ወቅታዊ ሪፖርታዥ
በሳምንቱ መግቢያ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ እና ድርድር እንዲደረግ ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል። አምስቱ የሕወሃት ቁንጮዎች ትእቢት የተሞላበት ምላሽ ነው የሰጡት። ከድርድር ይልቅ ከሕዝብ ጋር ጦርነት መግጠምን መርጠዋል።
አብዛኛው የፖሊስ እና የሃገር መከላከያ ሰራዊቱ “ሕዝብ ላይ አልተኩስም” ማለታቸው የህወሃት አመራርን ጭንቅ ውስጥ አስገብተውታል።
አዲስ አበባ ተቆላልፋለች። በአራቱም አቅጣጫ በኩል የሚገባም የሚወጣም የለም። መንገዶች በሙሉ ተዘጋግተዋል። ስልክ እና ኢንተርኔት ጠፍቷል።
በአዲስ አበባ ዙርያ ባሉ ከተሞች ሰኞ መስከረም 23 ቀን የተጀመረውን ሕዝባዊ አመጽ ለማዳፈን በህወሃት የተወሰደው የአፈሳ እርምጃ አመጹን አላቆመውም። ሰኞ ማምሻውን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታፍሰው ወዳልታወቀ ስፍራ በመወሰዳቸው ሳብያ አመጹ በዛሬው እለት ተባብሶ ቀጥሏል። የአካባቢ ፖሊሶችም ከሕዝብ ጋር በመሆን በአመጹ እየተሳተፉ በመሆኑ የስራአቱን ቁንጮዎች ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል።
ሰበታ ላይ የነበረው የቱርክ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና የሃይል ማመንጫ ኩባንያ በትናንትናው እለት መውደሙን ሮይተርስ ከስፍራው ዘግቧል። በሆለታ በነበረው አመጽ ሚስ ሻሮን ሬይ የተባለች አሜሪካው የግብርና ኤክፐርት መገደልዋንም ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር። ይህ ዜና በአለም የመገናኛ ብዙሃን ከተሰማ በኋላ ህወሃት የስልክ እና የኢንተርነት አገልሎት እንዲቋረጥ አድርጓል። የአመጹ ዜና ወደ ሌሎች እንዳይሰራጭ ታቅዶ የተደረገው ይህ ድርጊታቸው የህዝብን ቁጣ እያበረታው መጥቶ ካድሬዎችን እየለቀሙ መምታት እንዲጀመር አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሕዝብ በጋራ ተነስቶ የህወሃት ተላላኪዎችን እያስጠነቀቀ ሲሆን እንቢ ያሉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገናል። የወንጂ ስኳር ፍብሪካ ከፉተኛ ቃጠሎ የደረሰበት ሲሆን፣ ኩሪፉቱ የሼክ አላዓሙዲን የከብት ማድለቢያ ንብረት ሙሉ በሙሉ ወድሟል። በቀርሳ ወረዳ አንድ የህወሃት ተላላኪ በህዝብ ተገድሏል፣ በሆሮ ጉድሩ እና በጉጂም የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ላይ ሕዝብ እርምጃ ወስዶባቸዋል። በድሬ ዳዋ ዲፖ ጋዝ ስቴሽን በእሳት ጋይቷል።
የናይጄሪያዊው ኪሎ ዲንጎቴ ንብረት የነበረው ዲንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ በህዝባዊ አመጽ መውደሙን የአፍሪካ ሜድያ ኔትወርክ ዘግቧል። ጉጂ ዞን ያለው የሼክ አላሙዲን የወርቅ ማእድን በትላንትናው እለት መውደሙን ማህበራዊ ድረ-ገጾች ዘግበዋል።
ባዶ እጁን እየወጣ ሲገደል የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ አሁን ራሱን ራሱን የሚከላከልበት መሳርያ እየያዘ መውጣቱን የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአለም ገና ዳሽን ባንክ እና ከገዥው ፓርቲ ጋር ንክኪ ያላቸው መኪናዎች ተቃጥለዋል።
በአርሲ፣ በመቱ እና በጂማ በተማሪዎች የተቀሰቀሰው አመጽ እንደቀጠለ ነው። የጅማ ወህኒ ቤት ተቃጥሎ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ የተደረገው ትላንት ምሽት ላይ ነበር።
አዲስ አበባ ከእሬቻው እልቂት በኋላ የሙት ከተማ መስላለች። የንግድ እንቀስቃሴ በሙሉ ቆሟል። ሱቆች ዝግ ናቸው፣ የህዝብ ትራንስፖርትም የለም። መርካቶም ጸጥ-ረጭ እንዳለች ነው። በዛሬው እለት ታክሲ በከተማዋ ባለመኖሩ አብዛኛው ሰው ስራ አልገባም። ከተወሰኑ የግል ትምህርት ቤቶች በስተቀር የመንግስት ትምህርት ቤቶች አሁንም ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ተወስኗል። አንዳንድ የግል ት/ቤቶች ወላጆችንን ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት እንዳይልኩ እየመከሩ ይገኛሉ።
ለአዲስ ተማሪዎች ጥሪ ያደረገው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው። ሌላዎቹ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ተማሪ ገብቶ የመማሩ ጉዳይ የሚታሰብ አይደለም።
በደቡብ ወደ ሻሸመኔ እና ወደ አዋሳ የሚወስደው መንገድ እሁድ ጀምሮ ዝግ ነው። በሰሜን ሱልልታ፣ ለገዳዲ፣ ቦሌ ቡልቡላ፤ በም እራብ በአስኮ፣ በቡራዩ፣ ሰበታ፣ አለምገና፣ ብስራተ-ገብሬል፣ አየር ጤና፣ ወሊሶ፣ ወደ ሆሳዕና እና ጅማ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ተዘግተዋል። በዚያ የሚተላለፍ ተሽከርካሪ ቢገኝ የድንጋይ ናዳ ይወርድበታል።
አጋዚ ይህ ሕዝባዊ አመጽ ከቁጥጥር ውጪ ስለሆነበት አዲስ አበባን ብቻ ከብቦ እየጠበቀ፣ ንጹሃን ዜጋን በማፈስ ስራ ላይ ተጠምዷል።
ህወሃት በአማራው ሕዝብ ላይ በይፋ ያወጀው ጦርነት አልተሳካም። ራሱን ከመከላከል አልፎ አካባቢውን ከአጋዚ ነጻ እይደረገ ይገኛል። በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ነጻ ወጥተዋል። የባህርዳር ዩንቨርስቲ እስካሁን እንደተከበበ ነው። የኮሶበር ህዝብ የዳሽን ቢራን ጭኖ የነበረ ከባድ መኪና ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል።
በባህር ዳር ወጣቶችን ሲያሰቃይ የነበረ የማንኩሳ ተወላጅ ማንነቱ ባልታወቀ አካል ተገድሎ መገኘቱ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተዘግቧል።
የህወሃት ባለስልጣናት አሸንዳን በርችት፣ እሬቻን በጥይት ካስተናገዱ በኋላ በወገን ላይ በደረሰው አሰቃቂ እልቂት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ ሃዘን ላይ ነበር።
ብሄራው ሃዘን ላይ የነበረው ህዝብ ወደ ብሄራዊ አመጽ የገባ ይመስላል። ሰላማዊ ሕዝብን እንደ ግራዚያኒ፣ እንደ ሞሶሎኒ በጥይት እና በመርዝ ጭስ ከጨረሱ በኋላ በቴሌቭዥን ወጥተው አዝነናል እያሉ፣ ቁስልን የባሰ ሲነካኩበት ከዚህ ውጭ አማራጭ የለም። ሕወሃቶች ይልቁንም ለራሳቸው ይዘኑ። ሰላማዊውን ህዝብ እየጨረሱ ያሉት ሁሉ በተራቸው የሚያለቅሱበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በደም የታጠበ እጃቸው ገና ሳታደርቅ በቴሌቭዥን ወጥተው በሟች አጽም ላይ መቀለዳቸው ሳያንስ በተለመደ የሽብርተኞች ዲስኩር ህዝብ ላይ እጅ መቀሰር ድፍረት ነው።
ግዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል እንጂ እነዚህ ነብሰ-ገዳዮች የእያንዳንዱ ነብስ ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ ነው።
የቢሾፍቱው ግድያ የህወሃት “ጥልቅ ተሃድሶ” ጅማሬ መሆኑ ነው። ግን ህዝብን እየረገጡ ብዙ ሊዘልቁ አይችሉም። ፍም እሳት የሆነ የአመጽ ትውልድ ተፈጥሯል። እነሱ ባሰሩ እና በገደሉ ቁጥር ሚሊዮን ሆኖ የሚነሳ ትውልድ። ምንም ነገር ሳይዝ በድምጹ ብቻ የሚያስፈራ ትውልድ። ህዝብን ጠላት አድርጎ ለመግዛት የሚሞክር ስርዓት ይህንን ሁሉ ህዝብ ከቶውንም ገድሎ ሊጨርስ አይችልም።
ክንፉ አሰፋ