May 11, 2016
Watch: http://video.ethsat.com/?p=23778
ግንቦት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ታጣቂዎቹ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት 20 የመንግስት ወታደሮች ሲገደሉ፣ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል። ከተገደሉት መካከል የአካባቢው ወታደራዊ አዛዥም ይገኝበታል። የተኩስ ልውውጡ ለረጅም ሰአታት የቀዬ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ህክምና ተወስደዋል።
የመንግስት የጸረ ሽብር ግብረሃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ከኤርትራ የተንቀሳቀሱ ሃይሎች በሞያሌ በኩል ወደ አርባምንጭ ጫካ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ገልጿል። መንግስት በቁጥጥር ስር የዋሉና የተገደሉ ታጣቂዎች መኖራቸውን ቢገልጽም ፣ በአሃዝ ከመግለጽ ተቆጥቧል። ይሁን እንጅ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ድንገተኛ ጥቃቱን የፈጸሙት የታጠቁ ሃይሎች፣ ጥቃቱን ካደረሱ በሁዋላ ከአካባቢው ተሰውራል። ይህን ተከትሎም ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የከተማው ሰዎች እየታፈሱ ተወስደዋል።
አርበኞች ግንቦት 7 ጥቃቱን እንደፈጸመ በከተማው እየተወራ ቢሆንም፣ ንቅናቄው እስካሁን የሰጠው ይፋዊ መግለጫ የለም።