Goolgule.com: የመተማው “የዘር-ፍጅት” ትርክት በደህንነት ተቋሙ የተቀናበረ ነበር

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 29 Sep 2016 14:11:30 +0200

የመተማው “የዘር-ፍጅት” ትርክት በደህንነት ተቋሙ የተቀናበረ ነበር

displaced
 
 

በቅርቡ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ መተማ-ዮሀንስ አካባቢ በትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፈፀመ የተባለው ዘርን ያማከለ ጥቃት ሆነ ተብሎ በፀጥታ ሰራተኞች የተቀነባበረ እንደነበረ ጉዳዩን በቅርብ የመረመሩ የዲፕሎማቲክ ምንጮች መሰከሩ።

አጋጣሚውን የትግራይ ክልል መንግስት አልያም የሀገሪቱ የደህንነት ባለስልጣናት “የዘር-ፍጅት አደጋ” እንደተከሰተ አድርገው በማቅረብ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሀዘኔታና ድጋፍ ለማግኘት ሙከራ ማድረጋቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል።

የዋዜማ ሁነኛ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ባደረሱን መረጃ – ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት በስፍራው የነበሩ የረድኤት ስራተኞች፣ ከድርጊቱ በኋላ ወደ ስፍራው ያመሩ ሁለት አጣሪ ቡድኖችና የአማራ ክልል መንግስት ባልስልጣናት የደረሱበት መደምደሚያ፣ የመንግስት የደህንነት ሰራተኞች በበላይ አለቆቻቸው ትዕዛዝ መሰረት የትግራይ ተወላጆች ሸሽተው ወደ ሱዳን እንዲገቡ አድርገዋል።

ሽሽቱ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ውጥረት እንደነበረ ግን ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ላይ በተለይ ያነጣጠረ እንዳልነበረ ኋላ ግን በርካታ ትግርኛ ተናጋሪዎች ሽሽት መጀመራቸው ድንጋጤን ፈጥሮ እንደነበር ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ ዲፕሎማት በፃፉት የውስጥ ስነድ ላይ ገልፀዋል።

ይህን ጉዳይ ማጣራት ያስፈለገው የተባለው እውነት ከሆነ ችግሩን ለመቀልበስ በማለም እንደነበር ሰነዱ በመግቢያው ያትታል።

የትግርኛ ተወላጆቹ ሽሽት ከመጀመራቸው በፊት ፀጉረ – ልውጥ የፀጥታ ሰራተኞች ወደስፍራው መድረሳቸውንና የአካባቢው (የአማራ ክልል ባለስልጣናት) ስዎች በመኪና ተጭነው እስኪወጡ የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር ምስክርነት ሰጥተዋል። የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ከአካባቢው ሲወጡና ጉዞ ሲጀምሩ በደህንነት ሰራተኞቹ ፊልም መቀረፃቸውን መመልከታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ቢያንስ ሶስት መኖሪያ ቤቶች ላይ ነዋሪዎቹ ከወጡ በኋላ ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት መፈፀሙን የሚያሳይ መረጃ አለ።

በወቅቱ በስፍራው የነበሩ ሶስት የረድዔት ሰራተኞች በአጋጣሚ ሰዎች የተሰባሰቡበት አካባቢ በመገኘታቸው ለአራት ሰዓታት በአነስተኛ ምግብ ቤት ውስጥ ታግተው እንደነበርና ስልኮቻቸውና ካሜራቸው ላይ የነበሩ ምስሎች መበርበራቸውን ተናግረዋል።

ይህን ጉዳይ ለማጣራት ወደ ስፍራው የተላኩ ሁለት የተለያዩ መረጃ አሰባሳቢዎች ያገኙት መረጃ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ሽሽት በተደራጀ መልክ መካሄዱን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

“አካባቢው ለድንበር ቅርብ በመሆኑ ከፍተኛ ወታደራዊና የደህንነት ሰራተኞች የሚንቀሳቀሱበት ሆኖ ሳለ ለምን ሌሎች የደህንነት ሰራተኞች ከመቀሌ ወይም ከአዲስ አበባ ወደ ስፍራው እንደተላኩ ግልፅ አይደለም” ይላሉ መረጃ አሰባሳቢዎቹ።

“በትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ ስጋትና ፍራቻ መኖሩን መካድ አይቻልም ይሁንና ኢትዮጵያውያን በአመዛኙ ለማህበራዊ ትስስር በሚሰጡት ልዩ ዋጋ ይህ አብሮነት እንዲናጋ የሚፈቅዱ አይደሉም፣ በመተማ የነበረው ሁኔታም በዚህ መነፅር መታየት ይኖርበታል” ይላሉ ዲፕሎማቱ በሰነዱ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት።

“እስካሁን ባለን መረጃ ጥቃት የተፈፀመባቸው የትግርኛ ተናጋሪዎች በቁጥር እጅግ ኢምንት ናቸው። በአብዛኛው ገና ለገና ጥቃት ይፈፀምብኛ በሚል ስጋት ከባህር ዳር ጎንደርና የኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች መኖሪያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባና ወደ ትግራይ ያመሩ መኖራቸውን እናውቃለን” ይላል ሪፖርቱ ።

“ይህን ስጋት የደህንነት ተቋሙ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊጠቀምበት መሞከሩን በቂ ፍንጮች አሉ” ይላል ሰነዱ። “ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታና የትግራይ ተወላጆችን ከጎኑ ለማሰለፍ ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው”

“ለሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሀገሪቱ በዘር ፍጅት አደጋ አፋፍ ላይ እንዳለች አስመስሎ በማሳየት በሀገሪቱ ያለው ተቃውሞ ‘አደጋ ያመጣል’ የሚል ስጋት የማጫር ዕቅድም ሊኖረው ይችላል። ይህን ዋናው የደህንነት መስሪያ ቤት ወይም የትግራይ ክልል በተናጠል/ በጋራ ያደረገው መሆኑን መረጋገጥ አልቻልንም”

የትግራይ ክልል አልያም የማዕከላዊ መንግስት የዘር ፍጅት አደጋ ማንዣበቡን በመተማው አጋጣሚ በማሳየት ራሱን አረጋጊና የሰላም ዋስትና የማድረግ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ያለ ኢህአዴግ አመራር ሀገሪቱ ወደ እልቂት እንደምትገባ ለማመላከት ዓላማ ሊያውለው መሞከሩን ዲፕሎማቱ በሰጡት አስተያየት አስፍረዋል።

በጎንደር ተቃውሞ ተባብሶ በነበረበት ሀምሌ 2008 የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳትና) በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል (VOA ላይ የዘር ፍጅት ቅስቀሳ አድርገውብኛል ሲል ለአሜሪካ መንግስት ክስ አቅርቦ ነበር። ክሱ ተቀባይነት አላገኘም።

የኢትዮጵያ ደህንነት መስሪያ ቤት ራሱ ፈንጂ በማፈንዳት ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎችንና ኤርትራን ይወነጅል እንደነበረ ከዚህ ቀደም ይፋ የሆነ የአሜሪካምስጢራዊ የዲፕሎማቲክ ሰነድ መግለፁ ይታወሳል። (ምንጭ: ዋዜማ ራዲዮ)

(ፎቶ: የትግራይ ተወላጆች በዘር ፍጅት አደጋ ሊደርስባቸው በመሆኑ መፈናቀላቸው የሚያሳይ – Tigrai Online)

Received on Thu Sep 29 2016 - 06:50:34 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved