September 14, 2016
መስከረም ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር እና በሰሜን ጎንደሯ እብናት ትናንት መስከረም 3 /2009 ዓም ነጋዴዎች የጀመሩትን የስራ ማቆም አድማ ዛሬም በከፊል የቀጠሉ ሲሆን፣ በዚህ የተበሳጩት የአገዛዙ ካድሬዎች በርካታ የንግድ ድርጅቶችን ለመጨረሻ ጊዜ እያሉ በማሸግ ላይ ናቸው።
አዲሱን ዓመት በትካዜ የተቀበለው የባህር ዳር ህዝብ የታሰሩት ልጆቹ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም መልስ ሊያገኝ አልቻለም። የ25 ዓመታት የአፈና አገዛዝ በቃን የሚል ጠንካራ አቋም የያዘው የከተማው ህዝብ፣ በአስተባባሪዎች በኩል የሚሰጠው የተዛባ መረጃ ግርታን ቢፈጥርበትም የስራ ማቆሙን አድማ በራሱ ጊዜ በመጀመር ተቃውሞውን በመግለጽ ላይ ነው። በአድማው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ እየተሳፈ ሲሆን ፣ የተወሰኑ ቡና ቤቶችና ግሮሰሪዎች ድርጅቶቻቸውን ከከፈቱ በኋላ መልሰው በመዝጋት አድማውን ተቀላቅለዋል፡፡
ዘጋቢያችን በከተማዋ ልዩ ልዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት ወንድሞቻችን በየዕለቱ እየተገደሉ ባሉበት በዚህ ወቅት ሁሉም በመተባበር አንድነቱን ሊያሳይ ይገባል ብለዋል፡፡ አገዛዙ እስካልተወገደ ድረስ ትግሉ አያቆምም ያሉት የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ በተለያዩ የሃገራችን ከተሞች የአረፋን በአል ለማክበር ባዶ እጃቸውን በወጡ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት የተፈጸመው ድብደባና ውክቢያ በእጅጉ እንዳበሳጫቸው ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ደግሞ ‹‹ የስራ ማቆም አድማው እንደሚቀጥል ብናውቅም መቸ እንደሚጀመር ባለማዎቃችን ለስራ ወጥተናል ›› ብለዋል፡፡የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በእያንዳንዱ ባጃጅ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ሃላፊነቱን እንወስዳለን በማለት ቢናገሩም፤ ከአሁን በፊት በህዝቡ እርምጃ ለተወሰደባቸው ባጃጆች ምንም ዓይነት ካሳም ሆነ የጥገና ሽፋን አለመደረጉን አሽከርካሪዎች ተናግረዋል፡፡ ትናንት ምሽትና ዛሬ ደግሞ በበርካታ ሱቆች በር ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሚል ጽሁፍ ሲለጥፉ ታይተዋል፡፡
በማስታወቂያው ላይ “ ይህ የንግድ ድርጅት ከ23/12/08 እስከ 27/12/08 ዓም. ጀምሮ ለደምበኞች አገልግሎት መስጠት ሲገባው ባልታወቀ ምክንያት ለ 5 ቀናት ተዘግቷል እና መስከረም 3/2009 ዓም. ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አረጋግጠናል፡፡በመሆኑም ድርጅቱ በሩን ክፍት አድርጎ ደንበኞችን የማስተናገድ ግዴታ ያለበት መሆኑ ታውቆ በነገው ዕለት በ04/01/09 ዓ/ም ጀምሮ አገልግሎት እንዲሰጥ “ የሚል አስገዳጅ ይዘት ያለው መልክት የሰፈረ ሲሆን፣ ካድሬዎቹ በአንዳንድ ቦታዎች በመደዳ ፣ ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አለፍ አለፍ እያሉ የማስፈራሪያ ደብዳቤውን ለጥፈዋል፡፡
ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ የስራ ማቆም አድማውን በአንድነት ካካሄደ ሊወሰድ የሚችል እርምጃ እንደማይኖርና አንዳንዶች በዚህ ተደናግጠው ለመክፈት እንዳይሞክሩ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ትናንት አባይ ማዶ በሚባል አካባቢ በርካታ ወጣቶች በወታደሮች ታፍሰው መወሰዳቸውም ታውቋል። በእስር ቤት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች የሚገደሉ ወጣቶች መኖራቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በእስቴ ወረዳ ደግሞ የፌደራል ፖሊሶች ዛሬ ሌሊት አበበ ይልማ እና ይታያል ውባንተ የተባሉ ነዋሪዎችን አፍነው ወስደዋል። ውባንተ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ለ14 አመታት ያገለገለ ሲሆን በተፈታ በሁለት ቀናት ውስጥ ተመልሶ ተይዟል። በእብናት ወረዳ ደግሞ የንግድ ድርጅቶቻቸውን የዘጉ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የመስቀል በዓል በመላ አገሪቱ ለተሰውት የነጻነት ሰማእታት ጸሎተ ፍትሃት የሚደረግበት፣ ማንኛውም አይነት ዝማሬ ቀርቶ ህዝቡ ቀኑን በዝምታ እንዲያከብር በአንዳንድ አካባቢዎች ውሳኔ ተላልፏል። ውሳኔው በመላው አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን ምእመናን ጥያቄ አቅርበዋል።