September 13, 2016
መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃገራችን ከሚታዎቁ አንጋፋ የቢራ ፋብሪካዎች አንዱና ቀደምት በሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ የህወሃት ባለስልጣናት የፋብሪካውን ቁልፍ ቦታዎች በአባላቱ በመቆጣጠር ከፍተኛ ምዝበራ እያካሄደቡት መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል።
ከሰማኒያ ዓመታት በፊት የተመሰረተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሃያ ሺህ ካሬ ሜትር ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን
ከሶስት ሽህ በላይ ሰራተኞች አሉት።
ድርጅቱ ከመንግስት ወደ ግል ከተዛወረበት ጊዜ አንስቶ በፈረንሳዊ ባለሃብትነት የሚተዳደር ቢሆንም በፋብሪካው ውስጥ በከፍተኛ አመራር ላይ የተቀመጡት የህውሃት አባላት ከሚፈጽሙት የገንዘብ ዝርፊያ በተጨማሪ፣ ለድርጅቱ ገጽታ ግንባታ እየተጠቀሙበት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱን ከሚመሩት የህወሃት ሰዎች መካከል የማስታወቂያ ክፍል ሃላፊው አቶ ኢሳያስ አደራ አንዱ ሲሆኑ፣ ግለሰቡ ወደ ድርጅቱ ከገቡ በኋላ በማስታወቂያ ክፍል ኃላፊነት በመስራት ላይ ናቸው። ግለሰቡ ለማስተዋወቂያ በሚል ወደ ፋብሪካውተገዝተው ከገቡ በኋላ ለደንበኞች በስጦታ ለሚሰጡ ልዩ ልዩ ወንበሮች ፣ብርጭቆዎች፣ ጠረጴዛዎች እንዲሁም በሚሰሩ ቢል ቦርዶች እና ልዩ ልዩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች በሚካሄደው የጫራታ ሂደት ከፍተኛ ሃብት ማከበታቸውን የኩባንያው ተቆርቋሪ ምንጮች ይገልጻሉ።
ከቢጂአይ ኩባንያ ጋር በርካታ የማስታወቂያ “ባነሮችን” እና በፋብሪካው ውስጥ ለሚያገለግሉ መኪኖች የሚለጠፉ ስቲከሮችን ለረጂም ጊዜ በመስራት የሚታወቀው
“ፓንተር” የተባለው ድርጅት የአቶ ኢሳያስ ሲሆን፣ በዙሪያቸው ባሉ የህውሃትአባሎች በመታገዝ በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከኩባንያው እንደሚዘረፍ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ኩባንያውን በፋይናንስ ኃላፊነት በመምራት ላይ የሚገኙት ሌላው የህውሃት አባል አቶ ቴዎድሮስ ሲሆኑ ፣ የኩባንያውን ምርቶች ከቦታ ቦታ የሚያጓጉዙ ከባድና ቀላል መኪኖችን በኮንትራት ለማሰማራት ከ ባለንብረቶች ጋር በሚያደርጉት ያልተገባድርድር ከፍተኛ ሃብት በአጭር ጊዜ ያካበቱ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
አቶ ቴዎድሮስ ወደ ድርጅቱ ሲገቡ ምንም ሃብት ያልነበራቸው ሲሆን፣ በህገወጥ መንገድ ባገኙት ገንዘብና የህውሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ባመቻቹላቸው መንገድ ተጠቅመው ከሃያ በላይ “ኢሮ ትራከር” በመባል የሚታዎቁ ከባድ የጭነት መኪናዎችን
ከቀረጥ ነጻ በማስገባት አብዛኛውን የኩባንያው ምርቶች በማመላለስ ከፍተኛ ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው።
ግለሰቡ በኩባንያው ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የባለቤታቸውን ቤተሰቦች ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን ይዘው እንዲሰሩ በማድረግ ኩባንያውን የቤተሰብ ድርጅት
እንዲሆን አድርገውታል፡፡ኩባንያውን በበላይነት ከተቆጣጠሩት የህውሃት አባላት መካከል ሌላው የፋብሪካው የአስተዳደር ኃላፊ በመሆን ትልቁን ሚና
የሚጫወቱት አቶ ፍትኃነገስት ሲሆኑ፣ በአስተዳደሩ ውስጥ የህውሃት አባላትን ያለ ችሎታቸው ከፍተኛ ቦታ በመስጠትያልተገባ ጥቅም እንዲያካብቱ በማድረግ
በሰራተኛው መካከል ከፍተኛ አድልዎ በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ይገልጻሉ።
አስተዳዳሪው በስራ ድክመት የሚወርዱ የህውሃት አባሎች ተመልሰው ወደ ላይ እንዲወጡ፣ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ምንም አይነት እድገት እንዳያገኙ በማድረግ
በፋብሪካው ውስጥ ፍጹም የህውሃት የበላይነት እንዲሰፍን ጠንክረው በመስራትከፍተኛ በደል እየፈጸሙ ነው ሲሉ ምንጮች ያክላሉ።
ፋብሪካው ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገውን ግዥ በበላይነት የሚቆጣጠሩት አቶ ዘርዖም ደግሞ ግዥውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ከተለያዩ ኩባንያዎች
ጋር በሚያደርጉት የግዢ ድርድር፣ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ሃብት በማካበት የሁለትመኖሪያ ቤቶች ባለንብረት ሆነዋል።
አቶ ዘርዖም በድርጅቱ ውስጥ ከሚሰሩ የህውሃት አባል አመራሮች ጋር በመመሳጠር ከሚሰሩት ስራ በተጨማሪ፣ አንድ “አባይ” በመባል የምትጠራ ከሶስት መቶ ሽህ
በላይ የምታወጣ የቤት መኪና በሃሰት ተበላሽታለች በሚል በአስር ሽህ ብርእንዲሸጥላቸው አድርገዋል፡፡
ድርጅቱ በጡረታ ለሚገለሉ ከፍተኛ አመራሮቹ የሚፈቅደውን የመኪና ስጦታ ዕድል በማግኘት የቲዮታ ፕራዶ መኪና ለግላቸው እንዲጠቀሙ የተደረገ ሲሆን፣ ጡረታ
ከወጡ በኋላም ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደርጎ የዝርፊያው ሰንሰለት እንዳይበጥ ተደርጓል በማለት ምንጮች ይገልጻሉ።
በህውሃት ሰዎች የሚተዳደረው የጭነት ማመላለሻ ድርጅት ማህበር ሊቀመንበር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓት የድርጅቱን ምርቶች በአዲስ አበባ ከተማ
የሚያከፋፍሉት የህወሃት አባል አቶ ገብረስላሴ ሲሆኑ ፣ የአዲስ አበባ ከተማናአካባቢዋ የድራፍትና ቢራ ሽያጭ ጠቅላላ ወኪልና ትራንስፖርት አቅራቢ በመሆን ከፍተኛ
ሃብት እንዳካበቱ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
አቶ ገብረስላሴ በተለያዩ መንገዶች በዝርፊያ ባካበቱት ሃብት በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ኦሎምፒያ ከሳንሻይን ህንጻ ጎን አንድ ባለ ስድስ ፎቅ ህንጻ በመገንባት ላይ ናቸው።
ግለሰቡ በርካታ የሙስና ስራዎችን የሚሰሩት የፋብሪካው የፋይናንስ ዘርፍከሚቆጣጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ጋር በማበር መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
የአመራር ቤተሰብ በመሆናቸው ከአሜሪካን ሃገር ለዚሁ ስራ ተጠርተው በመምጣት በመላው አማራ ክልል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራና ድራፍት በማከፋፈል ከፍተኛ ገንዘብ
እንዲያከማቹ ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው የህውሃት አባል የሆኑት ወንድማማቾቹአቶ አብርሃም ተወልደና አቶተመስገን አብርሃም ሲሆኑ፣ ወንድማማቾቹ ከዚህ ስራቸው
ባካበቱት ከፍተኛ ሃብት “ሶቶይስ” በሚል መጠሪያ ለሚታወቀው ሱቅ፣ ከጀርመን ሃገር የህጻናት የመጫዎቻ ዕቃዎችን በማስመጣት በመስራት ላይ መሆናቸውንምንጮች
አስረድተዋል።
ወንድማማቾቹ የህውሃት አባላት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በመውሰድ የሚያከፋፍሉትን ምርት የሽያጭ ገቢ ገንዘብ ወደ ፋብሪካው ከመግባቱ በፊት ከፋብሪካው
ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመመሳጠር የአውስትራሊያ ጣውላ በማስወጣትእንደሚያከፋፍሉ፣ ስራቸው እንዳይጋለጥም ከፋብሪካው የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጋር
ከፍተኛ የጥቅም ቁርኝት መፍጠራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
በአዳማ ከተማ ና አካባቢዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ጠቅላላ አከፋፋይ በመሆን ከፍተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረጉት ሌላው የህውሃት አባል አቶ ገብሬ ሲሆኑ፣ ግለሰቡ
በከተማዋ ቀደም ብለው የፋብሪካውን ምርት ሲያከፋፍሉ የነበሩትን የከተማዋተወላጆች ስራ በመንጠቅ በብቸኝነት እንዲሰሩ ቢጂኤይን የሚመሩ የህውሃት አመራሮች
ማመቻቸታቸውን
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለረጅም ጊዜ የሰሩ ምንጮች ይናገራሉ።
የፋብሪካውን ስራ በአብዛኛው የሚሰሩ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ሲሆኑ፣ በተለይ በፕሮሞተር ስራ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች የህወሃትን ፖሊሲ ለሚደግፉ አርቲስቶች
ብቻ ስፖንሰር እንደሚሆኑና ለህወሃት የፖለቲካ ድጋፍ ለማስገኘት እንደሚጥሩ ምንጮች ያክላሉ። የፋብሪካውን አጠቃላይ የጥበቃ ስራ የሚሰራው “አጋር የጥበቃ ድርጅት”
የሚባለው ተቋም ሲሆን፣ ድርጅቱ ከአሁን በፊት በፖሊስ ኮሚሽነር ክፍል ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት የህወሃት አባል የሆኑት የቀድሞው የአአ ፖሊስ ኪሚሺን ኮሚሽነር
ተስፋዬ መረሳ ንብረት ነው።
በፋብሪካው በተመቻቸላቸው የውስጥ አሰራር መሰረት በፋብሪካው አጠቃላይ የጥበቃ ስራ ላይ የአንድ አካባቢ ተወላጆችን ብዛት መሰማራታቸውን የሚገልጹት
ምንጮች፣ የጥበቃ ድርጅቱ ከፋብሪካው በድብቅ የሚወጡ ዕቃዎችን አመቻችቶ ያለፍተሻ በማስወጣ በኩል የዝርፊያው ተባባሪ መሆኑን የድርጅቱ ነባር ሰራተኞች
ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኩባንያውን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ድርጅቱ በቀረበው ዘገባ ላይ የሚሰጠው አስተያየት ካለው ይዘን እንድምንቀርብ
ለመገለጽ እንወዳለን።