October 14, 2016
watch this.
ESAT DC Morning News Fri 14 Oct 2016
ESAT Daily News Amsterdam October 14,2016
http://video.ethsat.com/?p=29473ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዛሬው እለት በ9 ኦራል መኪኖች የተጫኑ ወታደሮች ዶጋው ገብተዋል። በከፍተኛ የቁጣ ስሜት ውስጥ የሚገኙት ወታደሮች ህዝቡ የኢሳት ስርጭቶችን እንዳይመለከት ለማድረግ በከተማዋ ያሉ ዲሾችን ሲነቃቅሉ ውለዋል።
ነዋሪዎች እንደገለጹት ትናንት የግለሰቦችን የጦር መሳሪያዎች ለማስፈታት እንዲሁም በአካባቢው የተደራጁ ሃይሎች አሉ በሚል ከጎንደር የተንቀሳቀሰው የመከላከያ ሰራዊት፣ ዶጋው በረሃ ላይ ሲደርስ ከነጻነት ተዋጊዮች ተኩስ ተከፍቶበታል። ታዋቂው አርበኛ አበራ ጎባው የመከላከያ ነዳጅ የጫነን መኪና በጥይት መትቶ እንዲገለበጥና እንዲቃጠል ማድረጉን፣ በተከታታይ በነበሩ ፒክ አፕ መኪኖች ላይ እሱና ጓደኞቹ አከታትለው ጥቃት በመሰንዘር በርካታ ወታደሮችን ከገደሉ በሁዋላ፣ ከሁዋላ የነበሩ ወታደሮች በአልሞ መቺ የጦር መሳሪያ መግደላቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
በአካባቢው ሲካሄድ በነበረው ተኩስ በርካታ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የአካባቢው ወጣቶች አካባቢያቸውን ለቀው ጫካ ገብተዋል። አበራ ጎባውን በስርዓት ለመቅበር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ በጧት በርካታ ወታደሮችን የጫኑ 9 ኦራል መኪኖች የገቡ ሲሆን፣ ያገኙዋቸውን ሴቶች ከመደብደብ በተጨማሪ፣ በእየቤቱ የተተከሉ የሳተላይት ዲሾችን ሲነቃቅሉ አርፍደዋል።
ህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚገኙ የግለሰብ የጦር መሳሪያዎችን በመቀማት፣ ኢሳትንና ሌሎችም ከውጭ ሃገራት የሚተላለፉ የዜና ማሰራጫዎችን ወጣቶች በሞባይል ስልኮቻቸው እንዳይመለከቱ በማድረግ እንዲሁም የሳተላይት ዲሾችን በመንቀል፣ የተቃውሞ አስተባባሪ ናቸው ብሎ የሚፈርጃቸውን ሃይሎች በማሰር፣ በስራ ማቆም አድማ የሚሳተፉ ነጋዴዎችን በማፈን እና ሌሎችም እርምጃዎችን በመውሰድ በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመፋን ሙከራ እያደረገ ነው።
የፖለቲካ ተንታኞች አፈናው ብሶትን እየወለደ ተቃውሞውን ያጠናክረዋል እንጅ አያበርደውም በማለት አገዛዙ ራሱን መልሶ እንዲያይ ምክራቸውን እየለገሱ ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት የአፈና እርምጃው ችግሩን ይፈታዋል ብለው እንደማያምኑ ሰሞኑን ባወጡዋቸው መግለጫዎች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ለ4ኛ ቀን በቀጠለው የባህርዳር የስራ ማቆም አድማ ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ነጋዴዎች ታስረዋል። ነጋዴዎቹ ሱቆቻቸውን በግድ እንዲከፍቱ ተደጋጋሚ ጫና ሲደርስባቸው ቢቆይም በአቋማቸው በመጽናት አድማውን ቀጥለውበታል። በዚህ የተበሳጨው ገዢው ፓርቲ ዋና ዋና የሚላቸውን ነጋዴዎች እያፈላለገ በማሰር ላይ ነው።የአዴት ተራ፣ ህንጻ መሳሪያ እና መናኃሪያ አካባቢ ያሉ ኤሌክትሮኒክስ ድርጅት ባለቤቶች በብዛት መታሰራቸው ታውቋል።
የባህርዳር የስራ ማቆም አድማን ተከትሎ የፊታችን ሰኞ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም የ3 ቀን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ጥሪ ቀርቧል። አድማውን የሚያስተባብረው ቡድን፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ለነጻነት በሚደረገው ትግል ተሳታፊ በመሆን አድማውን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
********************************************************************************
በደቡብ ክልል በአንድ ቀን በ3 አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ወታደሮች ቆሰሉ
October 14, 2016
ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ግጭቱን ተከትሎ በበና ኩሌ ወረዳ አልዱባ ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ ሲወድም፣ በበና ኩሌና ሃመር ወረዳዎች አዋሳኝ በሆነው ኤሪያ አንቡሌ ቀበሌ ደግሞ የቱሪስቶች መኪና በጥይት ተመቷል።በሳላማጎ ወረዳ በኃይል-ውኃ/ ኩራዝ 2 ስኳር ፕሮጀክት ማዞሪያ በፖሊሶች ላይ በደረሰ ጥቃት ደግሞ 3 ፖሊሶች ቆስለዋል።
ግጭቶችን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር መ/ር ዓለማዬሁ መኮንን፣ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል። የአካባቢው ህዝብ ለለውጥ ዘግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጥቅምት 2/2009 ዓ.ም በበናኩሌ ወረዳ ርዕሰ መዲና -ቀይአፈር- ከተማ በደቡብ አቅጣጫ በሚገኘው አልዱባ ቀበሌ ወጣቶች ባደረጉት ተቃውሞ ፖሊስ ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ አውድመውታል።
ወጣቶቹ “ ይህ መንግስት በቃው፣ የመንግስት ለውጥ እንፈልጋለን፣ አዲስ መንግስት ይምጣልን” ማለታቸውንና ገበያውም በጊዜ መበተኑ ታውቋል። አስቀድሞ እንደተበተነ በገበያው የነበሩ እማኞች አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ቀን በበናኩሌ ወረዳና በሃመር ወረዳ አዋሳኝ የ -ኤሪያ አንቡሌ ቀበሌ በጉዞ ላይ በነበሩ ቱሪስቶች መኪና ላይ ተኩስ ተከፍቶ መስተዋቱ ተመቷል። መኪናው ላይ ከደረሰው ጉዳት በስተቀር በተጓዦች ላይ አደጋ አልደረሰም፡፡ በወረዳው ያለው ችግር ለሁለት አመታት የዘለቀ ቢሆንም እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።
ከጂንካ በምዕራብ አቅጣጫ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ወደሚገኙበት የሳላማጎ ወረዳ በሚወስደው መንገድ ወደ ኃይሎ ውሓ ወይም ኩራዝ 2 ፕሮጀክት ማዞሪያ ላይ የሀመር ወጣቶች በፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍተው- ጎርኪ፣ አይካሮ እና ሀሰን የሚባሉ ሦስት የፖሊስ አባላትን ሲቆስሉ፣ ስሙ ያልታወቀው 4ኛው ፖሊስ ህይወቱ አልፏል። ሶስቱም ጥቃቶች ግንኙነት አላቸው ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ፣ በአካባቢው የሚካሄደው ተቃውሞ እየጨመረ መምጣቱን ሲታይ፣ ጥቃቶቹና ተቃውሞዎቹ ግንኙነት እንዳላቸው ያመለክታል ብለዋል።
በርካታ አርብቶአደሮችን ያፈናቀለውና ለግጭት መንስኤ የሆነው የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ላቀረብነው ጥያቄ፣ ፕሮጀክቱ ስራ አለመጀመሩንና የአካባቢው ህዝብ ስራ ይጀምራል ብሎ እንደማያምን ገልጸዋል ።