እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል
እንባ ከየት አባቱ
ደርቋል ከረጢቱ:
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እያለቀሰች መከረኛ ነብሴ::
(በአሉ ግርማ “ኦሮማይ”)
ምነው! ፈጣሪ አምላክ!
አላለቅስም ያልኩት …
እንባ የፈሪ ነው ብዬ ዋጥ ያ’ረኩት፣
አይቻል ተችሎኝ ይዤው የከረምኩት፣
ገንፍሎ ወጣና እንባዬ ፈሰሰ
ጉንጮቼን ሰንጥቆ ፌቴን አዳረሰ
በዛ እንባዬ መሀል አንገቴን አቅንቼ
ለፈጣሪ ጮኽኩኝ! እጆቼን ዘርግቼ
ምነው? ፈጣሪ አምላክ ምነው! ረሳኸን
ምነው! ይሄን በደል አላይልን አልከን
ምነው? የኛን ጩኸት ሰምተህ ጨከንክብን
ብዬ ወተውትኩት አልኩበት እዬዬ
አሁንም ይፈሳል አልቆመም እንባዬ
ምነው! ፈጣሪ አምላክ! …
ወለላዬ
የዛሬ 25 ዓመት ህወሃት የጀመረው በዚህ ነበር – ሜክሲኮ አደባባይ! አደባባዩ የከተማ ቀላል ባቡር ሃዲድ በሚል ሰንካላ ምክንያት አፍርሰውታል! መታሰቢያውን አጥፍተውታል! ወገን አስፋልት ላይ በደም ተነክሮ ተዘርግቷል፣ የህወሃት አጋዚ አስከሬን ይጠብቃል፣ ታክሲዋ አደባባዩን ዞራ ወደ ሳር ቤት ወይም ወደ ብሔራዊ መስመር ትሄዳለች፣ መንገደኞች አስፋልት እያቋረጡ ወደ ጉዳያቸው ይጣደፋሉ፣ ነጯ መኪናም ወደ ሆቴል ዲአፍሪክ መስመር … ወገን ግን በደም ተነክሯል! ህወሃት አሁንም ይገድላል፣ አሁንም ደም ማፍሰስ አልበቃውም! ሁልጊዜ ግን አይሆንም!