Ethsat.com: ጎንደር ቅዳሜ ገበያ ሱቆችን ለማቃጠል የተንቀሳቀሱ አራት ሰዎች ረቡዕ በቁጥጥር ስር ዋሉ፥ ሌሎች ሱቆችን ለማቃጠል 50 ያክል ሰዎች እንደተሰማሩ ተነግሯል

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 21 Sep 2016 22:51:58 +0200

ጎንደር ቅዳሜ ገበያ ሱቆችን ለማቃጠል የተንቀሳቀሱ አራት ሰዎች ረቡዕ በቁጥጥር ስር ዋሉ፥ ሌሎች ሱቆችን ለማቃጠል 50 ያክል ሰዎች እንደተሰማሩ ተነግሯል

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

September 21, 2016

Watch these News:

ESAT DC Morning News Wed 21 Sep 2016

http://video.ethsat.com/?p=28626

ESAT Daily News Amsterdam September 21, 2016

http://video.ethsat.com/?p=28620

በጎንደር ቅዳሜ ገበያ ያልተቃጠሉ ሱቆችን ለማቃጠል ቤንዚን ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ሰዎች ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በጎንደር እንደገና ቁጣ ተቀሰቀሰ። ግለሰቦቹ ከትግራይ ክልል መላካቸውንም ለኢሳት መረጃ ያደረሱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሱቆቹን ሲያቃጥሉ ሲሉ በነዋሪዎች ከተደረሰባቸው በኋላ በፖሊስ እጅ የገቡት አራቱ ግለሰቦች ወዲያውኑ ለፖሊስ በሰጡት መረጃ ለጥፋት ድርጊት የተላኩት እነሱን ጨምሮ 50 ያህል ሰዎች መሆናቸውንም እንዳስረዱም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በግለሰቦቹ ድርጊት የተሳጩትና የቀድሞዎም ቃጠሎ በዚህ ሁኔታ እንደሆነ የተገነዘቡት የአራዳና የቅዳሜ ገበያ አካባቢ የጎንደር ነዋሪዎች በቁጣ አደባባይ ወጥተዋል።

በአካባቢው የሰፈረው የአጋዚ ክፍለጦር ታጣቂ ሃይል በነዋሪው ላይ እየተኮሰ መሆኑን ይህም ማምሻውን መቀጠሉን የኢሳት ምንጮች አብራርተዋል።

በርካታ ወጣቶች መታፈሳቸውም ተብራርቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ የተኩስ ድምጽ ቀጥሏል።

********************************************************************************

በአማራ ክልል ሊካሄዱ የታሰቡ የኢንዱስትሪ ልማቶችን ለመደገፍ የተመደበ 4.5 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መተላለፉ በብዓዴን አባላት ዘንድ ቁጣ ቀሰቀሰ

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

በቅርቡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአማራ ክልል ሊካሄዱ የታሰቡ የኢንዱስትሪ ልማቶችን ለመደገፍ ሲሰጥ የነበረ 4.5 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መተላለፉ በብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዓዴን) አባላትና ደጋፊ ዘንድ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተገለጸ።

የፓርቲው አመራሮች ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ ባካሄዱት ልዩ ጉባዔ ወቅት የዚህ ገንዘብ ዝውውር ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡንና በድርጊቱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ጠንካራ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተሳታፊ እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለክልሎች በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ በአማራ ክልል ለሚካሄዱ የማምረቻና የኢንዱስትሪ ልማት ድጋፎች 4.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና በጀቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበውበት ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወር መደረጉንና ጉዳዩ በፓርቲው ልዩ ስብሰባ ወቅት መከራከሪያ ሆኖ መነሳቱን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የክልሉ ባለስልጣናት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም የብዓዴን አመራር የሆኑት አቶ በረከት ሰምዖን የአማራ ክልል በቂ የፕሮጄክት ቀረጻ ባለማከናወኑ ምክንያት ገንዘቡ ለክልሉ ሳይሰጥ መቅረቱን ምላሽ እንደሰጡ በጉባዔው የተገኙ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።

ይሁንና በርካታ ተሳታፊዎች የብዓዴን አመራሮች ለክልሉ የሚያስቡ ከሆነ ፕሮጄክቱ ስኬታማ እንዲሆነ ለምን ሙያዊ ድጋፍ እንዳልሰጡ ጠንካራ ጥያቄን ማቅረባቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

አቶ በረከት ስምዖን በጀቱ የተሻለ ለሰራ ክልል ተላልፏል ሲሉ የሰጡትን ምላሽ ተከትሎ ተሳታፊዎች ቁጣ ማሰማታቸውን የተናገሩት እማኞች ጉባዔው በልዩነት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ከሃምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ህወሃት በበላይነት እየተቆጣጠራቸው ያሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በዚሁ ጉባዔ መከራከሪያ ሆነው እንደቀረቡም እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

የጄኔራል ሹመቶችን ከአንድ ብሄር ብቻ ስለመሆኑ ተጠይቀው የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ሹመቱ የረጅም አመት የስራ ልምድን ግምት ውስጥ አስገብቶ የተከናወነ እንደሆነ ምላሽ መስጠታቸውም ታውቋል።

*********************************************************************************

ኦህዴድ አቶ ሙክታር ከድርንና ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከሃላፊነት አሰናበተ

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል ለወራት ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሙክታር ከድርንና ምክትል ሊቀመንበሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከሃላፊነት አሰናበተ።

በተሰናበቱት የኦህዴድ አመራሮች ምትክ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉ ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰሞኑን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን እንዲካሄድና በአመራሮቹና በአባላቱ ላይ ግምገማ ማካሄዱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከወራት በፊት አካሄዶት በነበረው ግምገማ ለህዝባዊ ተቃውሞ መፍትሄን አላመጡም ባላቸው አባላትና የክልሉ ሃላፊዎች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ከፓርቲው ሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት አመራሮች በኦህዴድ ማዕከላዊ አባላት ዘንድ መጠነ ሰፊ ግምገማ እንደተካሄደባቸውና አመራሮቹም የቀረቡባቸውን ትችቶች መከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

አቶ ሙክታር ከድር ከፓርቲው ሃላፊነታቸው ቢሰናበቱም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው በሃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ ታውቋል።

ይሁንና የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት በቀጣዩ ወር በሚካሄደው ልዩ ጉባዔ ወቅት አቶ ሙክታርን ከፕሬዚዳንትነት በማንሳት አቶ ለማ መገርሳን የኦህዴድ ሊቀመንበት አድርጎ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

የመንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ላለው ህዝባዊ ተቃውሞ የክልል አመራሮችን ተጠያቄ በማድረግ ሃላፊነታቸውን አልተወጡም ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ለወራት በቆየው የክልሉ ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ ዳኞች እና ሲቪል ሰራተኞች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እንዲነሳ አድርጋችኋል ተብለው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ ፓርቲው አሁንም ድረስ ግምገማን እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።

የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ለበርካታ አመታት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ማገልገላቸው የሚታወስ ነው።

ከክልሉ ለወራት ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሂውማን ራይትስ ዎችና የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልፅ ቆይተዋል።

Received on Wed Sep 21 2016 - 15:31:02 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved