Ethsat.com: በጎንደር እና ባህርዳር የሚካሄደው የስራ ማቆም አድማ ለሁለተኛ ቀን ሲቀጥል በአዲስ ዘመን ደግሞ አድማውን በአጋዚ ወታደሮች ለማስቆም ሙከራ እየተደረገ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 21 Sep 2016 00:18:09 +0200

በጎንደር እና ባህርዳር የሚካሄደው የስራ ማቆም አድማ ለሁለተኛ ቀን ሲቀጥል በአዲስ ዘመን ደግሞ አድማውን በአጋዚ ወታደሮች ለማስቆም ሙከራ እየተደረገ ነው

September 20, 2016

Watch this news:

ESAT Daily News Amsterdam September 20, 2016

http://video.ethsat.com/?p=28602

መስከረም ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ እየቀጠለ ቢሆንም፣ አገዛዙ አድማው እንዲቆም የተለያዩ እርምጃዎን መውሰድ ጀምሯል። ነጋዴዎች እየታሰሩ፣ የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ እንዲሁም ከስራቸው የቀሩ የመንግስት ሰራተኞች እየተመዘገቡ ደሞዛቸው እንደሚቆረጥና ከስራ እንደሚባረሩ ማስጠንቀቂያ እየተጻፈላቸው ነው። በአዲስ ዘመን ደግሞ በሁለተኛው የተቃውሞ ቀን በርካታ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ከተማው ገብተው በጉልበት ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማድረግ ሞክረዋል። ፈቃደኛ ያልሆኑትን ነጋዴዎች እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ወስደዋል።

በጎንደር ከተማ ወታደሮች ደፍረው የሃይል እርምጃ ለመውሰድ አለመቻላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በከተማው የሚታወቁ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል። የመንግስት ስራ ቆሟል። የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆነው ዳሸን ቢራ ሳይቀር በሰራተኞቹ አድማ ምክንያት ምርት አቁሟል።

በባህርዳር ነጋዴዎችን ለማስገደድ የተደረገው ሙከራ ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎ መስከረም 9፣ 2009 ዓም  የንግድ ማህበረሰብ አባላትን በሆምላንድ ሆቴል በመሰብሰብ ለማግባባት ሙከራ ተደርጓል።  የንግዱ ማህበረሰብ ጠንካራ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ስብሰባውን ሲመሩ ለነበሩት ለአቶ ደመቀ መኮንን አቅርቧል።

‹‹በአሁኑ ሰዓት የአማራን ህዝብ እንመራለን የምትሉ ከፍተኛ አመራሮች በእርግጥ አማራ ናችሁ ወይ? ከሆናችሁ የህብረተሰቡ መገደል ፣መድማትና መቁሰል ለምን እናንተንም አይሰማችሁም? ›› የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

‹‹ አሁን ስልጣን ላይ ያላችሁት አመራሮች ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት ስላልቻላችሁ ቦታውን ለተሻሉ ሰዎች ልቀቁ”  በሚል የተሰጠው አስተያየት የነጋዴውን ሙሉ ድጋፍ ያገኘ ነበር።

አቶ ደመቀ እና የከተማዋ ከንቲባ አቶ ላቀ አያሌው የከተማዋ ንግድና ትራንስፖርት ባለስልጣናት የንግዱ ማህበረሰብ  ከተማዋ እንድትረጋጋ ማድረግ እንዳለበት ለማሳሰብ ቢሞክሩም የንግዱ ማህበረሰብ ግን ስርዓቱ በተለያዩ ጊዜያት በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርገውን ጫና እስካላቆመና የህብረተሰቡን ጥያቄ እስካልመለሰ ድረስ በመካሄድ ላይ ያለውን የስራ ማቆም አድማ በሙሉ ልባቸው እንደሚደግፉና በተለያዩ የስራ ማቆም አድማዎችም ተሳታፊ መሆናቸውን እንደማያቋርጡ ግልጽ አድርገዋል።

በሌላ በኩል በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራንና በክልሉ  ባለስልጣናት የሚደረገው ውይይት ፣ ምሁራን በውይይቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደታሰበው መካሄድ አልቻለም: በህዝቡ ላይ በሚካሄደው የጀምላ ግድያ የተሰማቸውን ሃዘን በዝምታ እየገለጹ መሆኑን የሚናገሩት  ምሁራኑ፣  ከዚህ በተጨማሪ ሰብአዊ መብታቸውን በገፈፈ መልኩ ለሁሉም ምሁራን በግል የኢሜይል አድራሻቸው የደረሳቸው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለዝምታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።

ለምሁራኑ በኢሜል በተላከው መልዕክት ላይ  ማንኛውም መንግስትን የሚቃወም ፣ ህብረተሰቡን ወደ አመጽ የሚገፋፋ ንግግር ተናግረው በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች ቢወጣ ተጠያቂ ይሆናል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰፍሯል።

አብዛኛው ምሁራን ስብሰባውን  በዝምታ እየተከታተሉ ሲሆን ፣ አንዳንዶች ስብሰባውን  አቋርጠው መውጣታቸው ታውቋል፡፡

በስብሰባው ላይ በሃያ አምስት አመቱ የተካሄደውን የህውሃት/ኢህአዴግን መልካም ስራ በማቅረብ ለምህራኑ መግለጫ እንዲሰጡ የተመደቡት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሊቀመንበርና የብአዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ናቸው፡፡ አቶ አለምነው በመሩት ስብሰባ ምሁራን መሳለቂያ አድርገዋቸው መዋላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

Received on Tue Sep 20 2016 - 16:57:14 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved