June 29, 2016
Watch this: http://video.ethsat.com/?p=25324
ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወረዳ አንድ በተለምዶ ቀርሳ፣ ኮንቶማ፣ ኤንቱ ሞጆ፣ ዱላ ማርያም፣ ሰፈራ፣ ማንጎ፣ ገብሬአል በሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎችና እማወራዎች የሚኖረባቸውን አካባቢወች በማፍረስ መሬቱን ለባለሀብቶች ለመስጠት የተጀመረውን እንቅስቃሴ የተቃወሙ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ተከትሎ ድንጋዮችን በፖሊሶች ላይ ወረውረዋል።
የመብራት ሃይል ሰራተኞች ኮንቶማ እና ማንጎ ሰፈር በሚባለው አካባቢ የሚገኘውን የሃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ለመንቀል ሲሞክሩ ህዝቡ ተቃውሞ አሰምቷል። በተቃውሞው 3 ፖሊሶች እና አንድ የመስተዳድሩ ሰራተኛ ሲገደሉ፣ ከ20 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
የማንጎ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ቤተመንግስት ለተቃውሞ ቢያመሩም በፖሊሶች ታግተው ውለዋል። የቀርሳና ኮንቶማ አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ በተለያዩ መኪኖች ላይ ተሳፍረው ወደ ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ሲያመሩ ፖሊሶች አስቁመው ሰዎችን አስወርደው በትነዋቸዋል።
ይህ የህልውና ጉዳይ ነው የሚሉት ነዋሪዎች ፣ከዚህ በሁዋላ በጉልበት እናፈርሳለን ቢሉ ደም መፋሰስ ያስክትላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። በስብሰባው ላይ የተገኙ በተለይም ከሳውዲ አረቢያ ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች ፣ ለአመታት ደክመው ባጠራቀሙት ገንዘብ የሰሩዋቸው ቤቶች በግዴለሽነት እንዲፈርስባቸው መደረጉን በምሬት ገልጸዋል
የከተማ ልማት ሹሙ አቶ መኩሪያው ሃይሌ በአዲስ አበባ ባዶ ቦታ እየጠፋ መምጣቱን መናገራቸው ይታወቃል። በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶአደሮችን በማፈናቀል አዲስ አበባን ለማስፋፋት የተጀመረው እቅድ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ የኢህአዴግ መንግስት ግን አሁንም በማፈናቀሉ ዘመቻ ቀጥሎበታል።