| Jan-Mar 09 | Apr-Jun 09 | Jul-Sept 09 | Oct-Dec 09 | Jan-May 10 | Jun-Dec 10 | Jan-May 11 | Jun-Dec 11 | Jan-May 12 |

[dehai-news] Goolgule.com: ኢህአዴግ በፖለቲካ ወለምታ ውስጥ!!

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 14 Nov 2012 15:30:20 +0100


ኢህአዴግ በፖለቲካ ወለምታ ውስጥ!!


አባተ ኪሾን መልሶ ለመሾም ውስወሳ ተጀምሯል

 

November 14, 2012 08:59 am By <http://www.goolgule.com/author/tibebem/> Editor <http://www.goolgule.com/eprdf-in-disarray/#comments> Leave a Comment

(http://www.goolgule.com/)

ኢህአዴግ በ“ፖለቲካ ወለምታ” ውስጥ እንደሚገኝ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኢህአዴግ ዲፕሎማት ለጎልጉል ተናገሩ። በከፊል ኢህአዴግን የተለዩ የሚስሉት ዲፕሎማት በጎልጉል የቅርብ ሰው አማካይነት ድምጻቸው ሳይቀረጽ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት የተፈጠረው የፖለቲካ ወለምታ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተዋል። የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመካከለኛ አመራሩ ውስጥ የመጠራጠር ስሜት መፈጠሩን በፓርቲ ግምገማ ላይ በግልጽ መናገራቸው የዲፕሎማቱን አስተያየት የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የአቶ መለስን ሞት ደብቀው በመያዝና ማስተባበያ በመስጠት ጊዜ የወሰዱት ይኸው የተባለው የፖለቲካ ወለምታ እንዳይፈጠር ለማድረግ በማሰብ እንደነበር ዲፕሎማቱ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ አቶ መለስ ሁሉንም ጉዳይና ሃላፊነት ብቻቸውን ይዘውት ስለነበር በድንገት ማለፋቸው ፓርቲው ውስጥ አሁን በየደረጃው የሚታየው የመተርተር አደጋ መከላከል ግን አልተቻለም።

የፖለቲካ ወለምታ ስለመከሰቱ ማንም ማስተባበያ ሊያቀርብ አይችልም የሚሉት ዲፕሎማት በእርሳቸው እይታና ባላቸው መረጃ መሰረት ድርጅትን መክዳት፣ ድርሻዬ በሚል ገንዘብ ማሰባሰብ፣ ቤተሰብን በተለያዩ ምክንያቶች ማሸሽ፣ በቁልፍ የመከላከያ ሃላፊዎች ላይ ማነጣጠር፣ በግምገማ ስም ካድሬውን ማመስ፣ በስልጠና ስም የበታች አመራሮችን መደለል፣ ከሁሉም በላይ ማንኛውም ውሳኔ ሲወሰን በተናጠል እንዳይሆን የሚከለክል አሰራር መከተል የመሳሰሉት ተፈጠረ ለተባለው “ወለምታ” ዋና መግለጫዎች ናቸው።

ፓርቲያቸው ኢህአዴግ የመለሰን ምስል እየለጠፈ “የታላቁን መሪ ውርስ ሳይበረዝ እናስቀጥላለን” የሚለው ውሸት እንደሆነ በመግለጽ ተጨማሪ ማሳያ የሚያክሉት ዲፕሎማቱ፣ “ይህ ሁሉ ግርግር ካድሬውን ንዶታል፣ የምንቀራረብ ዲፕሎማቶችና ባለስልጣናት የምንቀያረውን መልዕክት ህዝብ ቢሰማ በመሪዎቹ ያፍራል። ካድሬውም ራሱን ይጠላ ነበር” በማለት ተናግረዋል።

“ዲፕሎማቶች እርስ በርሳችን ሃሜት ከጀመርን ቆይተናል” በማለት ሃሜት አንዱ የፖለቲካ ወለምታ ማሳያ እንደሆነ የሚናገሩት የኢህአዴግ ሰው፣ መለስን ታላቅ መሪ እያሉ የጋራ አመራር መሰየማቸው በካድሬውና በፓርቲው የተለያዩ አመራሮች ዘንድ ማፌዣ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ሲያብራሩም “የመለስ መስመር ሳይበረዝ እናስቀጥላለን እያሉ እየማሉ አገሪቱ በጋራ አመራር እንደምትመራ ይፋ ማድረጋቸው አቶ መለስ በጋራ አመራር የማያምኑ፣ አምባገነን፣ የስልጣን ጥመኛ፣ የዲሞክራሲ ባህል የሌላቸው፣ ከዚህ ቀደም የተቃወሙዋቸው የሚሉት ሁሉ ትክክል እንደሆነ መቀበልና አስተዳደራዊ መልካቸው የተበላሸ እንደነበር የማወጅ ያህል ነው” ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ መለስን በአደባባይ እያወገዘ እንዳለ ሁሉም እንደሚረዳ ማረጋገጫው በእህት ፓርቲዎች ውስጥ በተካሄደው ግምገማ ከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጣዊ ችግር እንዳለባቸው ማስታወቃቸው እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት በቅርቡ “በታሪክ አጋጣሚ ተሾምኩ” በማለት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመደቡትን አቶ ደመቀ መኮንን የተናገሩትን ያጣቅሳሉ።http://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2012/11/demeke-e1352872637505.jpg

የብአዴን ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ ባህር ዳር በተካሄደው የድርጅት ጉባዔ ላይ የአቶ መለስ ህልፈትን ተከትሎ ተፈጠረ የሚባለውን የፕሮፖጋንዳ መነቃቃት “የዘመቻ ውጤት” ብለውታል። አያይዘውም “የልማት ሰራዊት መገንባትና ማደራጅት አልተቻለም” በማለት የሚሰራውንና ተሰራ የተባለውን ስራ “ሸንኮራ ቆረጣ” እንዳስመሰሉት አስተያየት ሰጪው ይናገራሉ።በማያያዝም የክልሉ ምክትል ሊቀመንበር “የመጠራጠር መንፈስ አለ” በማለት ስጋታቸውን መግለጻቸውን ያክልሉ። አቶ በረከትም ተመሳሳይ አስተያየት መስጠታቸውን ጨምረው ገለጸዋል።አንዳንድ የስራ ባልደረቦቻቸው እንደገለጹላቸው ከሆነ በቅርቡ ብወዛ፣ ሹም ሽርና በመተካካት ስም ማስወገድ እንደሚደረግ በማውሳት አስተያየታቸውን የሰጡት የኢህአዴግ ሰው፣ በደቡብ ክልል ኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው አይነት ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ቅድመ ጥናት መደረጉን ይፋ አድርገዋል። ለዚህም ይመስላል በሙስና ተወንጅለው ለዓመታት ከታሰሩ በኋላ በነጻ የተለቀቁት አባተ ኪሾን መልሶ ለመሾም የማግባባት ስራ (ሎቢ) ተጀምሯል ብለዋል።

“ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ?” ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ “በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ በዳያስፖራ ዘንድ ለኢህአዴግ ሰዎች የሚሆን ቦታ ስለመኖሩ ሰምተው” እንደማያውቁ በመጠቆም ለመመለስም ሆነ ለመቅረት ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ “ከተቃዋሚዎች በኩል ሁሉንም የኢህአዴግ ሰዎች በአንድነት በመፈረጅ “ወዮልህ” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች መብዛታቸው ለስርዓቱ ኃይል እንደሆነው” አመለክተው “ወለምታው እኔንም ይመለከተኛል። እኔም እንደ ባልደረቦቼ ወጌሻ ያስፈልገኛል” የሚል መልስ ሰጥተዋል። አያይዘውም የተፈጠረውን ወለምታ ለመጠቀም ምላጭ ፖለቲከኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ምላጭ ፖለቲከኞች ምን መምሰል እንዳለባቸው ግን አላብራሩም። አቶ መለስን አስመልክቶ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በቀጣይ እናቀርባለን።

ጎልጉል ባለው መረጃ በደቡብ ክልል አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሲዳማ ብሄረሰብ ክፍሎች አሁን በቡና ንግድ የተሰማሩትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ አባተ ኪሾን ይቀበላል። በክልሉ ከሲዳማ ብሄረሰብ ውጪ ፕሬዚዳንት ለማድረግ እንደማይሞከር በተለያዩ ጊዜያት ስለክልሉ ሲዘገብ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባለፈው አርብ በመስከረም ወር ማድረግ የሚገባውን የመጀመሪያ ሩብ አመት ግምገማ በማካሄድ ያሳለፈው ውሳኔ በድርጅቱ ውስጥ አለ የተባለውን የፖለቲካ ወለምታ የሚያሳይ እንደሆነ ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ አስታውቀዋል። የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ በክልል ደረጃ አሉ የተባሉትን ችግሮች አድበስብሶ በጥንካሬ ከገመገመ በኋላ “የክረምቱ ስራ ስላለቀ፣ የበጋው ስራ ባስቸኳይ እንዲጀመር” ሲል የፖለቲካ ውሳኔ ማውረዱን ይፋ አድርጓል። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ክረምቱ ካለቀ ከሶስት ወር በኋላ “የበጋው ስራ ይጀመር፣ ክረምቱ አልቋል” የሚል ውሳኔ ማሳለፉ ከወለምታም በላይ ነው።

 






image001.jpg
(image/jpeg attachment: image001.jpg)

Received on Wed Nov 14 2012 - 10:27:53 EST
Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2012
All rights reserved