Zehabesha.com: የወያኔ ውድቀት የአደባባይ ምሥጢር መሆኑን የሚያመላክት አጋጣሚ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 31 May 2016 20:44:32 +0200

የወያኔ ውድቀት የአደባባይ ምሥጢር መሆኑን የሚያመላክት አጋጣሚ

ማስተዋል በለጠ (ከአዲስ አበባ)

Jarsoከደቂቃዎች በፊት ከአንዱ የመሥሪያ ቤቴ ቅርንጫፍ ወደ ዋናው መ/ቤት ስመጣ እንዲህ ሆነ፡፡ መኪናዋ ውስጥ  በተላላኪነት የምትሠራ አንዲት ወጣት፣ ሹፌራችንና እኔ ብቻ ነን የነበርነው፡፡ የዛሬው ቀን የከተማችን ወሬ የሆነውን የማትሪክ ፈተና መሰረቅ አነሳሁና የተለጎመውን የሦስታችንንም አንደበት በጋራ የሀገር ጉዳይ ከፈትኩት፡፡ በዚህን ዓይነት ሁኔታ እኔ ብዙውን ጊዜ ነገር እለኩስና ዋና ሥራየ ማዳመጥ፣ ማዳነቅና ማውጣጣት ነው፡፡ ቀዳሚው ሥራየ ግን የማዋራቸው ሰዎች በኔ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ነው፤ ሰው ከተጠራጠረህ የልቡን አይናገርም፡፡ ዝም ሊል ወይም ሊዋሽህና ሊያታልልህም ይችላል፡፡

ሹፌራችን ቀጠለ –  የኦሮምኛ ቅላፄው በሚነበብበት የሚጣፍጥ ዐማርኛው፡፡ “እኔ እምፈራው የማትሪኩስ መሰረቅ ቀላል ነው – እኔ እምፈራው እነዚህ ሌቦች ኃይለማርያምን ወይም ሌላውን ቱባ ባለሥልጣን እንዳይሰርቁ ነው፡፡ እንዴ! እንዲህ ያለ ነገር እኮ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ …” ሦስታችንም ሣቅን፡፡ ኃይማርያምን ሰርቀው ምስሉን በፌስቡክ እያሳዩ “ተላላኪ ሮቦት አሽከራችሁ እኛ ጋ ነውና ከፈለጋችሁት አንድ ሺ አምስት መቶ ብር ከፍላችሁ ልትወስዱት ትችላላችሁ” ሲሉ እየታየኝ እኔማ ፍርፍር ብዬ ነው የሳቅሁት፡፡ ደግሞስ ደብረጽዮንን ወይም ዐርከበን የሚሰርቁ ሰዎች ሰርቀው ሲያበቁ “ስብሃት ነጋንና አባይ ፀሐዬን ሰርቀናችኋል፡፡ እኛ ጋ ናቸውና ለያንዳንዳቸው አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ከፍላችሁ የምትወስዱ ከሆነ በጃችን ውስጥ የሚገኙትን ተሾመ ቶጋ ሙላቱንና ደመቀ መኮንንን እንደምርቃት በነፃ እንሰጣችኋለን፡፡” ሲሉ በምናቤ እየታየኝ የብቻ ሣቄን ቀጠልኩ፡፡ – ደብረጽዮንና ዐርከበ ብልጥ ስለሆኑ በቀላሉ አይሰረቁም ብዬ ነው ሳላስፈቅዳችሁ የለወጥኳቸው፡፡

ሴቲቱም የዋዛ አይደለችም፡፡ “እንዴ! ግን ግን እዚህ አገር መንግሥት አለ ማለት ይቻላል? ይሄ ነገር እኔስ እውነት አይመስለኝም፡፡ ወዴት እየሄደች ነው አገሪቱ? ብለው ብለው ፈተና ያሰርቁ? ሌላው ዓለም ሲሰማ ምን ይለናል? ከእንግዲህስ በምን መተማመን ይቻላል? መንግሥትንስ እንዴትና በምን እንመነው? በጣም አደገኛ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡” ጎበዝ ተናጋሪ ናት፡፡ ከጠበቅኋት በላይ ምጡቅ የሆነ ፖለቲካዊ ግንዛቤ አላት፡፡ ሁሉም ነቅቷል፡፡

ቢሮ ገብቼ ይህችን ማስታወሻ ለመከተብ ያነሣሣኝ ግን የሹፌሩ አንድ አስተያየት ነው፡፡ ከአንድ እምብዝም ካልተማረ አሽከርካሪ በፍጹም ያልጠበቅሁትን ነገር ነው የተናገረው፡፡ ይህ ንግግሩ የብዙዎች ዜጎችን አተያይና እምነት እንደሚወክል አልተጠራጠርኩም፡፡

እንዲህ ነው ያለኝ፡፡ “አሁን በውነቱ ወንድ ጠፋ እንጂ እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ማስወገድ በተቻለ ነበር፡፡ ግን ሰው ጠፋ፡፡ የሚደፍር ጠፋ፡፡ ቤተ መንግሥቱ እኮ አሁን ባዶ ነው፡፡ ልብ ያለው ቢገኝ በትንሽ መስዋዕትነት አንድ ወር እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እነዚህን ቀን የሰጣቸውን ባለጌዎች ከሥልጣን ማባረር ይቻላል፡፡ ግን ማን ይድፈር? እንጂ አሁን እነሱ ምናቸው ይፈራል? ሕዝብ የጠላቸው አረመኔዎች ናቸው፡፡ ከነሱው አባሎች ውጪ አንድ ሰው አይወዳቸውም፡፡ አብሯቸው የሚንጋፈፈውም ዜጋ ለሆድ እንጂ ለዓላማ አይደለም፡፡” ጭንቅላቴ በርሮ የሚጠፋ እስኪመስል አንገቴን እያወዛወዝኩ በአንክሮ አዳመጥኩት፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምንለውም ይሄንኑ ነው – መናገርና ማድረግ ይለያያሉ እንጂ፡፡ ወያኔዎች ሞተውም እንደሚኖሩ ያረጋገጥኩት በዚህ ልጅ አነጋገር ነው፡፡ እርሱ እንኳን ባቅሙ የወያኔን ወቅታዊ ሁኔታ ጠንቅቆ አውቋል፡፡ በርግጥም እኮ ፍርሀታችንና በፍርሀታችንም ምክንት መደራጀት አለመቻላችን እንጂ እነሱ እኮ አልቆላቸዋል፤ በንፋስም የሚወድቁ ይመስለኛል፡፡ የሚጥላቸው ቢጠፋ በውነትም በራሳቸው ሳይገነደሱ አይቀሩም፡፡ ሀገሪቱ በነሲብ መሽቶ ይነጋላታል፡፡ በጠፋ ፍትህ፣ በጠፋ እህል ውኃ፣ በጠፋ መልካም አስተዳደር፣ … እንዲሁ በግምት እንኖራለን እንጂ አንድም ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ የለም፡፡ ባዶ ሀገርና ባዶ መንግሥታዊ መዋቅር፡፡ ኢትዮጵያ መንፈሱ የላሸቀ ሕዝብና ተስፋ ያጣ ትውልድ የሚርመሰመስባት በከፍተኛ ፍጥነት እየወደመች ያለች ሀገር ናት፡፡ ለነፃነቷ ቆመናል የምትሉ ቶሎ ድረሱላት፡፡…

ሦስታችን ብዙ ተወያየን፤ ችግሩ ግን ወዲህ ነው፡፡

አንድ ወቅት ዐይጦች ተሰበሰቡ አሉ፡፡  አንድ ዕድሜ ጠገብ አረጋዊ ዐይጥም እንዲህ ሲሉ ጉባኤውን ከፈቱ አሉ፤ “ጎበዝና ጎበዛዝት ማኅበረ-ዐይጥ! እንኳን ደህና መጣችሁ፡፡ የዛሬው ጉባኤያችን የሚያተኩረው የዘመናት ባሕርያዊ ጠላታችንን የድመትን ጥቃት እንዴት መከላከል እንደምንችል በመዘየዱ ዙሪያ ነው፡፡ በድመቶች ጥቃት ያልደረሰበት ዐይጥ መቼም በመካከላችን ይገኛል ብዬ አላምንም፤ ልጁን፣ አባቱን፣ እናቱን፣ ወንድሙን፣ አክስቱን ወይ አጎቱን በድመት ያላጣ ዐይጥ በመካከላችን ይኖራል? በጭራሽ አይኖርም፡፡ እናስ? ምን ብናደርግ ይሻላል?…”

ውይይቱ ጦፎ ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም በድመቶች አንገት ላይ ቃጭል በማሰር ዐይጦችን ሊለቅሙ ሲመጡ ቃጭሉ ይጮሃልና በዚህ የማስጠንቀቂያ ደወል ማኅበረ-ዐይጥ ወደየጉድጓዷ እንድትገባ ቢደረግ ጥሩ እንደሆነ ስለታመነበት ይህ ሃሳብ በአብዛኛው ውሳኔ-ዐይጥ አለፈና ፀደቀ፡፡ ጉባኤው በውሳኔው አጨብጭቦ ሊበተን ሲል ግን አንዲት ብልህና አስተዋይ ዐይጥ ጥያቄ እንዳላትና መናገር እንደምትፈልግ ለመድረክ መሪው የተከበረ ዐይጥ አሳወቀች፡፡ ቀጠለች – “ሃሳቡና ውሳኔው በመሠረቱ በጣም ቆንጆ ነው፡፡ ነገር ግን ማነው ይህን ቃጭል በድመቶች አንገት ላይ የሚያስር?” – ጉባኤተኛው በጥሞና ያላሰበበት ጥያቄ ነበርና ውሳኔው በእንጥልጥል እንዲቆይ ተደርጎ የዕለቱ ስብሰባ አለውጤት ተበተነ፡፡

እኛስ? ከግርጌ እስከራስጌ በዘረኝነት ደዌ በበሰበሰና በገለማ ወያኔያዊ የአፓርታይድ  ሥርዓት እየተቀጠቀጥን እንኑር ወይንስ “ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት” ብለን ሁላችንም በሰ-ሰዓት(ወታደራዊ ቃል ነው) በመነሣት ቢያንስ ለልጆቻችን የምትሆን ሀገር እንፍጠር? የአሁኑ ጥያቄ በሼክሽፒራዊ አገላለጽ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄ ነው፡፡ ሀገራችን ከዚህ በላይ ልትዋረድ አትችልም፡፡ ወያኔዎች ጥምብርኩሳችንን አውጥተውታል፤ ያበለሻሹትን ነገር ለማቃናት ራሱ በጣም ብዙ ዓመታትን ይፈጅብናል – ዛሬ ማታ እንኳን ነፃነትን ብናገኝ ማለቴ ነው፡፡

(ትዝ ያለኝን አንድ ነገር በቅንፍ ልጡቁምና ላብቃ – ሰሞኑን ወደ አንድ የምርት ማሣያና መሸጫ መንግሥታዊ ግቢ ከጓደኞቼ ሄጄ ነበር፡፡ በግቢው ብዙ ድንኳኖች ተጥለው ንግድ ይጧጧፋል፡፡ ጥሎብኝ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሰዎችን ነገዳዊ ማንነት እቃኛለሁ፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ በታዘብኩት ነገር እጅግ አፈርኩ፤ ደነገጥኩም፡፡ አብሮኝ የነበረ አንድ ሰሜነኛ ጓደኛየ ራሱ በውስጡ ሣያፍር አልቀረም፤ ከሞላ ጎደል የሁሉም ድንኳኖች ባለቤቶች ትግርኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ቦታው ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚሉት ስለሆነና ኤግዚቢሽኑም እስከ ልደታ አካባቢ ስለሚቆይ ማንም ሰው ሄዶ ማረጋገጥ ይችላል፤ በመዋሸት የምጠቀመው ነገር የለምና አልዋሸኋችሁም፡፡ ግን ለምን እንዲህ ያለ ጭፍን ያለ መድሎ ይደረጋል? ሌሎች አላመለከቱ ሆነው ነው ወይንስ ዕድሉ ተነፍጓቸው ይሆን? ጤነኛ ነን የምትሉ የሕወሓት አባላት ይህን ዓይነቱን ዐይን ያወጣና መረን የለቀቀ አድልዖ ተመልከቱና ወደኅሊናችሁ በመመለስ በመጠኑም ቢሆን ለማስመሰል እንዲሞከር ጥረት አድርጉ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ ሁሉም ያልፋል፤ ትዝብትና ማኅበራዊ ቁስል ግን ዝንታለሙን እየነፈረቀ ሲያገረሽ ይኖራል፡፡ አብረው በኖሩና በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መካከል እንዲህ ያለ ከፋፋይ ሥርዓት አበጅቶ ዜጎች የጎሪጥ እንዲተያዩና “የኔ ጊዜ” “ያንተ ጊዜ” በሚል ጎራ ለይተው፣ ቀን ቆርጠው እንዲበዳደሉ ማድረግ ነውር ብቻ ሣይሆን በታሪክ የሚያስጠይቅ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ወያኔዎች ሆይ! ምክሬ ያጥፋችና ሃይማኖትም ይኑራችሁ ግዴላችሁም፡፡ ዘመናችሁ የመሸና የጨላለመ ቢመስልም ግዴላችሁም አሁንም ቢሆን ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ከብቶች ብቻ ናቸው የባሕርይ ለውጥ ሳያሳዩ የሚያረጁና የሚሞቱ፡፡ እናንተ ግን ሰው ስለሆናችሁ – ከሰውም ማነስ የለባችሁምና ቢያንስ አሁን እንኳን እንስሳዊ ባሕርያችሁን ለመለወጥ ሞክሩ፡፡ ለአእምሮ ትንሽ ጊዜ ሰጥቶ እንዲያስብ ማድረግ እኮ ነው – ለዚህ ትልቅ ፍጡር ዕድል ስጡት – እስካሁን  ከርሳችሁ ውስጥ ወሽቃችሁት ስትጨቁኑት ነበር – አሁን ግን ለርሱም ፋታ ስጡት፤ ዐውሬነት ይብቃችሁ፤ ክፋትን የዘወትር ልብስ ማድረግ አይሰለችም? ከስሜት ወጥታችሁ ለአንጎላችሁ ጊዜ ከሰጣችሁት የእስካሁኑ ሸፋፋና ወልጋዳ አመጣጣችሁ ሁሉ ቁልጭ ብሎ ይታያችሁና ወደ ደጉ መንገድ ትመለሳላችሁ – እኛስ ብንሆን አናሳዝናችሁም? በጋራ ሀገራችን እናንተ እንዲህ ስትዘባነኑ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ስናለቅስና ዕንባችንን ወደላይ ስንረጭ ለናንተስ ደግ ነው? “ልጅ አይውጣላችሁ! ጥቁር ውሻ ውለዱ! ኤ! የናንተን መጨረሻ ያሳየኝ!…” ተብሎ መረገምስ የኋላ ኋላ መቅሰፍትን እንጂ በረከትን የሚያመጣ ይመስላችኋል? በእናንተ ሰበብ ቅኑና ደጉ የትግራይ ሕዝብስ ለምን በቀጣይ ታሪክና በተከታታይ ትውልዶች እንዲወቀስ ታደርጋላችሁ? ኧረ ልብ ግዙ! ጭንቀቴ ስለናንተም ነው – ለኛ ብቻ እንዳይመስላችሁ – ‹ቀኝ ኋላ ዙሩ›ም ከአሁኑ ባልተናነሰ ሊያሳስበን ይገባል፤”የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ – አዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽም አልወጣ” ሲባል አልሰማችሁ ይሆን? ቸር ክራሞት ለሁላችንም፡፡)

 

 
Received on Tue May 31 2016 - 14:44:32 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved