ኢሳት (ግንቦት 26 ፥ 2008)
June 3, 2016
ESAT Daily News Amsterdam June 03, 2016
በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በአሸባሪነት ተወንጅለው በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙት እነ አቶ በቀለ ገርባ ጫማ ሳያደርጉ በሌሊት ልብስ ፍ/ቤት ቀረቡ።
ቁምጣና ከነቴራ ለብሰው ባዶ እግራቸውን ችሎት ለመቅረብ የተገደዱት ልብሶቻቸው በወህኒ ቤቱ ሃላፊዎች ስልተወሰደባቸው እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
አርብ ግንቦት 26 ፥ 2008 በሌሊት ልብስ እና በባዶ እግራቸው ችሎት የቀረቡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ሌሎች የአመራር አባላት አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጉርሜሳ አያና እንዲሁም አቶ አዲሱ ብላላን ጨምሮ በአጠቃላይ 22 ሰዎች መሆናቸውን ከተማሪዎች ቤተሰቦች ለመረዳት ተችሏል።
አርብ ግንቦት 26 ፥ 2008 ከፍተኛ ፍ/ቤት ባለባቸው ቀጠሮ ተቃውሞኣቸውን ለመግለጽ ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደችሎቱ ለማምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ፍተሻ በማድረግ ልብሶቻቸውን በመውሰዳቸው በሌሊት ልብስ ችሎት የቀረቡት እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ከጥቁር ልብስ ባሻገር ሌሎች ልብሶቻቸውም መወሰዳቸው ተመልክቷል።
አቶ በቀለ ገርባ ከአምስት አመት በፊት በአሸባሪነት ተወንጅለው የተፈረድባቸውን እስራት አጠናቀው በወጡ በወራት ጊዜ ውስጥ ተመልሰው በአሸባሪነት ተወንጅለው መታሰራቸው ይታወቃል።
በህዳር ወር 2008 የተቀጣጠለውን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ምሁራንና አክቲቪስቶች መታሰራቸው ይታወቃል።