ግንቦት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ መከላከያ ከፍተኛ የሰራዊት አዛዦች በአዲስ አበባ ዘመናዊ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶችን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ መገንባታቸውን የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች በኢሳት ሲለቀቁ ቆይተዋል። በአሁኑ ሰአት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚገነቡ ዋና ዋና የሚባሉ የህንጻ ግንባታዎች በህወሃት የፖለቲካ መሪዎች፣ በህወሃት ነባር ታጋይና አሁን ከፍተኛ የጦር ኣዛዦች በሆኑ ግልሰቦች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጥቅም ቁርኝት የፈጠሩ “ባለሃብቶች” የተያዘ ነው። በዚህ ረገድ የአገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት የሚመሩት እና ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ ከፍተኛውን ስልጣን በመያዝ አገሪቱን የሚመሩት ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በባለቤታቸው አማካኝነት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ግዛት እየመሰረቱ ነው።
ወ/ሮ ሶፍያ ይባላሉ። የ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ባለቤት ናቸው። ጄ/ል ክንፈ ዳኘው እና ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በሚስቶቻቸው አማካኝነት በጋብቻ ተሳስረዋል። በጋብቻ መተሳሰር ብቻ ሳይሆን ሁለቱም በረጅም ጊዜ የስልጣን እድሜያቸው በአገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ ግዛት እየመሰረቱ ነው። ጄ/ል ክንፈ ዳኘው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወይም ሜቴክ ስራ አስኪያጅ ናቸው። ሜቲክ ደግሞ በቅርቡ 10 የስኳር ፕሮጅክቶችን እገነባለሁ ብሎ ከስኳር ልማት ድርጅት ጋር የኮንትራት ስምምነት ካደረገ በሁዋላ ፣ ፕሮጀክቶቹን ለመስራት ባለመቻሉ ከ 77 ቢሊዮን ብር የሃገር ሃብት ያወደመ ድርጅት ነው። ሜቴክ በቀድሞው እና በኢህአዴግ መንግስት የተገነቡ ፋብሪካዎችን አጣምሮ የሚያስተዳድር ድርጅት ሲሆን፣ በስሩም ጋፋት አርማመንት ኢንዱስትሪ፣ ሆሙቾ ኮሚኒኬሽን ኢንዱስትሪ፣ ሃይቴክ ኢንዱስትሪ፣ ደጀን አቪየሽን እንዱስትሪ፣ አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ አዳማ እርሻ ኢንዱስትሪ፣ ኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ፣ ህብረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ ብረታብረትና ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፣ አቃቂ ቤዚክ ሜታል እንዱስትሪ፣ ሎኮሞቲቭ ንኡስ እንዱስትሪ፣ ነዳጅና ፕሮፔላንትን ንኡስ እንዱስትሪ እንዲሁም ኢትዮ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የተባሉ ድርጅቶችን ያስተዳድራል። መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ከሚያስገነባቸው የብረታብረት ስራዎች ውስጥ አብዛኛውን ፕሮጀክት የሚወስደው ሜቲክ፣ የወሰዳቸውን ፕሮጀክቶች በወቅቱ ካለማስረከቡም በላይ ስራዎች ጥራት የላቸውም። ለማዳበሪያ ግንባታ፣ ለመብራት ሃይል፣ ለአባይ ግድብ ግንባታና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች መቴክ የወሰደውን ድርሻ ባለመወጣት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ይቀርቡበታል።የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት በሜቴክ ላይ ተደጋጋመ ቅሬታዎች ከአገር ተቆርቋሪ ዜጎችና ከመንግስት መስሪያ ቤቶች ሃላፊዎች ቢቀርብለትም አንድም እርምጃ መውሰድ አልቻለም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን በጀኔራል ሳሞራ የኑስና በጄ/ል ክንፈ ዳኘው መካከል ያለው ቤተሰባዊ ትስስር እና የፈጠሩት ግዙፍ የቢዝነስና የደህንነት ግዛት ነው።
ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በባለቤታቸው በወ/ሮ ሶፍያ አማካኝነት በገነቡት የአስመጪና ላኪ የንግድ ድርጅት በሜቴክና በመከላከያ ስም ያለ ቀረጥ ከውጭ ያስገባሉ። በሚያገኙትም ትርፍ በአዲስ አበባ እና በትግራይ በርካታ የሪል ስቴት ግንባታዎችን አካሂደዋል። ጄ/ል ሳሞራ በባለቤታቸው ስም ካስገነቡዋቸው ግዙፍ የንግድ ማእከሎች መካከል ቄራ አካባቢ ገብሬል ቤተክርስቲያንን አለፍ ብሎ የሚገኘው ሶፊያ የንግድ ማእከል Sofina Mall የተባለው አንዱ ነው። ሶፊያ ሞል ለንግድ እንቅስቃሴ አመቺ በሆነ ሰፊ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን በውስጡ ባንኮች፣ የመድህን ድርጅቶች፣ ካፌዎች፣ የልብስና የጫመ መደብሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የፎቶ ስቱዲዮዎች፣ የመኪና አከራይ ድርጅቶች ፣ ኢትዮ ቴልኮምና ሌሎችም በርካታ ደርጅቶች ተከራይተውታል። ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ( ፓርኪንግ) ያለው ይህ የንግድ ማእከል በየወሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለጄ/ል ሳሞራና ባለቤታቸው ያስገባል። የህንጻውን የውስጥ ክፍል በተመለከተ ወኪላችን የቀረጸው ይህን ይመሰላል ። ጄ/ል ሳሞራ ወርሃዊ ደሞዛቸው ከ6 ሺ ባይበልጥም መንግስት ልዩ ጥበቃ የሚያደርግበትና ከ200 ሺ ብር በላይ ወርሃዊ ኪራይ የሚከፈልበት ዘመናዊ መኖሪያ ቤት አላቸው።