በዚህ በወርሃ ግንቦት ከጥቂት በላይ ጆሮ የሚጎትቱ ዜናዎች መስማታችን አልቀረም። የኦሮሚያ አመፅ በገጠር ከተሞች መቀጠሉ፣ የቦሌ አለማቀፍ አይሮፕላን ጣቢያን ስም ለመቀየር መታሰቡ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የስራ ፍለጋ ማመልከቻ ማስገባቱ፣ የህወሃት የፀጥታው መስሪያ ቤት ባልደረቦች በውስጥ ሽኩቻ መናጣቸው፣በርካታ የስርአቱ ደጋፊዎችና ቤተሰቦቻቸው ባለመረጋጋት ስሜት የሽሽት ጉዞ መጀመራቸው፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ተባብረው የኢትዮጵያን መንበረ ስልጣን እንዲረከቡ ግፊት በመደረግ ላይ መሆኑ እና ሌሎችም በወርሃ ግንቦት ከተሰሙ አበይት ዜናዎች መካከል ናቸው። አንዳንዶቹን ርእሰ ጉዳዮች በጨረፍታም ቢሆን ፈታ አድርጎ ማየቱ አስፈላጊ ነው። በርግጥም ይችን ወግ ለመክተብ ኮምፕዩተር ከመክፈቴ በፊት የኦሮሚያ አመፅ መቀጠሉን እየሰማሁ ነበር። ምእራብ ሸዋ ጊንጪ ላይ፤ ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ላይ፤ ሆሮጉድሩ ኮምቦልቻ ላይ፣ በአምቦ፣ በሃሮማያ፣ በአዋሮ፣ በምእራብ ሃረርጌ እና በሌሎችም አካባቢዎች በወያኔ ሰራዊት እና በኦሮሚያ ወጣቶች መካከል ግጭት እየተከሰተ ሰዎች መገደላቸው ቀጥሏል። መሞትን የናቀ ህዝብ በመጨረሻ እንደሚያሸንፍ ወያኔ ከራሱ የአመፅ ልምድ ያውቃል። የስልጣን ጉዳይ ሆነበትና ግን ጊዜ ለመግዛት መብት ጠያቂዎችን ማፈንና መግደሉን ቀጠለ።
ከአመታት በፊት ናይሮቢ ላይ ያገኘሁዋቸው አንድ የደምቢዶሎ ሽማግሌ ያወጉኝ ትዝ ይለኛል።
“OLF ምክር አይሰማም! ወያኔ ደግሞ እውር ነው!” አሉኝ።
“ምን ማለትዎ ነው አባት?”
“ምን ማለቴ መሰለህ? OLF እየሞተም እየታሰረም በወያኔ መንግስት ውስጥ መቆየት ነበረበት። የህዝብ ድጋፍ ስላለው ወያኔን ማስጨነቅ የሚችለው የመንግስት መዋቅር ውስጥ በመቆየት ነበር። ወያኔ ተረጋግቶ አገር እንዳይመራ ማድረግ ይቻል ነበር። OLF ግን ትልቁን የህዝብ ጫካ ትቶ የዛፍ ጫካ መረጠ። ኦቦ ሌንጮን አጊኝቼ ለራሱ ነግሬው ነበር። አልሰማኝም። ይኸው OLFን ተከትለን እኛም ተሰደናል። ‘ወያኔ እውር ነው’ ስል ደ’ሞ ምን ማለቴ መሰለህ? OPDO በOLF ተሞልቶ ሳለ፤ ቦረና ላይ በሶሎሎ፣ ባሌ ላይ በቤልቱ፣ ሃረርጌ ላይ በቦኬ፣ ወለጋ ላይ በጊዳሚ OLFን ፍለጋ ይንከራተታል።” በርግጥ በወያኔ የዜና ማሰራጫዎች OLF መተኛቱ፣ መከፋፈሉ፣ ከዚያም አልፎ ሞቶ መቀበሩ ተደጋግሞ ተነግሮን ነበር። ባለፈው የግንቦት ወር መግቢያ ላይ OLFን ጨምሮ አራት የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች ጥምረት መመስረታቸው ትኩረት የሳበ ዜና ለመሆን በቅቶ ነበር። እነ አቦማ ምትኩ ባጭሩ ሲቀጩ ሃላፊነቱን ወስደው OLFን የተረከቡት ሰዎች ተኮራርፈው መክረማቸው በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቅሬታ ማሳደሩ አልቀረም ነበር። የፖለቲካ ድርጅት መሪዎቹና ምሁራኑ በሰንካላ ምክንያት ልዩነታቸውን ሲያበዙ ህዝቡ ቀድሟቸው በመገኘት ትምህርት ሲሰጣቸው ቆይቷል። ጥምረቱ በህዝብ ግፊት የተፈፀመ እንደሆነ ግልፅ ነው። ህዝብን ማዳመጥ የፖለቲከኞች አባጫዳ ሊሆን እንደሚገባ ሲነገር የኖረ ነው።
ያም ሆኖ የአራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጣመር መነሻ በበቂ አልተገለፀም። የኦሮሚያ የፖለቲካ ሃይሎች ኢትዮጵያን እንዲመሩ የሚመኙ ወገኖች ግን ጅማሬውን ሩቅ ተመልካች ሲሉ አሞግሰውታል። በርግጥ በዚህ ጥምረት ውስጥ የምእራባውያኑ ተሳትፎ ምን ያህል እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም። የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በተግባር ጭምር መጣመር ከቻሉ የአካባቢው ጠንካራ ሃይል መሆን የማይችሉበት ምክንያት የለም። ርግጥ እንዲህ ባለ ሂደት ድብቅ አጀንዳዎች ሊኖሩ ይችላሉ። መፍትሄው ነቅቶ መጠበቅ እንጂ አንድነትን መሸሽ ሊሆን አይችልም። የኦሮሞ ፖለቲከኞች በዚህ ወሳኝ ወቅት በኢትዮጵያና በአፍሪቃ ቀንድ ደረጃ ተሰሚነት ሊኖራቸው የሚችለው በቅድሚያ የውስጥ ሽኩቻቸውን ቀንሰው በአንድ ልብ መጓዝ ከቻሉ እንደሆነ ከደርዘን በላይ መጣጥፎች ለንባብ በቅተዋል። ይሳካላቸው ይሆን? ወይስ ከነገ ወዲያ “ዳቦ ተቆረሰ – ጨዋታው ፈረሰ” ይሆናሉ? በአዲሳባ በምእራባውያን አገራት ኤምባሲዎች የሚሰሩ ወይም ዲፕሎማቶችን የሚያማክሩ በአብዛኛው የአማራ ልሂቃን መሆናቸው ይታወቃል። በቅርቡ ያየሁዋቸው ሰነዶች እንደጠቆሙኝ የአማካሪዎቹ ምክሮች በአብዛኛው ከኦሮሚያ አመፅ በሁዋላ “ጊዜ ያለፈባቸው” ተብለው ወደ መጋዘን ተልከዋል። አማካሪዎቹ ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ስለ ፌደራል ስርአቱ ደካማ ጎን ሲያቀርቡ የነበረው መረጃ ከኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ጋር ያልተስማማ ሆኗል። አማካሪዎቹ ወይም ጥቆማ ሰጪዎቹ የሚያመጡት መረጃ ወደ መጋዘን ከመላኩ በፊት፣ “የውስጥ ፍላጎታቸውን ብቻ የሚያንፀባርቅ፤ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን እውነታ ያላካተተ” ተብሏል። በመቀጠልም አውሮፓውያኑ መረጃዎችን በቀጥታ ከኦሮሞዎች ለማግኘት ሙከራ አድርገዋል። በዘበኝነት እና በአትክልተኛነት ከሚሰሩ ኦሮሞዎች ጀምሮ፤ እስከ ኦሮሞ ልሂቃን፣ እስከ አባ ገዳዎች፣ እስከ ቃሉዎች፣ እናቶችና ሽማግሌዎች ድረስ አጥኚዎችን በመላክ በተደረገ አጭር ጥናት እውነቱን እንዲያውቁ እንዳስቻላቸው በሪፖርታቸው ገልፀዋል። ማለትም ማስተር ፕላኑን ከመቃወም እና ከኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ባሻገር የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄና ዝንባሌ ለማወቅ ችለዋል። የዚህ መረጃ ትልቁ ፋይዳ የኦሮሞ ወጣቶች ጥያቄና ፍላጎት ትኩረት መሳብ መቻሉ ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ወጣቶች ከወቅታዊ ንቃታቸው፣ መደራጀት ከመቻላቸው፣ በህዝብ ብዛት አብላጫ ከመሆናቸው አንፃር ኢትዮጵያን ጠቅልለው ስለመምራት እንዲያስቡ፤ ኢትዮጵያዊነትን እንደማንነት እንዲቀበሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲመክሩ አስገድዷቸዋል። የአውሮፓውያኑ ሪፖርት አዲስ አበባ ከተማ ሊስተካከል በማይችልበት ደረጃ ስለ መበላሸቱ በእግረ መንገድ ገልፆአል። የአሮጌ መኪናዎች ጭስ የአዲሳባን አየር ክፉኛ በክሎት በአዲሳባ የሚወለዱ ልጆች ለአስም በሽታ በመጋለጥ ላይ መሆናቸውን ጭምር አስፍሯል። ሪፖርቱ በዋና ነጥቡ የጠቀሰው የኢህአዴግ ስርአት በመንግስት ቢሮ ውስጥ የመቆየት አቅሙን ስለማጣቱ ነው። የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰባሰብ ከዚህ ከምእራባውያን ግምገማ ጋር ስለመያያዙ የሚጠቁም መረጃ የለኝም። በቁርጠኛነት ለለውጥ የተነሱት የኦሮሞ ወጣቶች አማራጭ ሃይል ሆነው ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን እንዲረከቡ መንገድ መክፈት እንደሚገባ ግን ሪፖርቱ በአፅንኦት አስምሮበታል። በተጨማሪ ሪፖርቱ “የህወሃት አመራር በአማራ ልሂቃን ላይ ያለውን ንቀት” ይጠቁማል። አማሮች በአማራነትም ሆነ በኢትዮጵያዊነት ጠንክረው መደራጀት አለመቻላቸውን፣ ወደፊትም ሊደራጁ ስለመቻላቸው እንደሚያጠራጥር፣ በመንግስት ስራ ላይ ያሉ አማሮች የህወሃት አለቆቻቸውን ንቀት መለማመዳቸውን ፅሁፉ በጥቅሉ ያነሳል። ንቀቱን በተመለከተ ከዚህ በላይ ዝርዝር ነገር አላቀረበም። ይህ ጥቅል ጥቆማ ትኩረቴን ስለሳበው፣ “አማራን የመናቅ” ዝንባሌ ላይ ጥቂት መነካካት መረጥሁ። በቅርቡ ለእይታ የበቃ የአማርኛ የዘፈን ክሊፕ ስመለከት በዘፈኑ ውስጥ፣ “ነብር አይኑን ታሞ – ድመት ልምራህ አለችው” የሚል ቁጭት አዘል ስንኞች ሰምቼ ተገርሜ ነበር። አይኑን የታመመው የነብሩ ምሳሌ አማራ ሲሆን፤ ድመቷን ወክሎ የቀረበው ደግሞ ወያኔ ይመስላል። እንደ ድምፃዊው ያሉ ፖለቲከኞች ተጨባጩን እውነት በግልፅ መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። ተጨባጩን እውነት ተረድተው፤ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ ካልታገሉ ድመቷ አይነ በሽተኛውን ነብር ገደል ልትጨምረው እድል ታገኛለች።በውነቱ ከነብር ፊት እንደ “ድመት” ወይም እንደ “ፍየል” እየተመሰለች በአማራ ድምፃውያን የሚዘፈንባት ህወሃት “ነብሩን” እንዴት እንደምታየው በትክክል መገንዘብ ይገባል። የህወሃት አመራር ላለፉት 25 አመታት “ነብር” የተባለውን ወገን ያስተዳደሩት ከንቀት ጋር ነው። ምእራባውያኑ ይህንን በትክክል አስቀምጠውታል። በህወሃት አጠራር “ትምክህተኛው የአማራ ልሂቅ” የወያኔን ንቀት በጊዜ ሂደት መለማመዱን ለማሳየት ጥቂት ማስረጃዎችን መጥቀስም ይቻላል። ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ከግንቦት ሰባት ጋር በመተባበር ወያኔ ላይ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሲዘጋጅ ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል። ካሰሩት በሁዋላ “ሽንታም አማራ!” እያሉ እየሰደቡ በቡጡ ሲደበድቡት እንደነበር ተናግሯል። ኢሳት ቴሌቪዥንም ይህን ዘግቦታል። መረጃው በኢሳት ቴሌቭዥን ሲተላለፍ መላው የአማራ ህዝብ በቁጣ አገር ምድሩን ያናውጠዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። በወቅቱ ጋዜጠኛ ብዙ ወንድማገኝ ብዙ ህዝብ በተሰበሰበበት ፓልቶክ ላይ ቀርባ፣
“ወያኔዎች ከዚህ በላይ ምን ይበሉን!? ምን እስኪያደርጉን ነው የምንጠብቀው? አዋረዱን! ናቁን!! ልክ የሚያገባቸው ወንድ የለንም ማለት ነው?” እያለች እንባ እየተናነቃት ብትጣራም ቁጣ ሊቀሰቀስ አልቻለም። በዚህ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ስንነጋገር የተግባባንበት ነጥብ ወያኔን የሚቃወመው ሃይል በአግባቡ ያለመደራጀቱን ነበር። በርግጥም ያልተደራጀን ህዝብ በቃላት ማዋረድ ብቻ ሳይሆን አስቴር አወቀ እንዳቀነቀነችው፤ ቢጭኑት አህያ – ቢለጉሙት ፈረስ ነው። በአንፃሩ ወያኔ እንዲህ አማራ ላይ እንደፈለገው ለማላገጥ የሚደፍረው በጥብቅ መደራጀቱን ስለተማመነ ነው። ድርጅት ሃይል ነው። ካልተደራጀህ የህዝብ ቁጥርህ ቢከመር፣ የተማረ ሃይልህ ሞልቶ ቢተርፍ፤ ከበርቴህ ቢበዛ ምንም ዋጋ የለህም። ዞሮ ዞሮ የግለሰቦች ጥርቅም ብቻ ነህ። የሸንኮራ አገዳ እግር ነህ። ማንም እየመጣ ሊያጭድህ ይቻለዋል። የኦሮሚያ አመፅ ለወራት መቀጠል የቻለውም የተደራጀ አመራር ስላገኘ ነው። የኦሮሚያን አመፅ ቄሮ መራው ወይም ጃዋር መሓመድ መራው እሱ አይደለም ጉዳዩ። የኦሮሞ ወጣቶች ተደራጅተው በአንድ ማእከል በመመራት ላይ መሆናቸው ግን እውነት ነው።ወያኔ በትግሉ ጊዜ መቐለ ከተማ ገብቶ ከደርግ እስር ቤት ውስጥ 1500 እስረኞችን ፈልቅቆ ይዞ መውጣት የቻለው በጥብቅ የተደራጀ ሃይል መሆን በመቻሉ ነበር። በአንድነት ስም የተደራጁ ፖለቲከኞች አዲስአበባ ከተማ የደጋፊያቸው ዋና ማእከል መሆኑን እየተናገሩ እንዴት አንዳርጋቸው ፅጌን ወይም እስክንደር ነጋን ከእስርቤት ለማስለቀቅ ሳይሞክሩ ቀሩ? ብርቱካን ሚደቅሳን ጨለማ ቤት ውስጥ ዘግተው ሲያሰቃዩዋት በሚሊዮናት የሚገመተው የብርቱካን ደጋፊ እንዴት ዝም ብሎ አየ? ወያኔ እንደሚለው ልብ ማጣት ወይም ወኔ ማጣት አይመስለኝም። በጥቅሉ ፈሪ ወይም ጀግና የሚባል ህዝብ የለም። ችግሩ አለመደራጀትና መሪ ማጣት ነው። ብቅ የሚሉትን በመዶሻ መኮርኮም ራሳቸውን “የአንድነት ሃይል” እያሉ የሚጠሩ ወገኖች የፖለቲካ ባህል ሆኖአል። እነ አንዳርጋቸው፣ እነ እስክንድር፣ እነ አንዷለም እንደ እረኛው ሙሴ ወገናቸውን ሊመሩ ተነሱ። መንገድ ላይ ጠብቆ ወያኔ አፈናቸው። ደጋፊያቸው ከንፈሩን ከመምጠት ያለፈ የሚያደርገው ነገር ከሌለ፣ መሪ የመፍጠር እድሉ እየቀነሰ እንደሚሄድ ማወቅ አለበት። ጥንታዊው መንዜ ሲትርት “ፊተኛውን በምን ቀበርከው?” ይል ነበር።
ወደተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና ወያኔ በትግሉ ጊዜ “ተጋዳላይ ትግራይ – ዓሻ አምሃራይ” (ትግራይ ታጋይ – አማራ ሞኝ) በሚል ዘፈን ተዋጊዎቹን ይቀሰቅስ ነበር። በዚህ ዘፈን እየተቀሰቀሱ አዲስአበባን የተቆጣጠሩ የገበሬ ካድሬዎች፤ የተገነቡበትን ፕሮፓጋንዳ እንደእውነት አምነው ቀጠሉ። “አማራ ሞኝ እና ፈሪ ነው!” የሚለውን የጦርነት ወቅት ቅስቀሳ የአመራር አባላቱ ጭምር ለፕሮፓጋንዳ አገልግሎት የተነገረ መሆኑን ረስተው እንደ እውነት ሲያንፀባርቁት ተሰምተዋል። ለዚህ አባባል ጄኔራል ሳሞራ ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል።
አንድ ጊዜ ሰንገዴ ተብላ የምትታወቅ የኢህዴን ክፍለ ሰራዊት ከOLF ጋር ውጊያ ገጥማ ተሸነፈች። መሪዋ ተፈራ ካሳ የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር። በዚያን ጊዜ ገና የተዋሃደ ሰራዊት አልተቋቋመም። ሰንገዴ በOLF ተሸንፋ ከተበታተነች በሁዋላ ጄኔራል ሳሞራ በህይወት የተረፉትን ወታደሮችና መሪያቸውን ለግምገማ ሰበሰበ። እንዴት ሽንፈቱ ሊከሰት እንደቻለ ሰፊ ግምገማ ከተደረገ በሁዋላ ሳሞራ በጣም ስለተበሳጨ፣
“ሽንፈት የተከሰተው ተፈራ ካሳ ፈሪ ስለሆነ ነው። ችግሩ ይሄ ነው።” ሲል ይደመድማል።
መሪያቸው ፈሪ የተባለባቸው የሰንገዴ ክፍለ ሰራዊት ታጋዮች ከጫፍ እጫፍ አጉረመረሙ። “እንዴት እንዲህ ትናገራለህ?” አይነት ማጉረምረም እየቀጠለ ሄደ። በስብሰባው የህወሃት ካድሬዎችም ስለነበሩ ሳሞራ ንግግሩን እንዲያርም ጠየቁት። ሳሞራ ግን ጭራሽ ባሰበት።እንዲህ አለ፣
“እውነቱን መስማት ከፈለጋችሁ ልጨምርላችሁ! ሰንገዴ ክፍለሰራዊት ራሷ ፈሪ ናት!!
በዚህ ጊዜ አዳራሹ በጩኸት ተናወጠ። የእጅ መወናጨፍ ታየ። ሳሞራን በሃይለቃል ተቃወሙ። የህወሃት ካድሬዎችም ሳሞራን በመሄስ ሰራዊቱን ይቅርታ እንዲጠይቅ ተጫኑት። ሳሞራ የወረደበትን ሂስ ሁሉ በፈገግታ ሲሰማ ቆየና እንደገና ማይክራፎን ያዘ። እናም ይቅርታ ይጠይቃል ተብሎ ሲጠበቅ እንዲህ አለ፣
“እውነት ነው የተናገርኩት። ልጨምርላችሁም እችላለሁ። አማራ ራሱ በተፈጥሮው ፈሪ ነው!!”
በዚህ ጊዜ ግን ከፍተኛ ሳቅ አዳራሹን ሞላው። የተቆጣ አልነበረም።
ሳሞራ በልጅነቱ ህወሃትን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ በዚሁ መንገድ የተገነባ ነበርና ከዚህ እምነቱ በቀላሉ ሊላቀቅ አልቻለም። “አማራ ካልመራት ኢትዮጵያ አገር ልትሆን አትችልም።” የሚሉ ወገኖችም እንደ ሳሞራ በተቃራኒው በውሸት ፕሮፓጋንዳ የተገነቡ ናቸው። ልዩነት የላቸውም። እንዲህ አይነቱን ግንባታ በትምህርት ለመለወጥ አዳጋች ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም ስልጣን ሲይዝ የተማሩና ያነበቡ የሚባሉ ዜጎች በቆዳው መጥቆርና በከንፈሩ መወፈር ምክንያት ብቻ ኢትዮጵያ እንደተዋረደች ማሰባቸው በወቅቱ የተንፀባረቀና ለትእዝብት የበቃ ነበር። መንግስቱ ሃይለማርያም መሪያቸው ሆኖ ሳለ፤ የወደቀው ገዢ መደብ የአመለካከት ሰለባዎች ለቴሌቪዥን አንባቢነትና ለሆስተስነት ቀያይ ሴቶችን ይመለምሉ ነበር። ይህን አይነት የመረጣ መስፈርት በግልፅ ወረቀት ላይ ያሰፈሩት ሲሆን፣ “የኢትዮጵያን የቁንጅና ምስል ለማንፀባረቅ” የሚል ስም ነበር የሰጡት። ርግጥ ነው፤ የወያኔ ሰዎች በትግሉ ጊዜ አማራን እንደ ፈሪ በመሳል ለገበሬ ሰራዊታቸው ማስተዋወቃቸው በወቅቱ የተዋጊዎቻቸውን ወኔ ለማጀገን ጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ደርግም በአንፃሩ ወያኔ አንድ ጆሮውን እንደ ሰሌን አንጥፎ፤ ሌላ ጆሮውን እንደ ብርድ ልብስ ተከናንቦ የሚተኛ አስፈሪ ፍጡር አድርጎ ለማስተዋወቅ ጥረት አደርጎ ነበር። ጦርነቱ ካለቀ በሁዋላ የወያኔ ተዋጊዎች ጆሮ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ጆሮ ተመሳሳይ መሆኑ ታውቆአል። በአንፃሩ ጦርነቱ ካለቀ በሁዋላ የወያኔ መሪዎች ለፕሮፓጋንዳ የተጠቀሙበትን “አማራ ፈሪ – አማራ ሞኝ” የተባለ ወኔ የመገንቢያ ስልት እንደ እውነት ይዘው መቀጠላቸው ግን የሚያስቅ ጅልነት ነው። የወያኔ መሪዎች አማራ ፈሪና ሞኝ እንዳልሆነ ያውቁ ነበር። ሰራዊታቸውን ለማበረታታት የፈጠሩትን ግን በጊዜ ሂደት ራሳቸውም አመኑት። ህዝቡን ሲሰድቡት፣ ሲያዋርዱት፣ ሲገድሉት ምንም አለማድረጉን ሲመለከቱ፣ “በፊት ለፕሮፓጋንዳ የተጠቀምንበት እውነት ሳይሆን አይቀርም” ወደሚል ገቡ። ስብሃት ገብረእግዚአብሄር “ሃበሻና ውሻን ቀድመህ ካስደነገጥከው አይደፍርህም” ይል ነበር። ወያኔ አማሮችን ደግሞ ደጋግሞ በስድብ በማዋረድ ንቀቱን እንዲለማመዱት፤ ፈሪነትን እንዲቀበሉት ለማድረግ ጥሯል። አልተረዱትም እንጂ በመሰረቱ በውጊያ ያሸነፍከውን ሰራዊት “ፈሪና ሞኝ ነበር” ብለህ ካጥላላኸው ራስህን እንደሰደብክ ይቆጠራል። ምክንያቱም በሌላ አነጋገር “ፈሪና ሞኝን ለማሸነፍ 17 አመታት ተዋጋሁ!” እንደማለት ይሆናል።
እነሆ! ወርሃ ግንቦትን ተከትሎ ጆሮ የሚጎትት ወግ መስማት የተለመደ ሆኗል።
ቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ከግንቦት ሃያ የድል በአል ጋር ተያይዞ ስሙ ሊቀየር ታስቦ እንደነበር የሰማሁትም በዚሁ በግንቦት ወር ነው። አቦይ ስብሃት ውድቅ ባያደርጉት ኖሮ ምናልባት የዚህ አመት ትልቁ ርእሰ ጉዳይ ለመሆን በበቃ ነበር። ነገሩ የተነሳው ከወደ መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን አቅጣጫ ነው ይባላል። የመቐለው አየር ማረፊያ ለራስ አሉላ አባነጋ ስለተሰጠ፤ የጎንደሩ አየር ማረፊያ ለአጤ ቴዎድሮስ ስለተሰጠ፤ የአዲሳባውም እንዲሁ ለኢትዮጵያ ታላቅ ተግባር ለፈፀመ ሰው ቢሰጥ ተገቢ ስለሆነ፤ የግንቦት ሃያ 25ኛ አመት ሲከበር ቢከናወን የሚል ነበር።
መረጃውን የላከልኝ ሰው እንደጠቆመኝ “የአየር ማረፊያው ስም ለመለስ ዜናዊ በቀጥታ ተሰጠ” ከሚል ሃሜት ለመዳን ኮሜቴ ተቋቁሞ ዋለልኝ መኮንንና ጣይቱ ብጡል ከመለስ ዜናዊ ጋር ለውድድር ይቀርባሉ። ኮሚቴው የሶስቱንም ሰዎች ታሪክ አጥንቶ እንዲያመጣ ይታዘዛል። እቴጌ ጣይቱ አዲሳባን የመሰረተች፣ በአድዋ ድል አስተዋፅኦ ያደረገች፣ ለዚህ ግዙፍ ተግባሯ የሚመጥን መታሰቢያ ያላገኘች በመሆኑ አይሮፕላን ማረፊያው ይገባታል የሚል ፅሁፍ ቀረበ። ዋለልኝ መኮንንም ጠንካራ ድጋፍ ነበረው።የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ አንስቶ ተማሪዎችን ለለውጥ የቀሰቀሰ፤ በተጨማሪ ደግሞ ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ አይሮፕላን ውስጥ በግፍ የተገደለ በመሆኑ ቦሌ ኤርፖርት በስሙ ቢሰየምለት ይገባዋል ተባለ። በመለስ ዜናዊ ዙሪያም እንዲሁ ሰፊ ፅሁፍ ቀርቦ ነበር። ከመለስ እረፍት በሁዋላ የሚነገሩለት ገድሎቹ ሁሉ ተጨምቀው ቀረቡ።
ከታችኞቹ አሳብ አመንጪዎች አልፎ ጉዳዩ ስብሃት ነጋ ዘንድ ሲደርስ ግን አሳቡን ባጭሩ ቀጩት ተባለ። እንደሰማሁት አቦይ ስብሃት ጉዳዩን ሲዘጉ፣ “የቦሌ ኤርፖርትን ስምለመለወጥ ከታሰበ ለኤለሞ ቂልጡ መስጠት በተሻላችሁ!!” ብለው ተናግረዋል። ይህ አባባላቸው አቦይ ስብሃት የኦሮሞን ህዝብ ታሪክና ስነልቦና በትክክል እንደሚያውቁ ጠቁሟል። በአንፃሩ ቦሌን ለመለስ ዜናዊ መሸለም እየጨሰ በሰነበተው የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ቆጥረውት ከሆነ መልካም አስበዋል። ወርሃ ግንቦት ጆሮ የሚጎትት ወግ አታጣም።
በአፍሪቃ ቀንድ ከወርሃ ግንቦት ጋር በተያያዘ ከጥቂት በላይ የድልና የሽንፈት ታሪኮች አሉ። የወያኔ ደጋፊዎች ግንቦት ሃያ ዞሮ ሲመጣ “የደርግ ስርአት የወደቀበት” በሚል እለቱን በፈንጠዝያ ያሳልፉታል። በተለምዶ “የአንድነት ሃይሎች” እየተባሉ የሚታወቁ ወገኖች በበኩላቸው፣ “ግንቦት ሰባት” ለተባለችው ቀን “የዴሞክራሲ ቀን” የሚል ቅፅል ስም ሰጥተዋል። ምክንያቱ በምርጫ 97 ወያኔ በዝረራ የተሸነፈበት እለት ግንቦት ሰባት በመሆኑ ነው። የወያኔ ደጋፊዎች በበኩላቸው “ግንቦት ሰባት” ራስ ምታታቸው ነው። ከምርጫው ውጤት በተጨማሪ አንዳርጋቸው ፅጌና ብርሃኑ ነጋ የተባሉ ሁለት አስቸጋሪ ሰዎች በዚህ የእለት ስም የሚጠራ ድርጅት መስርተዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ “ግንቦት ስምንት” ሌላው ታሪካዊ እለት ሆኖ ተመዝግቧል። መርእድ ንጉሴና ፋንታ በላይ የተባሉ ጄኔራል መኮንኖች በኮሎኔል መንግስቱ ላይ የሞከሩት መፈንቅለ መንግስት በዚሁ እለት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በዚህ በግንቦት ወር ኤርትራውያን አገራቸውን ነፃ ያወጡበትን 25ኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ በአል አክብረዋል። በበአሉ ስነስርአት ላይ በክብር እንግድነት ከተጋበዙት መካከል የOLF ሊቀመንበር ኦቦ ዳውድ ኢብሳ፤ እንዲሁም የONLF ሊቀመንበር አድሚራል መሃመድ ዑመር ታይተዋል። የAG7 (አርበኞች ግንቦት ሰባት) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበአሉ ላይ ይገኝ ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበር። ቀደም ብሎ ለድርጅታዊ የስራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ከሄደበት ያለመመለሱን ተረዳሁ። በርግጥ ብርሃኑ በበአሉ ላይ አለመገኘቱ አጋጣሚው ለሱ ጥሩ ነበር። ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ አድናቂዎቹም ሆኑ አድቃቂዎቹ ለመሰንበቻ ፕሮፓጋንዳ ለጥብስ ያደርሱት ነበር። ወያኔ በበኩሉ የግንቦት ሃያን 25ኛ አመት በአል ያከበረው ደርግ በቀይ ሽብር የገደላቸውን ወጣቶች በማስታወስ ነበር። ይህን ማድረጉ ለምን ይሆን? በኦሮሚያ አመፅ የተገደሉትን ወጣቶች ከቀይ ሽብር ጋር አነፃፅረን “ህወሃት ሆይ! በኦሮሚያ የገደልከው ከደርግ የቀይ ሽብር ግድያ ያነሰ ነውና አይዞህ አትሳቀቅ!” ብለን እንድናፅናናው ፈልጎ ይሆን? ወይስ ቀይ ሽብርን በማስታወስ፣ “ዛሬም እንዲህ ሊደገም ይችላል!” በሚል የዚህን ዘመን ወጣቶች ለማስፈራራት? አላማው አልታወቀም።
ሰሞኑን በአንድ አጋጣሚ የአዲሳባ ነዋሪየሆኑ የትግራይ ሰዎችን አጊንቼ ነበር። የስርአቱ ደጋፊ ቢሆኑም ትግራይ ውስጥ አፈናው ከአዲሳባ የበረታ መሆኑን አጫውተውኛል። በአዲሳባ ነዋሪ የሆኑ የህወሃት ደጋፊዎች መጪውን ዘመን በመስጋት ገንዘብና ንብረታቸውን ወደ ዶላር እየቀየሩ እንደሆነም ጠቁመውኛል። በተመሳሳይ ከሌላ ምንጭ ይህን አረጋግጫለሁ። በኢህአዴግ ዙሪያ ያሉ ባለስልጣናት ቤተሰቦች እና ደጋፊዎቻቸው ወደ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ቦትስዋናና ኬንያ ወደ መሳሰሉት የአፍሪቃ አገራት በመሄድ ንብረት በመግዛት አንድ እግራቸውን ከአገር እያስለቀቁ ነው። ሙሰኛው ስርአት የወለዳቸው እነዚህ ቱጃሮች መቶ ሺህ ዶላር ላቀረበላቸው ሰው አንድ ዶላር በሰላሳ ብር ሂሳብ ይመነዝሩለታል። የህወሃት ስርአት ደጋፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው የምእራባውያን ኤምባሲዎችን በቪዛ ጥየቃ ማጨናነቃቸው ሌላው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው። የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ይህንኑ የቪዛ ጠያቂ መብዛት ወደ የአገሮቻው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፤ምክንያቱን በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ቤተሰብን የማሸሽ ዝንባሌ ስለመሆኑ ጠቅሰውታል።
የፖለቲካ አለመረጋጋቱ በቀጥታ ከኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጋር የተያያዘ ነው። ስርአቱ በ2015 ምርጫ በሙሉ ድምፅ መመረጡን ሲያውጅ 6 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ተናግሮ ነበር። አባላቱ ከነቤተሰባቸው ደግሞ 30 ሚሊዮን እንደሚጠጉ ምእራባውያንን አሳምኖ ነበር። የኦሮሚያ አመፅ መፈንዳቱ የመረጃውን ሃሰትነትና የምርጫውን መጭበርበር ያጋለጠ ክስተት ሆኖአል። በሙሉ ድምፅ ተመረጡ የተባሉት ተመራጮች ከስራ ተባርረው የኦሮሚያ ክልል በወታደራዊ አስተዳደር እንዲተዳደር መደረጉ ስርአቱ እንደ ስርአት መቀጠሉን ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቷል። በርግጥ ህወሃት ሩጫውን ጨርሶ ሲያበቃ ስልጣኑን ማን ሊረከብ እንደሚችል መተንበይ ቀላል ባይሆንም፤ የምእራባውያን ጣልቃ ገብነት ሊከሰት እንደሚችል ማሰብ ይቻላል።
ዞረም ቀረ መልከ ብዙ ትንበያዎች ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የመቀጠል እድል እንደሌላት የሚገልፁ አሉ። ጄኖሳይድ ሊያጋጥም ይችላል ብለው የሚሰጉም አሉ። በርግጥ በስርአት ውድቀት ዋዜማ ላይ እንዲህ ያሉ ትንቢቶችን መስማት የተለመደ ነው። በደርግ ውድቀት ዋዜማ ተመሳሳይ ትንበያዎች ተሰምተው ነበር። የተገመተው ግን አልሆነም።ንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ ከሞቱ የኢትዮጵያ ፍፃሜ እንደሚሆን ሲነገር የነበረው ትንበያም እንዲሁ ተረት ሆኖ ቀርቷል። ያለፉት ትንበያዎች ስላልደረሱ የዚህ ዘመን ስጋትም በተመሳሳይ የተጋነነ ነው ብሎ ማሰብ ግን ልክ አይሆንም። ስለ ነገ በእውቀት ማሰብ ብልህነት ነው።