Ethsat.com: ህዝቡ እንደ ሃማስ የከተማ የትጥቅ ትግል ሊጀመር ይችላል ሲል ኢህአዴግ ስጋቱን ገለጸ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam.1_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 24 Aug 2016 00:13:34 +0200

ህዝቡ እንደ ሃማስ የከተማ የትጥቅ ትግል ሊጀመር ይችላል ሲል ኢህአዴግ ስጋቱን ገለጸ

August 23, 2016

watch these:

ESAT Daily News Amsterdam August 23,2016

ESAT Daily News DC Tue 23 August 2016 Ethiopia

ESAT discussion on current affairs

http://video.ethsat.com/?p=27462

ነሃሴ  ፲፯ ( አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ፣ አሁን በሚታየው አካሄድ የአማራ እና የኦሮምያ ክልል ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን  እያጠናከሩ ከመጡ  እንደ ሃማስ መሳሪያ አንግተው ሰፈር ለሰፈር ከመንግስት ጋር የሚታኮሱ ሃይሎች እንደሚፈጠሩ፣ ጥያቄያቸውም ከሰፈር ነፃነት ጥያቄ ወደ አገራቀፍ አጀንዳ ሊያቀየር  ይችላል ሲል የኢህአዴግ የፖለቲካ ደህነነት ክፍል ግምገማውን አቅርቧል።

ብአዴን፣ የጎንደር ህዝብ አመፅ ህዝባዊ መሰረት ይዞ የተደራጀ በመሆኑ በሃይልም ቢሆን መፍታት አልቻልኩም ሲል አስተያየቱን በስብሰባው ላይ አቅርቧል። ኦህዴድም ተመሳሳይ የሆነ ግምገማ አቅርቧል።

ኢህአዴግ የገበሬ ሚሊሻዎችን የመከላከያ ልብስ እያለበሰ ሆቴል ተከራይቶ በመቀለብ በየወረዳው ፀጥታ አስከባሪዎች አድርጎ እያሰማራ ነው፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ለሚሊሺያዎች አዳዲስ መሳሪያዎችን እያስታጠቀ ፤ የመከላከያ ልብስ እያለበሰ ፣ የ ደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ቃል እየገባ በየወረዳ ከተማዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን የገበሬ ሚሊሻዎችን እርሻቸውን አስትቶ ሆቴል ተከራይቶ በመቀለብ ከተሞችን እንዲቆጣጠሩ እና የ ስነ ልቦና ጫና እንዲፈጥሩ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

በጎንደር ወለቃ አካባቢ ወታደሮች የጦር መሳሪያቸውን ጫካ ውስጥ ጥለው መጥፋታቸውን ተከትሎ መትረጌስ እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። የጎንደርን ህዝብ በጥይት እንዲደበድቡ ከአለቆቻቸው ትእዛዝ የተሰጣቸው ወታደሮች ትእዛዙን በመጣስ መሳሪያቸውን ጫካ ውስጥ ጥለው መጥፋታቸውን የተናገሩት ምንጮች ፣ የጦር መሳሪያዎችን ቀበሌው ተረክቦ ወደ ሚሊሺያ ጽ/ቤት ማስገባቱን ገልጸዋል።

አንዳንድ የሰራዊቱ አባላት የወሰዱትን እርምጃ ያደነቁት ምንጮች፣ ሰራዊቱ በሂደት ስርኣቱን በብዛት ይከዳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጻዋል።

በሌላ በኩል ኢህአዴግ አንዳንድ አመራሮችን አስገምግሞ በማበራር የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ አዲስ ስትራቴጂ ነድፏል።

ትላንት በቤተ መንግስት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመፍትሄው ዙሪያ የመከረው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣  የ15 ዓመታትን የኢህአዴግ  ጉዞ በመገምገም፣ ኢህአዴግን በአዲስ እይታ ለህዝብ ለማቅረብ ወስኗል።  ህዝብ የሚቃወማቸውን አመራሮች በማባረር እና በማሰር  የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ የሚያስችል ስራ እንዲሰራ ባለ አርባ ስድስት ገፅ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡

“የፖለቲካ ቀውሶችን ለመከላከል የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ ፣ የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ የእድገት ምዕራፍ የተከፈተበት የሩብ ምዕተ ዓመት የትግልና የድል ጉዞ” በሚል የተዘጋጀውና ስራ አስፈጻሚው ያጸደቀው ሰነድ ለኢሳት የደረሰ ሲሆን፣ በሰነዱ ላይ ግንባሩን የገጠሙት በርካታ ፈተናዎች ቀርበዋል።

ህዝቡን በቁስ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ጥቂት ምንጫቸው ያልታወቁ ሚልየኖረችን ፈጥረናል የሚለው ሰነዱ፣ የብሄር መከፋፈሎች ደግሞየስርዓቱ አደጋ መሆናቸው ተገልጾልናል ይላል።

የኢህአዴግ የ25 አመታት የግምገማ ሰነድ ኪራይ ሰብሳቢነት የስርዓቱን ህልውና እየተፈታተነው

*********************************************************************************

በአማራ ክልል የሚደረገው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ አድማሱን እያሰፋ ነው

August 23, 2016

ነሃሴ  ፲፯ ( አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባህርዳርን ለሶስት ቀናት ጸጥ ረጭ ያደረገው የስራ መቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ወደ ደባርቅ፣ ቆላ ድባ፣ ጯሂትና ጎርጎራ ከተሞች ተሸጋግሮ በጸጥታ ሃይሎችና በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። በገበያው ውስጥ ምንም እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የገበያው ዋና ዋና በሮች ተዘግተው በገበያው ጠባቂዎች ይጠበቃሉ፡፡በተለይ ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ  ግርግር የሚበዛባቸው የገበያው በሮችና የእግረኛ መንገዶች ምንም አይነት ውክቢያም ሆነ እንቅስቃሴ  አይታይባቸውም፡፡ ሁሉም የባህርዳር ነዋሪዎች የህዝባዊ እምቢተኝነቱ አካል የሆነውን የስራ ማቆም አድማ በሙሉ ልቡ ተቀብለው ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡

ዘጋቢያችን እንዳለው ዛሬ ማክሰኞ  በከተማዋ የታየው ለየት ያለ ተግባር የስርዓቱ ወታደሮች ከሁለት ሳምንት በፊት በንጹሃን ላይ በወሰዱት የግፍ ግድያ ጓደኞቻቸውን ያጡ ወጣቶች በቡድን በመደራጀት  በስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉትን ተሸከርካሪዎች ለማስቆም መሞከራቸው ነው፡፡በተለይ በቀበሌ አስራ ሁለት አካባቢ የተሰማሩት ወጣቶች አንድ በተለምዶ ʻአባዱላʼ በሚል የሚጠራ ተሸከርካሪ እንዲመለስ ሲያስጠነቅቁ ፣ ጥሶ ለማለፍ በመሞከሩ የፊት መስታውቱን በመምታት ርምጃ ወስደዋል፡፡ በትላንትናው ምሽትም ቀን ሲሰሩ በዋሉ ባጃጆች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፤የገዥው መንግስት አመራሮች የማይሰሩ ባጃጆችን እንቀጣለን በማለት ሲያስፈራሩ ቆይተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የግል ባንኮች ጠዋት አገልግሎት ለመጀመር ፈራ ተባ በማለት በራቸውን በከፊል በመክፈት ስራ ለመጀመር ቢሞክሩም ተጠቃሚ አላገኙም፡፡ከአምስት ሰዓት በኋላም ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ስራ አቁመዋል፡፡ዛሬም የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በራቸውን ክፍት ቢያደርጉም ከተወሰኑ ኃላፊዎች ውጭ ሰራተኛው እንዳልተገኘ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ፖስታ ቤት ዛሬም አገልግሎት አልሰጠም፡፡ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ከአውቶቡስ መናኸሪያ በስተጀርባ የሚገኙ ʻሽሮ ቤቶችʼና አልፎ አልፎ ሙዝና ብርቱካን የሚነግዱ ኮንቴይነሮች  ብቻ ናቸው፡፡

በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ አባት ለዘጋቢያችን አንደተናገሩት በከተማዋ የሚደረገውን ትግል አባቶችና አዛውንቶች ሊያግዙ ይገባል።

‹‹በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄደው ትግል አባቶችም ተሳታፊ ልንሆን ይገባል፡፡አሁን የስርዓቱ ማንነት ተጋልጧል፡፡ከዚህ በኋላ ወደፊት እንጅ ወደኋላ ማለት አይገባም፡፡ቁርስ ምሳና እራት እንበላ እንደሆን ምሳ ብቻ በመብላት ከህዝብ ጋራ መተባበር አለብን፡፡ህዝቡም በየአካባቢው የሚገኙትን ሰርቶ አዳሪዎች መደጎምና ማገዝ እንጅ ፤የስራ ማቆሙ አድማ እንዲቆም የሚቀሰቅሱ የህውሃት አደርባይ አመራሮችን ድምጽ መስማት የለብንም፡፡ ሁሉም አንድ ከሆነ እኮ ሊወሰድ የሚችል አንድም እርምጃ አይኖርም›› በማለት በወቅታዊው ሁኔታ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

መስተዳድሩ በንግድ ድርጅቶች በሮች ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በማለት ወረቀቶችን እየለጠፈ ቢሆንም፣ ነጋዴዎች ለማስፈራሪያው ቦታ አልሰጡም። መስተዳድሩ በንግድ ድርጅቶች ላይ ቅጣት የሚጥል ከሆነ እርምጃው ከዚህ በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በደባርቅ ዛሬ በተጀመረው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ ደግሞ ፣ የገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች ነጋዴዎች በግዴታ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማስገደድ ሲሞክሩ፣ ከህዝብ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ሁለት ታጣቂዎች በድንጋይ ተመትተው ሆስፒታል ሲገቡ ከሲቪሉ ወገን ደግሞ ሶስት ሰዎች ተጎድተዋል። የከተማው ህዝብ በአንድ ድምጽ በወሰደው እርምጃ፣ ወደ አካባቢው የሚንቀሳቀስ ተሽካርካሪ ቆሟል። በከተማው ውስጥ ተከታታይ የተኩስ ድምጾች እየተሰሙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በቆላ ድባ፣ ጫሂትና ጎርጎራ ከተሞች የሚደረገው አድማ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን፣ በቆላ ድባ ሁለት ወጣቶች መታሰራቸውን ተከትሎ ህዝቡ በአንድነት በመሄድ እንዲፈቱ አድርጓል። በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪም ሆነ የተከፈተ የንግድ ድርጅት እንደሌለ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጎንደርም ተመሳሳይ አድማ ለ2ኛ ጊዜ እንዲጀመር የሚጠይቅ ወረቀት እየተበተነ ነው። ህዝቡ ለተከታታይ ቀናት የሚያቆየውን ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲገዛ ተጠይቋል።

********************************************************************************

በባህር ዳር ከቤት ያለመውጣት አድማ ለሶስተኛ ቀን በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ

August 23, 2016

ኢሳት (ነሃሴ 17 ፥ 2008)

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እሁድ በነዋሪው የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ እንዲያበቃ ቅስቀሳንና ዛቻን ቢያደርግም አድማው ማክሰኞ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

ከተማዋ ማክሰኞች ምሽት ድረስ ሙሉ ለሙሉ ከማኛውም እንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን የተናገሩት እማኞች የባህር ዳር ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ የንግድ ተቋማት ስራቸውን እንደሚጀምሩ ማሳሰቢያዎችን ቢያሰራጭም ነዋሪው እምቢተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ለሶስት ቀን እንዲካሄድ የተጠራው ከቤት ያለመውጣት አድማ ማክሰኞች ያበቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች መንግስት ይፈጽመዋል ያሉትን ግድያና አፈና ለመቃወም የተለያዩ ዕርምጃዎችን በቀጣይ እንደሚወስዱ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የከተማዋ አስተዳደር ነዋሪው የንግድ ድርጅቱን እንዲከፍት ማሳሰቢያዎችን በተደጋጋሚ ቢያሰራጭም የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ለሶስተኛ ቀን ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ሆነው መዋላቸው ታውቋል።

በከተማዋ በቅርቡ የተፈጸሙ ግድያዎችን በመቃወም የባህርዳር ከተማ በራሱ ተነሳሽነት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እሁድ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ አድማ ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ሲካሄድ የቆየው አድማ የተሳካ እንደነበር አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች አድማው የህዝቡ ጥያቄ ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ በተለያዩ ስልቶች ቀጣይ እንደሚሆን አክለው አስታውቀዋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባትን እንዲያገኝና እየተፈጸመ ያለው ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ የተነሳው ህዝባዊ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ተቃውሞ እየቀረበ ይገኛል።

Received on Tue Aug 23 2016 - 16:52:39 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved