በብዙ የጎጃምና የጎንደር አካባቢዎች መንግሥት ፈርሷል፤ የጎበዝ አለቆች ክፍተቱን እየሞሉ ነው
• ባሕር ዳር፣ መራዊና ዳንግላ ከተሞች በጪስ ታፍነው ተኩስ ሲናጡ ውለዋል
• ‹‹በአዴት ከተወለዱ በጤና እያለ አንድስ እንኳ እቤት የዋለ የለም›› የአዴት ሪፖርታዥ
• ከወረታ ከተማ አቅራቢያ ጉማራ ላይ በገበሬውና በትግረው መከላከያ መካከል ከባድ ጦርነት ሲደርግ አድሯል
• ቋሪት፣ አገው ምድር፣ ጋይንት፣ በለሳ፣ አብዛኛው የደበርቅና የጃናሞራ አካባቢዎች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ናቸው
• በአንዳቤትና በፋርጣ የጎበዝ አለቆች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል
ከሙሉቀን ተስፋው
ባሕር ዳር፤ በባሕር ዳር ከተማ በሕዝብ የተጠረውን የቤት ውስጥ አድማ ለማደናቀፍ በሞከሩ የወያኔ አባላትና ቅጥረኛ ባንዳዎች ንብረት ላይ ዐማራው እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ የዐማራው ሕዝብ ቆራጥነቱን በተግባር ያሳየበት ከዛሬ የበለጠ ቀን አልነበረም፡፡ ጠዋት አካባቢ አድማውን ችላ በማለት ሥራ የጀመረ አንድ የከተማ አውቶቡስ ሾፌር መኪናውን ሰባብረው ልጁን እንዲማር መጠነኛ አካላዊ ጉዳት ደርሶበት አሰናበቱት፡፡ ሥራ የጀመረው የንግድ ባንክም ሕንጻ መስኮቶች ተሰባብረዋል፡፡ በሕዝብ አስቀድመው የተለዩ የሕወሓት አባላት እና የዐማራ ቅጥረኛ ባንዳ ሰዎች ስም ዝርዝር አስቀድሞ የተሰራ ሲሆን ተራ በተራ ሲቃጠል ውሏል፡፡ ባሕር ዳር አሁን ከዝናቡ ጋር በጭስ ታፍናለች፡፡ ከቦታው አስተያየቱን እንዲሰጠን የጠየቅነው የከተማዋ ነዋሪ ‹‹የጥይት ሩምታው ይሰማሃል? የቤት ጣራ ላይ ሆኜ ነው የማወራህ አንድ ሁለት… ወደ ዘጠኝ ቤት ሲቃጠል ይታየኛል እኛ ሰፈር እንኳ፡፡ የአምቡላንስና የጥይት ድምጽ እየረበሸኝ ነው›› ሲል የነበረበትን ሁኔታ ገልጦልናል፡፡ ቀበሌ 08 የሚባለው ሰፈር በርካታ ቤቶች የተቃጠሉበት ነው ተብሏል፡፡
በባሕር ዳር በዛሬው የዐማራ ተጋድሎ ቀበሌ 06 ሦስት ዐማሮች ተሰውተዋል፡፡ ቀበሌ 14 ኤፍራታ እሚባለው አካባቢ ደግሞ ለታጋይ ዐማሮች ውሃና ምግብ ለማቅረብ ሲሄዱ የነበሩ እናት ወድቀው መሰዋታቸውን ሰምተናል፡፡ በርካታ ተሸከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን ዐማራው በየሰፈሩ የጎበዝ አለቃዎችን እየመረጠ በመታገል ላይ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ያልተዘጋ መንገድ የለም፡፡ የዐማራ ፖሊስ ሕዝብን በመጠበቅ ያደረገው ተጋድሎ የሚደነቅ መሆኑን ሰምተናል፡፡ በባሕር ዳር ዛሬ የተደረገው ተጋድሎ እጅግ የሚያኮራና ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሕዝቡ የተቆጣጠረበት ሁኔታ እንዳለ ሰምተናል፡፡ የባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በግቢ የዐማራን ተጋድሎ ሲያንጸባርቁ ውለዋል፡፡
ከባሕር ዳር ከተማ 17 ኪሎ ሜትር አካባቢ ያለችው የመሸንቲ ከተማና የይባብ ኢየሱስ ቀበሌም የዐማራ ተጋድሎ ከዋለባቸው ቦታዎች ውስጥ ናቸው፡፡ መሸንቲ ያለው የሕወሓት አባል የድንጋይ ጠጠር ማምረቻ ፕላንትም ተቃጥሏል ተብለናል፡፡
መራዊ፤ በመራዊ ከተማ የዐማራ ሕዝብ ለተጋድሎ የወጣው በጠዋት ነበር፡፡ የሜጫዋ መራዊ ከተማ እንደ ባሕር ዳር ሁሉ በጢስ ታፍና ውላለች፡፡ ለተጋድሎ የወጣው የዐማራ ሕዝብ ከጉያው ተሸጉጠው ሲያንገላቱት የነበሩትን የሕወሓት አባላትና ቅጥረኛ ባንዳዎች ሀብትና ንብረት ተለቅሞ ተቃጥሏል፡፡ የገብረ ሥላሴ ኃይለማርያም ክሊኒክና ፋርማሲ፣ የገ/ድህን ክሊኒክ፣ ፒታ ዳቦ ቤት፣ ኃይሌ ፎቅ፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ ብአዴን ጽ/ቤትና በርካታ የሰላዮች መኖሪያ ቤትና ንብረት ወድሟል፡፡ የዐማራ ሕዝብ ከተማዋን ይህ ሪፖርት እስከተሠራበት ጊዜ ድረስ ተቆጣጥሯት ይገኝ እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡
አዴት፤ የይልማና ዴንሳዋ አዴት ከተማ በዐማራ ተጋድሎ ስትናጥ ውላለች፡፡ ከአዴት ከተማ የሚገኘው ሪፖርተራችን የላከልን መረጃ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ የአዴት ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ወያኔን ሲቃወም ዋለ፡፡ በአዴት ከተወለዱ በጤና እያለ አንድስ እንኳ እቤት የዋለ የለም፡፡ ከወጣት እስከ ሽማግሌ፣ ሴትና ወንድ፣ እስላምና ክርስቲያን ሁሉ በቁጣ ገንፍሎ ወጥቷል፡፡ ሰልፉን የሰሙ የይልማና ዴንሳ አርሶ አደሮችም ከወንዳጣ ድረስ እየመጡ በወኔ ተጋድሎውን ተቀላቅለው ውለዋል፡፡
‹‹ወያኔ ሕወሓት ሌባ ነው፤ ቅጥረኛው ብአዴን አይወክለንም፤ ድንበራችን ተከዜ ነው፤ ወልቃይት ዐማራ ነው፤ በዐማራ ላይ የሚደርሰው ጭቆና ይቁም፤ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ይቁም፤ …›› እና ሌሎችም መፈክሮች ሲሰሙ ውለዋል፡፡ የዐማራው ሕዝብ ወደ ባሕር ዳር በኩል 2 ኪሎ ሜትር መንገድ በመጓዝ አቦላ ተራራ አካባቢ ያለውን መንገድ መዝጋት ቅድሚያ የሠጠው መርሃ ግብር ነበር፤ ይህም የወያኔን አልሞ ተኳሾች እንዳይመጡ መንገዱን ማበላሸት ሲሆን ይህን የሰሙት የባሕር ዳር አናብስት ወጣቶች ሰባታሚት አካባቢ መንገዱን ጠርቅመው በመዝጋት የአዴት ዐማሮችን ተባብረዋል፡፡ ሰልፈኞች ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ወጣቶችን ሰብረው በመግባት አስፈትተዋል፤ የአስተዳደር ቢሮው ተሰባብሯል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ኮምፕዩተሮች በእሳት ጋይተዋል፡፡ አካለ መንግሥቱ የሚባለው የወያኔ ቅጠረኛ ዐማሮችን ሲሰልልና ሲያሰቃይ የሰነበተ ሲሆን የሕንጻ መሣሪያ መደብሩ ወድሞበታል፡፡
ክሊኒክና ፋርማሲ በመክፈት የአዴት ዐማራን ጊዜው ባለፈበት መድኃኒት ሲበዘብዙና ሲሰልሉ የነበሩት የገ/እግዚአብሔር ቤተሰቦች ከሳምንታት ቀደም ብለው ከአዴት ቢወጡም ንብረታቸውና መኖሪያ ቤታቸው በእሳት ከመጋየት አልዳነም፡፡ የገ/እግዚአብሔር ልጅ የሆነው አቶ አማኑኤል ዐማሮችን በሽጉጥ ሲያስፈራራ የሰነበተ ሲሆን ዛሬ ተፈልጎ የገባበት ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የወያኔ ቀኝ እጅ የሆኑት የሃይማኖት አባቶች ሰልፉን ለመገላገል ቢገቡም እናንተን አንሰማም ብሎ አሳፍሮ መልሷቸዋል፡፡ ይልማና ዴንሳ በህዝብ ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ ለዘጋቢያችን ምስጋና ይድረሰው፡፡
ዳንግላ፤ የአገው ምድሯ ዳንግላ ከተማ የዐማራን ተጋድሎ የተቀላቀለችው ትናንት ነበር፡፡ ትናንት ነሃሴ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 1፡00 ጀምሮ የዳንግላ አገው ዐማራ ሕዝብ ለተጋድሎ ወጣ፡፡ የዐማራውን ጥያቄዎች አንግቦ ወደ ወኅኒ ቤቱ አቅጣጫ ሲሄድ መዘጋጃ ቤት አካባቢ ሲደርስ የወያኔ አባል የሆነው የመዘጋጃ ቤት ሠራተኛ አቶ ሀብተወልድ ወደ ሕዝብ በመተኮስ ሁለት ሰዎችን አቆሰለ፡፡ ሕዝብ ተቆጣና የአቶ ሀብተወልድን ቤት ሙሉ በሙሉ አቃጠለው፡፡
ወደ መሃል ከተማ ሲመጣ አንድ ቅጥረኛ የሆነ ያረጋል የሚባል ፖሊስ የዳሸን ቢራ ማስታወቂያን ከሚቀዱት የአገው ዐማራ ወጣቶች ላይ ጥይት አርከፈከፈ፡፡ ፖሊሱ የቤቱን አጥር ጉድብ ይዞ ሁለት ሰዎችን ገደለ፡፡ ከሕዝብ ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ ጥይት ጨረሰ፡፡ ሕዝቡ ሊይዘው ሲል ጎረቤቱ አንድ ካዝና ጥይት ሲሰጠው አናብስቶቹ አዩት፡፡ ባንዳው ጎረቤቱ ተጨፍጭፎ ተገደለ፡፡ ፖሊሱ ቢያመልጥም ቤቱ ከመቃጠል አላመለጠም፡፡ ይህ ሙሰኛ ፖሊስ መኖሪያ ቤት ውስጥ 50 ኩንታል ስኳርና 20 ጀሪካ ዘይት ተደብቆ ተገኘ፡፡ ሁሉም ንብረት አብሮ እንዲወድም ተደረገ፡፡ መኪናም ነበረችው፤ ወደመች፡፡
ዳንግላዎች ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ ነሃሴ 23 ቀን ጠባ፡፡ ዳግም ለተጋድሎ ተሰለፉ፡፡ ከዚያም ዳንግላ ከተማ ከክረምት ጉም እኩል የእሳት ጭስ አፈናት፡፡ የህወሓት አባላትና የቅጥረኛ ባለሥልጣናት ቤት ሙሉ በሙሉ ወደመ፡፡ ከተማዋም በሕዝብ ቁጥጥር ሥር ሆነች፡፡ የከንቲቫው (አቶ ሙላት እሸቴ) በሙስና የተከማቹ ሦስት ቤቶች፣ የጥቃቅን ኃላፊው አቶ ያለው ዘለቀ፣ የብአዴን ኃላፊው አቶ ዳዊት ብርሃኑ፣ የማዘጋጃ ኃላፊው አቶ መንግሥቴ ቢተው፣ የትራፊክ ፖሊሱ አቶ አይተነው፣ የደኅንነቱ አቶ ይመኑ፣ እና ሌሎችም ዛሬ ወደ አመድነት ከተለወጡ በቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የአጋዚና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋን ቢወሯትም ሕዝብን ግን እስካሁን ማሸነፍ አልተቻለም፡፡