ሕዝባዊ ቁጣ ያንቀጠቀጠው ህወሃት/ኢህአዴግ በተለምዶ “የሰፈር ጉልበተኛ” የሚባሉ ወጣቶችን ለስለላ ስራ እየመለመለ እንደሆነ ተሰማ። ጥያቄውን ተቀብለው በየሰፈሩ ያሉትን የለውጥ አራማጆች ለመሰለል ፈቃደኛ ያልሆኑ እንደሚታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ከታሰሩት መካከል ከማዕከላዊ የተሰወረው ወጣት ጉዳይ በጥበቃ የተሰማሩትን ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። አዲሱ ምልመላ የቀበሌ የስለላ መዋቅር መሰበሩን አመላካች እንደሆነ ተጠቁሟል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ዋቢዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢህአዴግ ቀደም ሲል “አደገኛ ቦዘኔ” ሲላቸው የነበረውን ወጣቶች ለስለላ ተግባር እየመለመለ ነው። የሚመለመሉት በሰፈር ውስጥ በተደባዳቢነት፣ በጉልበተኛነት የሚታወቁ ናቸው። በየሰፈሩ በተለምዶ “ጉልቤ” የሚባሉትን ወጣቶች የሚመለምሉት የህወሃት ሰዎች ናቸው። አመላመሉ በድንገት ከሚያዘወትሩበት ቦታ ወይም ከመንገድ አለያም ከተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች የሚፈለጉትን “ጉልቤዎች” በማደን ነው።
በየሰፈሩ ኢህአዴግን የሚቃወሙ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን የሚከታተሉና የሚደግፉ፣ እንዲሁም በህቡዕ የድርጅት አባላት በመሆን ተቃውሞዎችን የሚያደራጁ ሰዎችን እንዲሰልሉ የሚመለመሉት ወጣቶች ጠቀም ያለ ክፍያ አላቸው። ቀደም ሲልም ስራ የማይሰሩ ናቸው።
ለጥንቃቄ ሲባል ስሙና አድራሻው እንዲሁም የደህንነት ኃይሎች የት እንደተገናኙት ይፋ ያላደረገው ዘጋቢያቸን ከአንድ ፑል መጫወቻ ቤት ስለተመለመለውና ፈቃደኛ ባለመሆኑ ስለታሰረው ወጣት መጨረሻ አትቷል። ወጣቱ ፑል እየተጫወተ ሳለ ሁለት ሰዎች መጥተው አብረውት ይጫወታሉ። ከዛም ሲወጣ እያሳሳቁ ሻይ አብሯቸው እንዲጠጣ ይጠይቁታል። በድንገት አንድ መኪና ትመጣና አስገብተውት ይጓዛሉ። አንድ አመቺ ቦታ ይዘው ስለመጡበት ጉዳይ ያስረዱታል።
ይህ በሰፈሩ ኃይለኛ የሚባል ወጣት በምንም ዓይነት ሰላይ እንደማይሆንና ጥያቄውን ሊቀበል እንደማይችል ይነግራቸዋል። ከብዙ ንትርክ በኋላ ጉዳዩ ባለመስማማት ሲቋጭ እስረኛ መሆኑ ይነገረውና ወደ ማዕከላዊ ይወስዱታል። ፈቃደኛ ባለመሆኑ ይታሰራል። ቤተሰቦቹና የትዳር ጓደኛው የት እንደገባ ለማወቅ ቢባዝኑም ሊያገኙት አልቻሉም። ሶስት ቀን ሙሉ ፈለገውት ሊያገኙት አልቻሉም። በአራተኛ ቀን ማዕከላዊ ይሄዳሉ። እዛም ስሙን ጠቅሰው ቢጠይቁ እንደሌለ ተነገራቸው።
ተስፋ የቆረጡት ቤተሰቦች ማዕከላዊን ለቀው ሲወጡ አንድ የሚያውቃቸው ሰው ከመካከላቸው አንዱን ጠርቶ ለማንም እንዳይናገር በማስጠንቀቅ የሚፈለገው ወጣት እዚያው ማዕከላዊ እንደሚገኝ ሹክ ይላቸዋል።
እንደመረጃው ምንጮች ከሆነ ወጣቱ ቀደም ሲል ፌደራል ፖሊስ የነበረና “በቃኝ” በማለት የለቀቀ ነው። በሰፈሩ የሚፈራና ጉልበታም ሲሆን ለነገሮች ቅርብ የሆነ ልበ ሙሉ እንደሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። ይህ ወጣት በአምስተኛው ቀን ከማዕከላዊ እስር ቤት ይሰወራል። ወጣቱ እንዴትና በምን በኩል እንደተሰወረ የመረጃው አቀባዮች ዝርዝር ባይናገሩም፣ የማዕከላዊ እስር ቤቱ አባል የሆነ እንዳመለከተው ወጣቱ የተሰወረው እርምጃ ተወስዶበት ወይም እክል ገጥሞት ሳይሆን አምልጦ ነው።
ቀደም ሲል የሥራ ባለደረቦቹ የነበሩ በጥበቃ ሥራ ላይ ማዕከላዊ አግኝቷቸው ሲያጫውቱት እንደነበር የጎልጉል ዘጋቢ አረጋግጧል። ይህ ወጣት በእነሱ እርዳታ ያምልጥ ወይም በራሱ ስልት ይሰወር ግን ለማወቅ አልተቻለም። ከወጣቱ መጥፋት ጋር በተያያዘ የታሰሩ የጥበቃ ሰራተኞች እንዳሉ ግን ለማወቅ ተችሏል። ወጣቱ ለጊዜው በትክክል ስሙ ወደማይጠቀስ ሌላ አገር ሸሽቷል።
በተመሳሳይ ከየሰፈሩ “ጉልቤ” የሚባሉ ሥራ ፈላጊዎችና የራሳቸውን የገቢ ምንጭ ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ለስለላ ስራ መመልመላቸውን የጎልጉልዘጋቢ አረጋግጧል። አንዳንዶቹም “ቢዚ ነው” እያሉ እንደሚቀለዱ ከጓደኞቻቸው እንደሰማ ዘግቧል። ከቄራ የተመለመለ “ጉልቤ” ጫት ቤት ለሚቀርቡት እንዴት እንደተመለመለና እነማን አብረውት እንደሚሰሩ መንገሩን ስፍራው ድረስ በመሄድ አረጋግጧል።
ከአንዳንድ ተመልማዮች እንደተሰማው ከሆነ ኢህአዴግ በቀበሌ መዋቅሩ እንደቀድሞው መረጃ አይጎርፍለትም። የቀበሌ አደረጃጀቶች በከፍተኛ ደረጃ ለደህንነቱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር አይዘነጋም። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ የቀበሌ መዋቀሩና ጥርነፋው ተሰብሮበታል ወይም በመረጃ ፍሰት ድርቅ ገብቶበታል።
ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ዙሪያ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ሆነው ማታ ማታ የሚሰሩት የህወሃት የደህንነት ሰዎች እንደሆኑ፣ ቀን ቀን ግን በመልክ ስለሚለዩ ለመስራት እንደማይችሉ መዘገባችን ይታወሳል። በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞችና ሰፈሮች በማታ ለመንቀሳቀስ እንደሚፈሩ ታውቋል። ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋና አካባቢው፣ ወደ ቃሊቲና አቃቂ እንዲሁም ሱሉልታ የሚሄዱ ሰዎች ሳይመሽ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ሲራወጡ ይታያሉ። ለዚህም ምክንያቱ ፍርሃቻ ነው። ዘጋቢያችን እንዳለው አዲስ አበባ ሰላም ብትመስልም ፍርሃት ውጧታል። የንግድ እንቀስቃሴዎች ተዳክመዋል። ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ እቃዎች እጥረት በስፋት ይታያል። የዶላር ፈላጊና አቅራቢዎችም የአገዛዙ ሰዎች ናቸው። (ፎቶ: ለማሳያ የቀረበ)