: ወታደሮችንና ከባድ ማሳሪያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ግንባር እየተጓዙ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Fri, 1 Jul 2016 00:24:23 +0200

ወታደሮችንና ከባድ ማሳሪያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ግንባር እየተጓዙ ነው

June 30, 2016

Watch this:

 http://video.ethsat.com/?p=25348

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከደቡብና ከመሃል አገር የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም አዳዲስ የገቡና ነባር የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ግንባር እየተጓዙ ነው። የህዝብ ማመላለሻ ተሽካርካሪዎች በግዳጅ ወታደሮችን እንዲያመላልሱ እየተደረገ መሆኑን የሚናገሩት የአይን እማኞች፣ ከባድ መሳሪያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከዚህ ቀደም ባልታዬ መልኩ በብዛት ወደ ግንባት እየተጓዙ ነው ብለዋል።

ከትናንት በስቲያ ወደ ትግራይ ሲጓዝ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ኮንቮይ ኮምቦልቻ ላይ ሁለት ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው መንገድ ዘግተውበት ከ5 ሰአታት በላይ መንገድ ዘግቶ መቆየቱንም የአይን እማኞች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የ አዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን በሰፊው በተደራጀ አግባብ እየሰለሉዋቸው መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል። ይህንን ተከትሎ በደንብ ማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ ካድሬዎች ጭምን ድንጋጤ ውስጥ  መግባታቸው ታውቋል።

ስለላው ለምን እንደሚካሄድ ባይታወቅም፣ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ እየጨመረ የመጣው አለመተማመን ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በማለት ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። ከፌደራል ፖሊስና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስራቸውን ጥለው የጠፉትን  ፖሊሶች አዲስ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየታደኑ መሆኑን ምንጮች አክለው ግለጸዋል።

*******************************************************************************************

በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደው ዘመቻ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ተገደሉ

June 30, 2016

ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በላፍቶ ከተማ ዙሪያ ህገወጥ ናቸው ያላቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ እያካሄደ ባለው ዘመቻ ሃሙስ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ።

በዚሁ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሃና ፋሪ ተብሎ በሚጠራው በዚሁ አካባቢ እየተካሄደ ባለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው መፅሄት በበኩሉ ረቡዕ ከሞቱ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የወረዳ ስራ አስፈጻሚ በተጨማሪ አንድ ነዋሪ መገደሉን ሃሙስ ዘግቧል።

ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ባለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ተሰማርተው በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥጥርን እያደረጉ ሲሆን፣ የመገኛና ብዙሃን ወደስፍራው እንዳይዘልቁ መደረጉ ታውቋል።

ሃሙስ ረፋድ ላይ በጸጥታ ሃይሎች ከተገደሉ ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛ በጥይት መገደሉንና ሌላ መንገደኛ በጸጥታ ሃይሎች ተደብድቦ ህይወቱ ማለፉን ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ህገወጥ ግንባታ ታከሄዶበታል በሚለው የሃና ፋሪ አካባቢ ወደ 30ሺ የሚጠጉ ቤቶች ሲኖሩ አስተዳደሩ አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች ህወገጥ እንደሆኑ ይገልጻል።

የመኖሪያ ቤታቸው እያፈረሰባቸው የሚገኘው ነዋሪዎች በበኩላቸው በአካባቢው ከ10 አመት በላይ መኖሪያቸውንና በዝናብ ወቅት የተጀመረው የማፍረስ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቀው እንደተሰደዱ የሚናገሩት ነዋሪዎች ቀርሳ ኮንቶማ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በርካታ ነዋሪዎች ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የጸጥታ አባላት ገድለዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የጸጥታ ሃይሎች በነዋሪዎች ላይ እንግልት እየወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ረቡዕ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ግድያን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፍለጋን እያካሄደ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ሃሙስ በተካሄደ የማፍረስ ዘመቻ በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን ለመረዳት ተችሏል።

በሌሉበት የመኖሪያ ቤታቸው እንደፈረሰባቸው የተናገሩ ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር እንዲህ ያለ የሃይል እርምጃ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የከተማዋ አስተዳደር በተለያዩ ቦታዎች ህገወጥ ግንባታ ተካሄዶባቸው ያላቸውን የመኖሪያ አካባቢዎች ለማፍረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን በድጋሚ ገልጿል።

******************************************************************************************
በኦጋዴን የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀ በመላ ኢትዮጵያ እየደረሰ የሚገኝ ወንጀል ነው ተባለ

June 30, 2016

ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)

በኦጋዴን የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በመላው ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያሳይ እንደሆነ ተገለጸ።

በኦጋዴን ህዝብ ላይ በኢህአዴግ ታጣቂዎች የተፈጸመው ወንጀል ተደብቆ የተቀመጠ እና ለመገናኛ ብዙሃን የማይነገር በመሆኑ ተመሳሳይ ወንጀሎች በኦሮሚያ፣ ጋምቤላና፣ አማራ ክልሎች ላይ መፈጸሙን የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ ለኢሳት ተናግረዋል። የውጭ መገናኛ ብዙሃን በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመዘገብ ፈቃድ መከልከላቸው ችግሩ ተባብሱ እንዲቀጥል አስተዋጽዖ አድርጓል ተብሏል።

የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ግርሃም ፒብልስ ባለፈው ሳምንት በኦጋዴን ላይ በምስል ተቀናብሮ በቀረበው ዘገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጽንዖት ሰጥቶት እንዲመረምረው የሚያግዝ መሆኑን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስም ፊልሙ ጄኔቫ በሚገኘው በተባበሩት  መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደታየ ለማወቅ ተችሏል። ፊልሙን ያዩት የምክርቤቱ አባላትም በከፍተኛ የሃዘን ስሜት ተውጠው እንደነበሩ ሚስተር ፒብልስ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በኦጋዴን ሴቶች ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች የተፈጸውን ወንጀል የሚያሳየው ፊልም በአውሮፓ ፓርላማ ለእይታ እንደበቃ ለማወቅ ተችሏል። በእንግሊዝም ከአውሮፓ ህብረት መውጣት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ለምክር ቤት አባላትና ሰብዓዊ መብት ተቋማት ቀርቦ እንደሚታይ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተዓማኒነት የተጠየቁት የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ ሲናገሩ፣ “ጭስ ባለበት እሳት አለ” የሚለውን የእንግሊዛውያን አባባል ተጠቅመዋል። በኦጋዴን የታየው የጥቃቱ ሰለባ ሴቶች ምስክርነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በትክክል እንደተፈጸመ ማሳያ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በህጻናት ጭቆና፣ በመሬት ነጠቃና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጥናት ያደረጉ ግርሃም ፒብልስ፣ በኦጋዴን ውስጥ ሲደረግ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመቃወም አገዛዙን ከድተው በስደት የሚገኙ ወታድሮች ላይ የደረሰውን ሰቆቃ በምስል አቀናብረው ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

መንግስት እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቀረት የተጠናከረ ዘመቻና እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግም ፒብልስ ተናግረዋል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የእንግሊዝ መንግስት ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ አገራት ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

“በኢትዮጵያ ውስጥ ፍርሃት አለ፣ አገሪቷ በዘር፣ በሃይምኖት፣ በክልል ተከፋፍላለች” ያሉት የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህዝቡን በአንድ ላይ በማንቀሳቀስ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።

 
Received on Thu Jun 30 2016 - 17:03:28 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved