Ethsat.com: አፋኝ የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በወጣ ማግስት የጎንደር ከተማ ህዝብ የመጀመሪያውን ቀን አድማ በተሳካ ሁኔታ አደረገ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 18 Oct 2016 00:23:06 +0200

አፋኝ የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በወጣ ማግስት የጎንደር ከተማ ህዝብ የመጀመሪያውን ቀን አድማ በተሳካ ሁኔታ አደረገ

October 17, 2016

Watch these news:

ESAT DC Morning News Mon 17 Oct 2016

http://video.ethsat.com/?p=29573

ESAT Daily News Amsterdam October 17,2016

http://video.ethsat.com/?p=29564

ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አስተባባሪ ግብረሃይሉ ባለፈው አርብ የጠራውን የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ ዛሬ የከተማ ሱቆች፣ ሆቴሎች እና አገልግሎት ተቋማት ሁሉ ተዘግተው የዋሉ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ከሚንቀሳቀሱ ባጃጆች በስተቀር፣ አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች ስራ አቁመዋል።

“ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ክልክል ነው” የሚል አፋኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በሁዋላ፣ አዋጁን ከምንም ባለመቁጥር በክልሉ የሥራ ማቆም አድማ ሲደረግ ከባህርዳር ከተማ አድማ ቀጥሎ ይህ ሁለተኛው ነው።

ድርጊቱ ያበሳጫቸው የሚመስሉት አገሪቱን በወታደራዊ ሃይል እየመሩዋት ያሉት የእዝ አመራሮች ፣ወታደሮቻቸው የተዘጉ የንግድ ድርጅቶችን እየሰበሩ እንዲያስከፍቱ ጥብቅ ትእዛዝ በመስጠታቸው፣ከሰአት በሁዋላ ድርጅቶችን ለማስከፈት ሙከራ ሲያደርጉ ታይቷል። ይሁን እንጅ አብዛኛው ህዝብ የሚመጣበትን ለመቀበል በመዘጋጀት የመጀመሪያውን አድማ በስኬት አጠናቋል። አገዛዙ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ወንጀል ነው በማለት ያወጣው ድንጋጌ ሳምንት ሳይሞላው ባለፈው ሳምንት ባህርዳር አሁን ደግሞ ጎንደር አድማውን ማድረጋቸው አገዛዙ አፍኖ ለመግዛት የጀመረው ሙከራ እንደማይሳካ ማሳያ ነው በማለት የተቃውሞው አስተባባሪዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤንንና ሌሎች የውጭ የመገናኛ ብዙሃንን እንዳይታዩ ለመከልከል ዲሾችን ለማስወረድ የሞከሩ ካድሬዎች፣ በድንጋይ ተመትተዋል። በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ወታደሮች በብዛት እየተሰማሩ ህዝቡን መግቢያ መውጫ እያሳጡት መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ ለመጀመር ወታደሮች ቀድሞ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በየአካባቢው የተሰማሩ አደራጆች አሳስበዋል።

*******************************************************************************

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክሸፍ ማለት የወያኔን ህልውና መጨረስ ማለት መሆኑን ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ

October 17, 2016

ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ህወሃት መራሹ መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ዛሬ በሰጡት መግለጫ  አዋጁ “ ሰው ሆኖ መኖርን የናፈቀውና ካሁን በኋላ ያለነፃነት በፍጹም አልኖርም ብሎ ፍርሀትን በሚገርም ጀግንነት አሸንፎ ውድ ሕይወቱን እየከፈለና እየታገለ ያለውን፤ ከሞላ ጎደል መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ እንደገና በፍርሀት ቆፈን ውስጥ መልሶ በመክተት ከቀድሞውም በባሰ ባርነት ውስጥ ዘፍቆ ለመግዛት” ታልሞ የወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሁን በኋላ ባርነትን የሚሸከምበት ምንም ጫንቃ የለውም። በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም በፍጹም ተመልሶ የባርነት ሕይወት ውስጥ ሊኖር አይፈቅድም። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የፍትህና የነፃነት ኃይሎች ዋና ተግባር ያላቸውን አቅም ሁሉ አስተባብረውና ነፃነት የራበውንና የጠማውን ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው፤ ጊዜውና ሁኔታው የሚፈቅደውን ተለዋዋጭና ተለማጭ የትግል ስልት እየተጠቀሙ ይህ አዋጅ በፍጹም ተግባራዊ እንዳይሆንና እንዳይሳካ ማድረግ” ይኖርባቸዋል ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ ይህ አዋጅ ተሳካ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ላልተወሰነ ጊዜ በባርነት መቀመቅ ውስጥ እንዲኖር መፍረድ ነው ብለዋል።

ስለዚህም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ ይህን አዋጅ አከሸፍነው ማለት የወያኔ ስርዓት አከተመለከት ማለት በመሆኑ፣ የመጨረሻውን የሞት ሽረት ትግል እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። “ባርነትን በጉልበት ሊጭንብን ጦር ሰብቆ የመጣውን እኩይ ኃይል፤ ምርጫችን ሆኖ ሳይሆን በላያችን ላይ የተጫነ ግዴታ ስለሆነ ከእንግዲህ ገድሎ መሞት እንጂ “በሰላምተኝነት” መሞት የሌለ በመሆኑ፣ ነፃነት የጠማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የነጻነት ሃይሎችን እንዲደግፍ እና እንዲቀላቀል ጠይቀዋል። ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ያስተላለፉት ፕ/ር ብርሃኑ “የዛሬ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የባርነትን ኑሮ ከኛ እንዳያልፍና ወደ ልጆቻችን እንዳይጋባ ማስቆም ታሪክ የጣለብንና በእርግጠኛነት የምንፈጽመው ተግባራችን” ይሆናል ብለዋል።

*******************************************************************************

አዲሱ አፋኝ አዋጅ በወጣ ማግስት ዝርፊያ እየተጧጧፈ ነው

October 17, 2016

ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያሳዩት መላውን የአገሪቱን ህዝብ ለማፈን የወጣው አዋጅ ተግባራዊ ከሆነበት ቀን አንስቶ ፣ በእዙ ሰንሰለት ወይም ኮማንድ ፖስቱ ስር ነን ያሉ የተደራጁ የገዢው ፓርቲ አባላት በባለሃብቶች ቤት እየገቡ በማስፈራራት ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው።

እነዚሁ ታጣቂዎች፣ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ነን በማለት ባለሃብቶችን “ የተቃዋሚ ደጋፊዎች መሆናችሁን ደርሰንብታል፣ ገንዘብ ካመጣችሁ አንነካችሁም “ በመላት ገንዘብ መዝረፍ መጀመራቸውን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሰዎች ተናግረዋል።

ሰሞኑን ከተከናወኑት ዝርፊያዎች መካከል በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ የተፈጸመው ከፍተኛ ነው። ቤቴል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ፣ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ነን ያሉ ግለሰቦች አቶ ኡስማን ከተባሉ ግለሰብ ቤት በመግባት 400 ሺ ብር እና የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ ሞባይል ስልኮችን ወስደዋል። ምሽትና ሌሊት አካባቢ የሚጓዙ ሰዎችን በማስቆም መታወቂያ አሳይ በማለት ኪስ እየበረበሩና ስልኮችን እየቀሙ እየተሰወሩ መሆኑን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ተናግረዋል።

 
Received on Mon Oct 17 2016 - 17:02:10 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved