆይቷል። የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል ርዕስ መስተዳድሮች፤ ከፀጥታና ደህንነት ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ የካቢኔ አባላትና ተስማሚነት ያላቸው የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በተደጋጋሚ የተካሄዱ ውይይቶች ፍሬ አልባ ሆነዉ በመቅረታቸው አካባቢው ሁሌም ቢሆን ውጥረት የነገሰበት ሊሆን ተገዷል። በዚህ የተነሳ የትግራይና የአማራ ክልል ግልጽ የሆነ የድንበር አዋሳኝ ቦታ የላቸውም። ይህን ጉዳይ ከወልቃይት መሬት ጋር አስተሳስረው ለማየት የሚሞክሩ የአካባቢው መካከለኛ አመራሮች ለወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት ጥያቄ መቀጣጠል የራሳቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ።telemt welkait

በሁለቱ ክልል የድንበር ወሰን ላይ በተለይም “ግጨው” (የቦታ ስም መሆኑን ያስታዉሷል) እና በአካባቢው የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በአካባቢው መካከለኛ አመራሮች ጥልቅ ቅሬታን እየፈጠረ በመሄዱና ‹የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው› የሚለው ተረክ አካባቢውን በሚያስተዳድሩ የአማራ ክልል መካከለኛ አመራሮች እያጎነቆለ በመምጣቱ የወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት ጥያቄ የደጀን ኃይል ድጋፍ አግኝንቶ ሊያንሰራራ እንደቻለ በሁለተኛ ደረጃ የቢሆን እድል ማስቀመጥ ይቻላል።

የቢሆን ዕድል ሦስት፡- በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው የቢሆን እድል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሁለቱም የቢሆን ዕድሎች ጋር ይገናኛል። የቅማንት የማንነት ጥያቄ ከቋንቋው ተናጋሪዎች መመናመንና የባህል መግለጫዎቹ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው እየተዋጡ (assimilate) መሄዳቸውን እንደ ምክንያት በማቅረብ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ለማፈን የክልሉ መንግስት ብዙ ርቀት ለመጓዝ ሞክሯል። በዚህም የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር ደም አፍሳሽ ግጭቶች አካሂደዋል። በፌዴራሉ መንግስት መሪነት የማንነት ጥያቄው በክልሉ ምክር ቤት ምላሽ እንዲሰጠው መደረጉ ይታወሳል። የቅማንት የማንንት ጥያቄ ከአመታት ዝምታ (ያዝ ለቀቅ) በኋላ በአዲስ ኃይል ገንኖ ሊወጣ የቻለበት ምክንያት የትግራይና የአማራ ክልል ድንበር ውዝግብ የአካባቢውን ውጥረት እያባባሰው ከመጣ ወዲህ ነው። የድንበር ውዝግቡ በዋናነት በምዕራብ አርማጭሆ በኩል የ“ግጨው” ቦታና አካባቢው ሲሆን፤ ጉዳዩ በሁለቱም ክልል ርዕስ መስተዳድሮች ተይዞ ሰፊ ድርድር (ክርክር ማለት ይቀላል) የተካሄደበት፤ ከዚህም ባሻገር በአካባቢው ገበሬዎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ተካሂዷል። የህወሓት አመራሮች ይህን ውጥረት ለማስቀየስ (tension divert ለማድረግ) የቅማንት የማንነት ጥያቄ ጎልቶ እንዲወጣና የአማራ ክልል መንግስት በቅማንት የማንነት ጥያቄ እንዲጠመድ ማድረጋቸው የብዙዎቹ የጉዳዩ ተከታታዮች ምልከታ ነው (ይህን ጉዳይ በተመለከተ “የኢህአዴግ ቁልቁለት” የሚለውን መጽኀፍ በማንበብ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል)።

ወትሮዉንም ቢሆን የሴራ ፖለቲካ የተጣባው የኢህአዴግ ፖለቲካ አሁን ደግሞ ተራው የብአዴን ሆነና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ወደፊት እንዲገፋ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ አመራሮች ያሉ ይመስላል። ይህን የቢሆን እድል ይበልጥ የሚያጠናክረው ከሀምሌ 04/2008 ጀምሮ በሰሜን ምዕራብ እየታየ ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭት በተመለከተ የአማራ ክልል መንግስት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዉ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጠዉ መግለጫ የ“መልካም አስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎችን መነሻ ያደረገ” መሆኑን አምኗል። በአንጻሩ የፌዴራሉ መንግስት “ጸረ-ሰላም ኃይሎች፣ የጥፋት ተልዕኮ ያላቸው፣ በአንድ ብሄር ያነጣጠረ ጥቃት …” በሚሉ ቃላት የታጀቡ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት የማንነት ጥያቄውን ታኮ የተፈጠረውን ግጭት ለማድበስበስ ሲታትር ተስተውሏል። የአማራ ክልልና የፌዴራሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ እየሰጡት ያለውን ያልተናበበ መግለጫ በሴራ ፖለቲካ ልዩነት መስመር መሀል ስናስተውል የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጎልቶ ሊወጣ የቻለበት ምክንያት ግልጽ ይሆንልናል።

“ … ብናረፍድም የአማራ ክልል ህዝብ ከጎናችን ነው!”

ሐምሌ 04/2008 ዓ.ም ምሽት፤ ጎንደር ከተማ ላይ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ አባላትን ለማሰር የተደረገው ዘመቻ በፌዴራሉ መንግስት አገላለጽ “እክል” የገጠመው በመሆኑ ምሽቱንና በተከታታይ ሁለት ቀናት በጸጥታ ኃይሉና በከተማዉ ነዋሪ መካከል ደም አፍሳሽ ግጭቶች ተከስቷል። በወቅቱ የፌዴራሉ መንግስት ባመነው መረጃ መሰረት 9 የፌዴራል፣ አንድ የመከላከያ እና አንድ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ በድምሩ 11 የሰራዊቱ አባላት እንደተገደሉ፣ ከሲቪል ደግሞ 5 ሰዎች እንደሞቱ በተጨማሪም 9 የሰራዊቱ አባላት ቁስለኛ እንደሆኑ መገለጹ የሚታወስ ነው። ከሐምሌ 05-06/2008 ዓ.ም ድረስ በዘለቀው ህዝባዊ አመጽ በአስር ሚሊዮኖች የሚገመት ንብረት መውደሙም ይታወሳል።

የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ የታፈነው ህዝባዊ አመጽ መቀስቀሻ ሆኖል። ሐምሌ 24/2008  ጎንደር ከተማ ታሪኳን በሚመጥን መልኩ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል። የተቃውሞ ሰልፉ በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ያልተሰጠው ቢሆንም ብሶት የማያስጉዘው መንገድ የለምና የጎንደር ከተማና አካባቢ ነዋሪ በእለቱ ህግና ፍርድን በእጁ በመጨበጥ መብቱን አስከብሯል። ጎንደር የነፃነትና የክብር ፋና ከተማ መሆኗን ባስመሰከረችበት የተቃውሞ ሰልፍ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ የቀረበዉ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄና የታሰሩ የኮሚቴ አባላትን በተመለከተ ነበር። ከዚህ ጎን ለጎን ለብዙዎቹ የጉዳዩ ተከታታዮች ግርምት ሊፈጥር የቻለው በኦሮሚያ የሚደረገውን የብላቴናዎች ግድያና አፈና አጥብቀው የሚያወግዙ፣ የፖለቲካ ነፃነት መሻትን የሚያንጸባርቁ፣ የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎችን ያዘሉ፣ አፋኝ አዋጆችን የሚቃወሙ፣ የኃይማኖት ነጻነትን የሚጠይቁ፣ … መፈክሮች በሰልፉ ላይ ተሰምተዋል። ከሁለቱ ታላላቅ ኃይማኖቶች (ኦርቶዶክስና እስልምና) የተጋበዙ የኃይማኖት አባቶች በተገኙበት የተቃውሞ ሰልፍ አራት መቶ ሃያ ሺህ የሚሆን ህዝብ ተሳታፊ እንደነበረ ይገመታል። የጎንደር እናቶች የመላኩ ተፈራ የመከራ ጊዜ ከአደባባይ እንዲያፈገፍጉ ሳያደርጋቸው የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ሆነዋል። እናቶች በሰልፉ ተሳታፊ gondar24 ለሆኑ ወጣቶች ከእንስራቸው ውሀ እየጨለፉ ሲያጠጡ የታየበት ሁኔታ ህዝባዊ ብሶቱ ምን ድረስ እንደዘለቀ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ የሰልፉ አስተባባሪዎች የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄን በተመለከተ ጥያቄውን በህገ-መንግስታዊ አግባብ እንዲመለስ፣ የታሰሩ የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ አጽኖት ሰጥተዉ ጠይቀዋል። የማንነት ጥያቄውን ወደ አደባባይ ለማውጣት ብዙ መስዋዕትነት እንደተከፈለበት የተናገሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች “የማንነት ጥያቄውን ለማቅረብ ብናረፍድም የአማራ ክልል ህዝብ ከጎናችን ነው!” በሚል ደስተኛነታቸውን ገልጸዋል። ያለምንም የጸጥታ ግርግር የተጠናቀቀው የጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ፤ በቀጣዮቹ ሳምንታት በሌሎች የክልሉ ከተሞች ላይ ለተካሄዱ የተቃዉሞ ሰልፎች መነቃቃት ፈጥሯል። ይሁንና ህዝባዊ ጥያቄዎችን ለሚያንጸባርቁ ሰልፈኞች አጸፋው ጠብ-መንጃ ሆነና ብዙዎቹ ብላቴኖች እንደወጡ ቀርተዋል። የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን ቤት ይቁጠራቸው።

ከጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ደባርቅ፣ ደባት፣ ሳንጃ፣ ሶረቃ፣ አብራሃጅራ፣ ማክሰኝት፣ ቆላድባ፣ አዲስ ዘመን፣ ወረታ፣ ሀሙሲት፣ ደብረታቦር፣ ንፋስ መውጫ (ጋይንት)፣ ባህርዳር፣ ጢስ አባይ፣ ፍኖተ ሰላም፤ ደብረማርቆስ ከተሞች ላይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሄደዋል። በብዙዎቹ የተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደባቸው ከተሞች የመንግስት ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ የብዙ ሰልፈኞች ህይወት ሊያልፍ ችሏል። በተለይም በደብረ ታቦርና በባህርዳር ከተማ የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የብዙዎቹን የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞች እምነት በሚፈትን መልኩ የብዙ ብላቴኖች ህይወት በጎዳና ላይ ተቀጥፏል (ከእያንዳንዱ ከተማ የሚሰማው የሟቾች ቁጥር የተለያየና ተቀራራቢነት የሌለዉ በመሆኑ የሟቾችን ቁጥር እዚህ ላይ መጥቀሱ አንባቢን ማሳሳት ስለሚሆን ቁጥሩን መዝለሉ የተሻለ ነው)።

መፈክር ይዘው የወጡ ብላቴናዎች የጓደኞቻቸውን አስክሬን ተሸክመው ወደየሰፈራቸው ተመልሰዋል። በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ ሰልፉን የተቀላቀሉ ጎልማሶች በቃሬዛ ወደ ቤታቸው ገብተዋል። ግፈኞች “በለው!” ማለታቸውን አላቆሙምና እናቶች ዛሬም እንደ ትላንቱ ዋይታ አልተለያቸውም፣ አባቶች ምርኩዝ አቀባይ ልጆቻቸውን ተነጥቀዋል። ጎዳናዉ የብላቴኖችን ደም መምጠጥ አልሰለቸውም። መንግስታዊ ፍጅት በሚመስል መልኩ በተወሰደው የኃይል እርምጃ አትራፊው ማን እንደሆነ ግዜና ትውልድ የሚወስነው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ነገ …

ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በፍጥነት በሚቀያየሩባት ኢትዮጵያ ነገን መተንበይ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ይሁንና የኢትዮጵያን ዛሬ ስናስተዉል የትላንቷ ኢትዮጵያ ዉጤት መሆኗ ከአንባቢ የተሰወረ አይደለም። በዚህ አግባብ የኢትዮጵያ ዛሬ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ ምስል የሚሰጠን ጭብጥ ይኖራል።

የድህረ መለስ ኢህአዴግ የበዛ ዝግ አምባገነንነት ምርጫዉን አንድ መቶ ፐርሰንት ከመጠቅለል ጀምሮ የአፈና እጆቹ እየበረቱ መጥተዋል። የምርጫ ፖለቲካን ሁለንተናዊ ፋይዳ አርቆ የቀበረዉ ኢህአዴግ፤ የፖለቲካ አደባባዩን የመቃብር ስፍራ አስመስሎታል። ያም ሆኖ ፖለቲካዊ መብቃት ላይ ያልደረሱ ብላቴኖች የህዝባዊ አመጹ አቀጣጣይ ሆነዋል። አንዳች የቅቡልነት መነሾ የሌለዉ ኢህአዴግ ሁሉን ጠቅልሎ የመግዛት አባዜዉ የበዛ ዋጋ የሚያስከፍለዉ ጊዜ ላይ ይገኛል።

አስር ወራትን ያስቆጠረዉ የኦሮሞ ተቃዉሞ የወዲያዉኑ መንስኤ “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን” ቢሆንም፣ ማስተር ፕላኑ ከተሰረዘ በኋላም ተቃዉሞዉ ተጠናክሮ ቀጥሏል። እጅግ በተጠናና በተደራጀ መንገድ በሚመስል መልኩ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ እስከ ዮኒቨርስቲ ባሉ የክልሉ ተወላጅ ተማሪዎችን ባቀፈ መልኩ የተካሄዱ ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎች የወጣቶች ግድያና እስር ተጠናክሮ ቀጥሏል። የተቃዉሞዉ መሰረት በጊዜ ሂደት እየሰፋ መጥቶ በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች በተፈራራቂነት በመዝለቁ ህዝባዊ ተቃዉሞዉ መቆሚያ አጥቷል። እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተከታታይ ሪፖርቶች ሐምሌ 30/2008 ዓ.ም በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች በተጠራዉ የተቃዉሞ ሰልፍ የሞቱትን ጨምሮ አስር ወራትን ባስቆጠረዉ የኦሮሞ ተቃዉሞ ከ600 በላይ ሰዎች ህይወታቸዉ አልፏል። ኦሮሚያ ክልል በሲቪል አስተዳደር እየተመራች ያለ የሚመስለዉ በ“መንግስት” ሚዲያ ነዉ እንጂ በእዉነታዉ በወታደራዊ አስተዳደር ስር ወድቃለች።

ጥልቅ የማንነት ቅሬታዎችንና የኢኮኖሚ ብዝበዛ ተረክን እየሰሙ ያደጉት የኦሮሞ ልጆች የመሬት ባለቤትነትን አስታከዉ ያነሱት ተቃዉሞ ወደ ቀደመዉ መሰረታዊ ቅሬታ ተጠምዞ ‹የፖለቲካ ነጻነትና በማዕከላዊ መንግስቱ በቁመታችን ልክ የፖለቲካ ዉክልና ይስጠን! የኢኮኖሚ የራስ ገዥነት አቅማችን  በህዳጣኖች አይወሰንም! ኦሮሚያን ለኦሮሚያ!› ወደሚል ፈታኝ አቋም ተሻግሯል። ይህ አቋም ብዙዎች የኦሮሞ ልጆች ሊወድቁለት የፈቀዱት እዉነት ሆኗል። እየሆነ ያለዉም ይሄዉ ነዉ።

በመስመር መሀል ለወራት ድምጹን አጥፍቶ የቆየዉ “የድምጻችን ይሰማ!” የሙስሊሙ ንቅናቄ በየአቅጣጫዉ በሚታዩ ህዝባዊ ተቃዉሞዎች አስታከዉ አጀንዳቸዉን በማንጸባረቅ ላይ ናቸዉ። ይህ መነቃቃት ምናልባትም በቀጣይ ወራት የንቅናቄዉ መገንፈል ከታየ የምዕራቡንና ምስራቁን የኢትዮጵያ አካባቢ ሊያዳርሰዉ ይችላል። የሙስሊሙ ንቅናቄ በራሱ ኃይማኖታዊ ነጻነትንና የኮሚቴዎቹን ጉዳይ በሚያጠይቅ የአጀንዳ መስመር ተነጥሎ ባይወጣ እንኳ በየአቅጣጫዉ እየታዩ ላሉ ህዝባዊ እምቢተኝነቶች መጎልበት ቀላል የማይባል ዋጋ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያን ባህል መለዮ አርቃቂዉ አማራ በቅሬታ የተሞሉ ሃያ አምስት አመታትን ገፍቷል። የደርጉ ወታደራዊ ዘመን እንደ ሀገር የመጣ መዐት በመሆኑ አስከፊነቱ የወል ገጽታ ነበረዉ። ዛሬ ላይ የአማራ ጉዳይ የሥልጣን ጥያቄን በሁለተኛ አጀንዳ በመያዝ ማንነትን የማስከበርና ህልዉናን የማስቀጠል ጉዳይ ሆኗል። ሩብ ክፍለ ዘመን የተሻገረዉ የገዥዉ ግንባር አገዛዝ እንደ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዉ ፈተና ያበዛበት ዘዉግ ቢኖር ኦሮሞ ብቻ በደሉን የሚስተካከለዉ ይመስለኛል።

ብሶት ህወሓትን ብቻ ወልዶ አልቆመምና ለአመታት የተከማቸዉ ግፍና ጭቆና በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ጎንደር አካባቢ እየተስተዋለ የመጣዉ ብረት ማንሳትን ያካተተ ህዝባዊ አመጽ ቀስቅሷል። ብረት አከሉ ህዝባዊ አመጽ የአመጹን ተራዛሚነት ከማበርታት ባሻገር ኢ-ተቀልባሽ ያደርገዋል። ዘውግ ተኮር የማንነት ትንቅንቅ የሀገሪቱ ዋነኛ ፖለቲካዊ ክስተት በሆነባት ኢትዮጵያ ለማንነታቸዉ የሚወድቁ ወጣቶች ቢፈጠሩ የሚገርም አይደለም።

ጥልቅ ድህነትና ሥራ አጥነት በስፋት በሚስተዋልባቸዉ ሁለቱም ክልሎች እየታየ ያለዉ ህዝባዊ እምቢተኝነት በማህበራዊ ድረ-ገጾች የጥላቻ ንግግሮች/ጽሁፎች መታጀብ ጀምሯል። ይህ አዝማሚያ የገዥዉ ግንባር አስኳል-ህወሓት ላይ የሚያርፍ ይሆናል። በህወሓት አመራሮች የበዛ የሥልጣን ጥመኝነት የተነሳ የህወሓት አወዳደቅ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ እንዳይኖር ያሰጋል። በበሽር አላሳድ ቤተሰቦች በኩል የአላዋይቶች ጉዳይ እንደሚታየዉ ህወሓት ይህችን መሰል የፖለቲካ ቁማር መጫወት ሳይጀምር (አንዳንዶች ጨዋታዉን ከጀመረ ቆይቷል ይላሉ) የትግራይ ህዝብ ዝምታዉን በመስበር የህወሓትን አደጋ ያዘለ የጉርምስና ተግባር ‹ተዉ!› ሊለዉ ይገባል። ይህ የማይሆን ከሆነ የኢትዮጵያ ነገ ከተስፋ ይልቅ የጭንቅና መዐት ጊዜ እንደሚሆን እሙን ነዉ። የርስ በርስ ጦርነትም የቀረበ እንጅ የራቀ አይሆንም።

መዉጫ በር!

ሀገሪቱ ለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ወታደራዊ እርምጃ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ያሻታል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃኑ በብቸኝነት የያዙት መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ‹በልሂቃን የበላይነት ተጠፍንጎ የተያዘዉን የፖለቲካ ተሳትፎ፤ የፖለቲካ ተሳታፊነት መብት የበርካታ የሀገሪቱ ዜጎች መብት ማድረግ ይገባል› የሚለዉን የተቺዎች ምልከታ እያሰመርንበት አፋጣኝ ጊዜያዊ መፍትሄ ከመሻት አኳያ የሀገሪቱ ልሂቃን በሰከነ መንገድ መወያያት ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራት ሀገር እንድትሰነብት ከተፈለገ የምሁራን ሚና ጎልቶ ሊወጣ ይገባል። ጉዳዩ የሀገር ህልዉና መቋጠሪያ ዉል ነዉና ከጠባብ ልሂቅነት ሰፋ ያለ ሀገራዊ ምልከታ ማንሳት ተገቢ ነዉ። በርግጥ ምሁራዊ ዋጋ በሚጠይቁ ጭብጦች ላይ ለመናገርና ለመወያየት ብሎም ለመጻፍ አለመፍቀድ የገዥዉ ግንባር ምሁር-ጠል ፖሊሲ ዉጤት ነዉ። ግና፤ ይህን መሰል አፍራሽ የፖለቲካ መስመር ለመግራት ምሁራዊ አይናፋርነትን መግፈፍና እዉነት ላይ ቁሞ በእዉነት ስለ እዉነት መናገር ‹ሳይማር ያስተማራችሁ› ህዝብ ዉስጣዊ መሻት ነዉ። መቼም በዚህ ጊዜ እንደ ንጉሱ ዘመን ለሥርዓት ለዉጥም ሆነ ለሀገራዊ ፈተናዎች መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት መጠየቅ አዋጪነቱ አይታየኝም። የልሂቃኑ ሚናም ወሳኝነቱ ከዚህ አንጻር ነዉ።

የጥቅመኝነት ፖለቲካን በተሻገረ መልኩ ይህችን የበደል ቋት ሀገር እንደ ሀገር የሚያሰነብታትን ረብ ያለዉ የፖለቲካ ሃሳብ ወደ አደባባይ ማዉጣት በዘመን የተፈተነ የሀገር ጥሪ ነዉ። ዋጋ ባለዉ መንገድ አቻቻይ የፖለቲካ ሀሳብ ማፍለቅ ሀገርና ትዉልድ ለልሂቃኖቻችን የጣሉት ኃላፊነት ሆኗል። መፍትሄዉ በዘገየ ቁጥር ግን ፖለቲካዊ መብቃት ላይ ያልደረሱ ብላቴኖች ህግንና ፍርድን በእጃቸዉ ጨብጠዉ ጎዳናዉ ላይ እየተዋደቁ መቀጠላቸዉ አይቀሬ ነዉ። ከብላቴኖቹ ፍርካሽ ጭንቅላት ጀርባ የነገዋን ኢትዮጵያ መሰንበት መጠራጠር ተገቢ ነዉ።

በሌላኛዉ ጫፍ ከህዝብ ጋር ደም እየተቃባ ያለዉ ገዥዉ ግንባር ነገን አሻግሮ ማየት ግድ ሊለዉ ይገባል። በአለም ታሪክ ህዝብን ገድሎም ሆነ አስሮ የጨረሰ አገዛዝ አልታየም። ከገዳዮች ቁጥር በላይ ለመሞት የተዘጋጀዉ ህዝብ ይበልጣል። ከዉልደቱ እስከ ሞቱ ድረስ በድራማ የታጀበዉ ደርግ መቃብሩን የቆፈረዉ በገዛ እጁ ነዉ። ደርግ የሻዕብያንና የህወሓትን የገጠር ሽምቅ ዉጊያ መቋቋም ተስኖት የወደቀዉ አንዳች ህዝባዊ ቅቡልነት የሌለዉ በመሆኑ እንጅ በሸማቂዎቹ ብርታት አልነበረም። ማህበራዊ መሰረቱን አጥብቦ፣ አጥብቦ … ባዶ እጁን የቀረዉ ገዥዉ ግንባር ጠብ-መንጃን የብቻ መተማመኛ አድርጎ እስከምን ድረስ ይዘልቃል?!

ዛሬም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተሻለ መንገድ የማዘመን ዕድል በገዥዉ ግንባር እጅ ላይ ነዉ። ለታሪክ የሚበቃ ዕድል እጁ ላይ ያለዉ ገዥዉ ግንባር ሥልጣን እሰከ መቃብር ከሚለዉ መለሳዊ የድርጅት ቀኖና ተሻግሮ ነገን ቢመለከት ለዚህች መከረኛ ሀገር ይበጃል (ከዉስጣዊ ቀዉስ መሻገር እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊ ትሩፋቱን ከገዥዉ ግንባር በተሻለ ማን ይረዳዋል?) አሁን ያለዉን የኢህአዴግ ምክር ቤት የመሰለ ፓርላማ በማፍረስ የብሄራዊ ዕርቅ መድረክ እንዲመቻች፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ በአሸባሪነት የተፈረጁም ሆነ ያልተፈረጁ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ ለያዙ ኃይሎች የሰላም ጥሪ ማድረግ፣ … ብሎም የብሄራዊ አንድነት መንግስት ለማቋቋም የሚያስችሉ ፖለቲካዊ መደላድሎችን መፍጠር የገዥዉ ግንባር የመጀመሪያም የመጨረሻም በጎ እርምጃ ነዉ። ይህን ከማድረግ ይልቅ በማንአህሎኝ የትምክህት መንገዱ በማያዘግም ከህዝብ ጋር ደም መቃባቱን ‹ግፋ በለዉ!› የሚል ከሆነ፤ የቁርጡ ቀን ሲመጣ በማልኮም ኤክስ አንደበት “The chickens [are coming] home to roost” በሚል “You are welcome!” ለማለት ዝግጁ ነን።

ይህችን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ወድቅት ለሊት “It is dangerous to be right when the government is wrong” የሚለዉ ፍርሃት አዘል ምክር በአዕምሮዬ ይመላለስ ነበር። ግና፤ የኢትዮጵያ ነገ የተሸከመዉ መዐት ከባድ ነዉና እየመጣ ያለዉን የበዛ መከራ መጠቆምም ሆነ ከሞት በመለስ መዉጫ ጫፎችን ማሳየት ትዉልዳዊ ጥሪ ነዉ። ይህችን ምክር ለማይቀሉ የገዥዉ መደብ ልሂቃን ግን ወዮ ለዚያች ቀን!!

በሙሉዓለም ገ.መድህን

Received on Tue Aug 23 2016 - 12:45:55 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved