ከአዘጋጁ: ይህ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ታትሞ በወጣው ‘ውይይት’ መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቷል:: በሃገር ቤት ያላችሁ አንባቢዎች መጽሔቷን ገዝተው እንዲያነቧት ትበረታታላችሁ::
ለዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ቅድመ-ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከዴሞክራት ፓርቲ ተቀናቃኞቻቸው በርኒ ሳንደርስ ጋር እየተፎካከሩ ያሉት ወ/ሮ ሒላሪ ክሊንተን በሥራ ጉዳይ እ.አ.አ. ከ2009 እስከ 2013 ሲለዋወጧቸው የነበሩ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢሜይሎቻቸው ከአጠቃቀም ግድፈት ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይፋ ሆነዋል፡፡ ከነዚህ ኢሜይሎ መካከል ዘላለም ክብረት ኢትዮጵያን የሚመለከቱትን 100 ኢሜይሎች ተመልክቶ ስለአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ያላቸውን አንድምታ እንደሚከተለው አቅርቦልናል፡፡
አሜሪካዊው ፒተር ሺዌዘር ደርዘን የሚሆኑ መጽሐፍትን ጽፈዋል። የመጽሐፍቶቻቸው ዋነኛ የትኩረት ነጥብም በፖለቲከኞች የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ ደባዎችን ማጋለጥ ነው። ከጻፏቸው መጽሐፍት መካከል ግን በዓለማቀፍ ደረጃ በግንቦት 2015 እንደጻፉት ‘Clinton Cash: The Untold Story of How and Why Foreign Governments and Businesses Helped Make Bill and Hillary Rich’ ባለረጅም ርዕስ መጽሐፋቸው ትኩረት የሳበ መጽሐፍ ነበራቸው ማለት አይቻልም። በዚህ ባለ 256 ገጽ መጽሐፋቸው አሁን የአሜሪካ ፕሬዘደንት ለመሆን ጫፍ ላይ ደርሰዋል ተብሎ እየተነገረላቸው ያሉት የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተንና የባለቤታቸው የቢል ክሊንተን የዕርዳታ ተቋም የሆነው ‘Clinton Foundation’ ከተለያዩ አምባገነን መንግሥታትና ባለሀብቶች ገንዘብ በመቀበል ሒላሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ከ2008 – 2012) በነበሩባቸው አራት ዓመታት ውስጥ በአምባገነኖች የሚደረጉ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን አይተው እንዳላዩ አልፈዋል የሚል ነው። መጽሐፉ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ሰጥቶ ትኩረት ካደረገባቸው የትኩረት ነጥቦች አንዱ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚፈጽማቸው የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችና የሙስና ተግባራት የአሜሪካ መንግሥት ምንም ዓይነት ተጠያቂነትን ሳያስቀምጥ ዕርዳታ ይሰጣል” የሚል ይገኝበታል። ጸሐፊው ለዚህም ጥሩ ማሳያ አድርገው ያቀረቡት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼኽ ሙሐመድ አል አሙዲን ለክሊንተን ፋውንዴሽን ሰጡት የተባለውን የ20 ሚሊዮን ዶላር ስጦታ ነበር። በወቅቱ ስጦታውን ሰጡ የተባሉት ግለሰብ “ስጦታ አልሰጠሁም” ቢሉም በኋላ ግን የተሰጠው ስጦታ 6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ገልጸው፤ ስጦታው ኤድስን ለመከላከል ከመሆን በቀር ምንም የፖለቲካ ዓላማ የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።
ክሊንተን በምርጫ ሒደታቸው በተለይም ከሪፐብሊካን ተቀናቃኞቻቸው ይህ መረጃ እዚህም እዛም ሲነሳባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከዚህ መረጃ ይልቅ ግን ክሊንተንን እስከ ምርመራ ያደረሳቸው ጉዳይ “ደኅንነቱ ባልተጠበቀ በግል ሰርቨራቸው በመጠቀም ጥብቅ ሚስጥር የያዙ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ኢሜይል ተላልከዋል” የሚለው ክስ ነው። በዚህም ምክንያት በአማካሪዎቻቸውና በባለሙያዎች የተጻፉትንና በአብዛኛው በሦስቱ ረዳቶቻቸው ማለትም ቼሪል ሚልስ፣ ጄክ ሱሊቫንና ሁማ አባዲን የተላኩላቸውን በፍርድ ቤት ከሃምሳ ሺሕ ገጽ የሚልቁትን ወደ ሠላሳ ሺሕ ኢሜይሎች በፍርድ ቤት ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ከነዚህ ኢሜይሎች መካከል 100 የሚሆኑት ኢትዮጵያ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተገናኙ ናቸው።
ኢትዮጵያና ረኀብ
በ2003 እና በ2004 በምስራቅ አፍሪካ ከባድ የድርቅ አደጋ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ሶማሊያዊያንና ኬኒያዊያን ለረኀብ ተጋልጠው ነበር። ከሒላሪ ክሊንተን ኢሜይሎች እንደምንረዳው ረኀቡ የአሜሪካን መንግሥት እጅግ አሳስቦት እንደነበረ ነው። ከመልዕክቶቹ በአንዱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ስለረኀቡ ገለጻ ያደረጉት ቼርሊ ሚልስ “ረኀቡ እጅግ ሰቅጣጭ ነው። ነገር ግን በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መካከል መልካም ዜናም ይሰማል። ይሄውም ባለፈው ኢትዮጵያ በዚን ያህል ከባድ ድርቅ በተመታች ወቅት 14 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን 4.5 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ናቸው ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡት። ይሄም አሜሪካና ሌሎች አገራት የሠሩት የሴፍቲ ኔት ዕርዳታ ውጤት ነው” ይላሉ። ይሄን ተመልክትን ዛሬ ቁጥሩ በዐሥርና በሃያ ሚሊዮን መካከል ከፍ ዝቅ እያለ ለሚገኝው ለረኀብ የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ስንመለከት ለጋሽ አገራት ያላቸው እምነት የተሳሳተ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ከዚህ ባለፈ ግን አስገራሚው ጉዳይ የኢትዮጵያ ረኀብ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚቀባበሉት ብቻ ሳይሆን፤ ሚስጥራዊ የመልዕክት ልውውጦችም የሚገልጡት ያገጠጠ እውነታ መሆኑ ነው።
የአሁኑ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ና አሜሪካ
ከሰባት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በአሜሪካ ረጅም ግንኙነት ላይ ድንቅ መጽሐፍ የጻፉት ዶ/ር ጌታቸው መታፈሪያ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን ኢትዮጵያ ‘የአሜሪካ Gatekeeper’ ሲሉ ይጠሯታል።
አሜሪካ ከአፍሪካ ቀንድ መንጭተው ጥቅሟን ሊጎዱ የሚችሉ ጉዳዮችን ለማረጋጋት በማሰብ ኢትዮጵያን የአካባቢው አለቃ አድርጋ መሾሟ ያለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ታሪክ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ጌታቸው፤ ነገር ግን አሜሪካ ግንኙነቷን ከኢትዮጵያ ተቋማት ጋር ከማድረግ ይልቅ ከግለሰብ አመራሮች ጋር ማድረግን መርጣለች ይላሉ።
በነሐሴ 2004 ሒላሪ ክሊንተን የተለዋወጧቸው ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ኢሜይሎችም የሚያረጋግጡት ይሄንኑ ነው። ኢሜይሎቹ በወቅቱ የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን መሞት ተከትሎ መለስ የአሜሪካ ሁነኛ ወዳጅ በመሆናቸው አሜሪካ ታላቅ ባለሥልጣናትን ለቀብር እንድትልክ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ሲጎተጉቱ የሚያሳዩ ናቸው። “አሜሪካ ትልቅ የዲፕሎማሲ ቡድን እንደምትልክ ስገልጽላቸው [በወቅቱ የኢትዮጵያ ምክትል የውጭ ጉዳይ የነበሩትና] መለስ ሲሞቱ አብረዋቸው ቤልጅየም፣ ብራሰልስ የነበሩት ብርሃነ [ገብረክርስቶስ] በደስታ ከሰው ፊት አቅፈው ሳሙኝ” ይላሉ በወቅቱ የሒላሪ ሁነኛ ወዳጅ የነበሩትና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊ የነበሩት ቼሪል ሚልስ ለሒላሪ በተላከ አንድ ኢሜይላቸው ላይ ከአዲስ አበባ የደረሳቸውን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን እምነት አቶ መለስ ላይ ብቻ ጥሎት እንደነበርና የዶ/ር ጌታቸውን የአሜሪካና የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ዋ ኢትዮጵያ ግንኙነት እንደ መለስ ባሉ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚል ሐሳብ የሚያረጋግጥልን ደግሞ በወቅቱ በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የፖለቲካል ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ዊንዲ ሸርማን የመለስን ሞት አስመልክተው ለሒላሪ ክሊንተን የጻፉት ኢሜይል ነው። ዊንዲ በኢሜይላቸው “የመለስ ሞት ለኢትዮጵያም፣ ለአፍሪካም ለሁላችንም ጉዳት ነው። ካርሰን እንደሚያምነውም የመለስ ተተኪ የሚሆን ማንኛውም ቀጣዩ መሪ የበለጠ አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ፤ ለእኛም መጥፎና የሚጎረብጥ ይሆናል” በማለት የመለስ ሞት ለአሜሪካ ጥቅም ትልቅ ጉዳት መሆኑን ገልጸው፤ የመለስ ተተኪ ግን ለአሜሪካ ጥቅም የማይመች መሆኑን ገምተዋል። ይሄም የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት በመለስ ላይ እንጅ በተቋማት ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን አመላካች ነው። ነገር ግን እንደ ተገመተው የመለስ ተተኪ ለአሜሪካ አልተመቻትም ማለት ደግሞ ከባድ ነው።
ሁሌ ‘deeply concerned’ የምትሆነው አሜሪካ
“አሜሪካ የዓለም አለቃ ናት” የሚለው አባባል ብዙ እውነትነት አለው። በመላው ዓለም ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች፣ የሁሉንም የዓለም ሐገራት ዓመታዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የደኅንነትና የሰብኣዊ ይዞታ አጥንቶ የሚተነትን ስርኣት ከአሜሪካ ውጭ ማንም የለውም። አዎ አሜሪካ ትልቅ አገር ናት። ለዚህም ነው በተለያዩ አገራት የመብት ጥሰትም ሆነ ብጥብጥ በተነሳ ቁጥር ከሁሉም ቀድማ አሜሪካ የተለመደውን ‘We are deeply concerned’ የሚል መግለጫ የምታወጣው። አሜሪካ ዝም ስትልም ‘እንዴት አሜሪካ ዝም ትላለች?’ የሚል ወቀሳ ቀድሞ የሚያርፍባት። ምናልባትም ይህ ‘አሜሪካ በተለያዩ የመንግሥታት ለውጦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጋለች’ የሚለው ሐሜት ተቀጥላ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁን አሁን “አሜሪካ ‘We are deeply concerned’ (በፅኑ አሳስቦናል) የሚል የተለመደ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ ለሰብኣዊ መብት ጥሰቶችም ሆነ ለአምባገነናዊ አገዛዞች ትኩረት አትሰጥም” የሚለው ሐሳብ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የብዙ የሰብኣዊ መብት ታጋዮች ድምዳሜ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ‘We are deeply concerned’ የሚል ሁሉንም የማያስከፋ የሚመስል የዲፕሎማቲክ ቋንቋ (diplospeak) መጠቀም እንደጀመረ ጉዳዩን የተከታተሉ ሊቃውን ይገልጻሉ:: የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሠራተኛ የነበሩት ኮሪ ስኬክ (kori Schake) እንደሚሉት አሜሪካ ‘We are deeply concerned’ ስትል በዲፕሎማቲክ ቋንቋ [ሁለቱንም ወገኖች ላለማስከፋት] መሐሉን መያዟ እንደሆነ ከGoldilocks መርሁ “just rights’” ጋር በማመሳሰል ይገልጹታል። ኮሪ አያይዘውም “ጉዳዩ ያሳስበናል ማለት ቢሆንም በጣም አሳስቦናል ማለት ግን አይደለም” ይላሉ።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ‘We are deeply concerned’ ስትል ምን ማለቷ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚመስሉ ጉዳዩች በሒላሪ ክሊንተን ኢሜይሎች ውስጥ ማየት እንችላለን።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሚያዚያ ወር መጨረሻ 2008 ባወጣው መግለጫው አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ) አመራሮች በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሠረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ናችሁ ተብለው መከሰሳቸው በጥብቅ እንዳሳሰበው (deeply concerned) ገልጾ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን በመጠቀም የሠላማዊ ዜጎችን ድምፅ ከማፈን እንዲታቀብ ጠይቆ ነበር። ነገር ግን ይህን መግለጫ በሰኔ 2003 ከቼሪል ሚልስ ለሒላሪ ክሊንተን ከተላከላቸው አንድ ኢሜይል አንፃር ስንገመግመው እውነትነቱን እንጠራጠራለን። በሰኔ 2003 የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ናቸው የተባሉ ዐሥራ አራት ኢትዮጵያዊያን ላይ ከዘጠኝ ዓመት እስር እስከ ዕድሜ ልክ እስር መፍረዱን ተከትሎ ለሒላሪ በተላከላቸው አንድ ኢሜይል ላይ “የኢትዮጵያው ዴስካችን እንዳሳወቀን ከሆነ ይህ የፍርድቤቱ ውሳኔ መንግሥት በሽብርተኝነት ላይ እየወሰደ ካለው ጠንካራ እርምጃ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው” በማለት ኦነግ የሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ በተዘዋዋሪ በመግለጽ፤ የመንግሥትን እርምጃ ያወድሳል።
ሌላው ለዚህ ጉዳይ ማሳያ ሊሆነን የሚችለው ጉዳይ በ2003 በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ረኀብ በአፍሪካ ቀንድ ማንዣበቡን ተከትሎ የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን ድርቁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰፋፊ የግል እርሻችን (commercial farms) አጥቅቶ እንደሆነ ላቀረቡት ጥያቄ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ቡዝ ድርቁ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተ
እንደሆነ ገልጸው፤ “ሰፋፊ የግል እርሻዎች ደግሞ የሚገኙት በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ነው” ካሉ በኋላ፤ “ይሄ ብዙ መሬት ከገበሬዎች ተነጥቆ ለባለሀብቶች ተሰጥቷል የሚባለው ነገር ሚዲያዎች ያጋንኑታል” ብለው ይመልሳሉ። እንግዲህ የአሜሪካን መንግሥት (በአምባሳደሩ ደረጃ) በተለምዶ የመሬት ነጠቃ (land grab) እየተባለ የሚታወቀውን እና ብዙ የሰብኣዊ ተቋማት እያወገዙት የሚገኘውን ከገበሬዎች መሬት ነጥቆ ለባለሀብቶች የመስጠት ሒደት ነው “የተጋነነ ወሬ ነው” ሲል በአምባሳደሩ አማካኝነት የሚያጣጥለው።
የሒላሪ ክሊንተን ኢሜይሎች መካከል አሁንም የአሜሪካን አቋም ሊያሳየን የሚችለው ሌላው ጉዳይ አሜሪካ በምርጫ 2002 ላይ ያሳየችው አቋም ነው። ምርጫውን ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሙሉ ለሙሉ ከማሸነፉ ጋር ተያይዞ በወቅቱ የአሜሪካ ብሔራዊ የፀጥታ ካውንስል ቃለ አቀባይ የነበሩት ማይክ ሐመር ውጤቱን አስመልክተው “We are concerned that international observers found that the elections fell short of international commitments” በማለት የተለመደውን ‘We are [deeply] concerned’ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃለ አቀባይ የነበሩት ፒ.ጀ. ክሮውሊም “ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት ከግምት ውስጥ አስገብታ የእኛን መግለጫ በጥሞና እንድታጤነው እንጠይቃለን” ብለው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኢሜይል ላይ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አቋምን እናገኛለን። ግንቦት 16፣ 2002 የሒላሪ ‘ስታፍ’ አባል የነበሩት ወጣቱ ጄክ ሱሊቫን ከአዲስ አበባ የደረሳቸውን መልዕክት ለሒላሪ ባስተላለፉት (Forward) ኢሜይል ”ምርጫው ብዙ ሰዎች መሳተፋቸው መልካም ነው። የመለስ ፓርቲ ምርጫውን እንደሚያሸንፍ ግልጽ ነው። እንደ 1997 ምርጫ ብጥብጥና ሁከት የሚፈጠርም አይመስልም” በማለት በምርጫው ውጤት ዙሪያ ምንም ዓይነት ቅሬታ የሌለበት ሐሳብ ይሰነዝራሉ። በአደባባይ የምርጫው ውጤት እንደሚያሳዝናት የገለጸችው አሜሪካ በውስጥ ብዙም ስትጨነቅ አይታይም።
ኢሜይሎቹ ምን ይነግሩናል?
በሒላሪ ክሊንተን ኢሜይሎች (ኢትዮጵያን በሚመለከት የተለዋወጧቸውን) ውስጥ ከዶ/ር ገቢሳ ኢጀታ እስከ የአሜሪካ ‘የድሮን’ ጣቢያ በአርባ ምንጭ፤ ከኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ቆይታ እስከ ለኢትዮጵያ የሚደረግ የአምባሳደር ሹመትና መረጣ ድረስ የሚገኙ ሲሆን፤ ከላይ መርጠን ያወጣናቸው ኢሜይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣን ለውጥ ከአሜሪካ ለሚጠብቅ ግለሰብ ጥሩ መረጃ የያዙ አይደሉም። አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀንደኛ አጋርነቷ አሁን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ገዝፎም እንደሚታይም ማሳያ ናቸው። በብዙዎች ግምት አርባ አምስተኛዋ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ይሆናሉ ተብለው ግምት እየተሰጣቸው ያሉት ሒላሪ ክሊንተን ወደ ፕሬዘደንትነቱ መንበር መምጣታቸው የኢትዮጵያን መንግሥት እና የአሜሪካን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክረው እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ያግዘዋል ብሎ ማሰቡንም ሞኝነት ያስመስለዋል።