Basic

Goolgule.com: ኢትዮጵያ፤ ህወሓትና የትግራይ ወጣት

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Tuesday, 23 May 2017

ኢትዮጵያ፤ ህወሓትና የትግራይ ወጣት

 

ኢትዮጵያ ወጣትነትን15-29 ዓመት ባለ የዕድሜ ክልል ከፍላ ትበይነዋለች፡፡ አገሪቱ ውስጥ ካለው የህዝብ ብዛት በአማካይ 60% የሚሆው ወጣት ተብሎ ሊጠቀስ በሚችለው የዕድሜ ክልል ይገኛል፡፡ የተሻለ የትምህርት ጥራት፣ አማራጭ የሥራ ዕድል፣ ምቹ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የፖለቲካ ነፃነትና መሰል ወሳኝ ጉዳዮችን አጥብቀው የሚሹት የኢትዮጵያ ወጣቶች ከህወሓት/ኢህአዴግ አፓርታይዳዊ ዘረኛ የፖለቲካ አሰላለፍ ጋር በተደጋጋሚ ሲላተሙ ይስተዋላል፡፡

ለህወሓት/ኢህአዴግ አንድ አይነት ወይንም ተመሳሳይ አጀንዳ የሚያነሳ፣ በዘውጋዊ (በዘረኛ) ማንነት የማይከፋፈል፣ ለአገዛዙ የማያጎበድድ ወጣት “የሥርዓቱ አደጋ” ነው፡፡ በ1997 ታሪካዊ የምርጫ ዘመን የአገዛዙን ዘረኛ የአፓርታይድ አሰላለፍ የማይቀበሉ፣ ከአካባቢያዊ ማንነት ይልቅ የጋራ ማንነትን ያቀነቀኑ ወጣቶችን ከመንግስታዊ ፍጅቱ ጎን ለጎን “አደገኛ ቦዘኔ” ብሎ መፈረጁ የሚታወስ ነው፡፡

በርግጥ አገዛዙ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አዲሱን ትውልድ ቦዘኔ ለማድረግ ያልሰራው እኩይ ሥራ አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው እኩይ ተግባሩና የወጣቱ ማምከኛ መንገድ የትምህርት፣ ታሪክ፣ ባህል … ወዘተ አዲሱ ትውልድን የበቃ አድርገው የሚቀርፁ ተቋማትን ማፈራረስ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይም ትውልድ ገዳይ የሚባለው የትምህርት ፖሊሲ አብዛኛውን ወጣት ቦዘኔ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ “በትምህርት ፖሊሲው” ላይ ጥናት የሰሩ ገለልተኛ ምሁራን የጋራ ድምጽ ነው፡፡ የተሻለ የትምህርት ፖሊሲና አዳዲስ ብቃት ያላቸው መምህራን እንደሚያስፈልጉ እየታወቀ ከህወሓት/ኢህአዴግ መስመር የሚወጡ የከፍተኛ ትምህርት ምሁራን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዩኒቨርሲቲዎች ተባርረዋል፡፡ በዱሪ መሐመድ ሁለት መስመር ደብዳቤ ለዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ያገለገሉ 42 ምሁራን በመለስ ትዕዛዝ መባረራቸውን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ የከፍተኛ ትምህርት አቅጣጫዎች፤ የአገሩን ታሪክ በደንብ የተረዳ፣ አገራዊ ራዕይ ያለው ወጣት ከመፍጠር ይልቅ በይድረስ ይድረስ የተማረና ለአገሩ ከሚያበረክተው ይልቅ በየትም ብሎ አገሩ እንድታበረክትለት የሚፈልግ  ካድሬ “ምሩቅ” ማፍራትን ዋነኛ ዓላማው  አድርጎ ወስዶታል፡፡ ዛሬ ላይ በማዕከላዊ አሰቃቂ እስር ቤት ውስጥ የብቻ እስረኛ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በተደጋጋሚ ይሉት እንደነበረው የአሁኑ ወጣት ከዩኒቨርሲቲው “A” ውጤት ይልቅ በየአባል ድርጅቶች “C” አግኝቶ መቀጠርን የሚፈልግ እንዲሆን አገዛዙ በ“ትጋት” እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ በገዳይ የትምህርት ሥርዓት የተፈለፈለ ወጣት ከተማረው የሥራ ዘርፍ ይልቅ የማያውቀው ድንጋይ ፈለጣ እንደሥራ ሲቀርብለት ቆይቷል፡፡ በአንፃሩ ድንጋይ ፈለጣም ሆነ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ዕውቀትን የማይጠይቁ ሥራዎችን ለመስራት ወጣቱ የግዴታ የአገዛዙ አባል መሆን ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ከሚከተለው ዘረኛ የአፓርታይድ የፖለቲካ አሰላለፍ የተነሳ የኢትዮጵያ ወጣቶች ድምፅ በጊዜ ሂደት ቅርፅ እያጣና እየተከፋፈለ መጥቷል፡፡ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ወጣቶችን ዘንግቶ የኖረው አገዛዝ በቅድመ እና ድህረ ምርጫው የወጣቱን የማይተካ ሚና በጉልህ ተረድቶታል፡፡ ድህረ-ምርጫ 97 ተከትሎ ወጣቶችን በሥራ ዕድል በማማለል የአገዛዙ አባል እንዲሆኑ ማስገደድ ካልሆነ ደግሞ የተሻለ ሥራ ዕድል የማይታሰብ መሆኑን በተግባር እያስረገጠ መሄዱን ቀጥሏል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የተከፋፈለ፣ በዘውጋዊ ቅርፅ የሚፈስ፣ አገራዊ አጀንዳ የማያነሳ፣ ጥራዝ ነጠቅና ደንታ ቢስ ትውልድ በመፍጠሩ ረገድ ዛሬም በትጋት ላይ ሲሆን የድካሙን ያህል ባይሳካለትም ፍሬው ግን በአደባባይ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየው የዘር ክፍፍል የወጣቱን ድምፅ ቅርፅ እንዲያጣ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ከአገዛዙ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ወጣቶች ከሃሳብ አንድነት ይልቅ አካባቢያዊ ማንነት ላይ የተንተራሰ ህብረት መፍጠር ይቀላቸዋል፡፡ ሳይንሳዊ ጥናት በላቀ ደረጃ ይተገበርባቸዋል የሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአካባቢያዊ ማንነት መተብተባቸው የአገሪቱን መፃኢ ዕድል አጨልሞታል፡፡

በህወሓት የፖለቲካ መሃንዲሶች በሚዘወረው የአገሪቱ ፖለቲካ፤ ወጣቶች እንደየአካባቢያዊ ማንነታቸው የበረከት እና የመከራ ተካፋዮች ሆነዋል፡፡ የዜግነት ደረጃ በየፈርጁ በሚታይባት ኢትዮጵያ፤ ወጣትነት ከክልል ክልል፣ ከዘር ዘር የተለያየ ነው፡፡

ህወሓትና የትግራይ ወጣት

መሀሉን እንደተቆጣጠረ ዳሩን (ትግራይን) እንደአገር የመገንባት ፖለቲካዊ ስትራቴጂ የያዘው ህወሓት፤ ትግራይ እንደ “ክልል” ከ“ፌዴራሉ መንግስት” ከምታገኘው ዓመታዊ የበጀት ድጋፍ በግዙፉ የኢኮኖሚ ኢምፓየር – ኤፈርት በኩል በማህበራዊና በኢኮኖሚው መስክ እንደአገር እየተደራጀች ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ህወሓት ተተኪ ወጣቶችን በከረረ ዘውጋዊ ማንነት በማነፁ ረገድ “የተሳካ” ተግባር ፈጽሟል፡፡

የትግራይ ብሄርተኝነት ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በተጠና መንገድ በህወሓት ካድሬዎች በኩል ለተተኪው የትግራይ ወጣት ብሄርተኝነቱን እንዲወርስ በመደረግ ላይ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ባሉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች “የዜግነት ክብር” የሚለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አይዘመርም፡፡ በአንፃሩ የክልሉ መዝሙር ተብሎ በየትምህርት ቤቶች በሰንደቅ ዓላማ ሥነ-ሥርዓት የሚዘመረው መዝሙር የህወሓት የበረሃ ዘመን መዝሙር መሆኑ የትግራይ ወጣቶች ህወሓትን እንደዘላለማዊ አዳኝ፣ ህይወትም፣ መንገድም የሆነ መሲህ ድርጅት መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡

የጭቆናና የትግል ታሪኮችን በሥርዓተ ትምህርት ደረጃ እንዲማሩ የተደረጉት (በመማር ላይ ያሉ) የትግራይ ወጣቶች በአገዛዙ ላይ የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰሙበት አንዳች አመክንዮ የላቸውም፡፡ ለብዙዎቹ የትግራይ ወጣቶች “ደርግ” እና “አማራ” የአንድ ሳንቲም መንታ ገጽታዎች ናቸው፡፡ “ብሄር ብሄረሰቦች” በህወሓት “መስዋዕትነት” የቆሙ መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ህወሓት ከሌለም ኢትዮጵያ እንደአገር መፅናት የማይቻላት የህወሓታዊያን የእጅ ሥራ ውጤት ትመስላቸዋለች፡፡

አገሪቱ ውስጥ ካለው የትምህርት ሥርዓት እጅግ በተሻለ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ግብዓቶች (የተማረ የሰው ኃይልና የትምህርት ቁሳቁስ ግብአቶች) ተሟልቶላቸው በመማር ላይ ያሉት የትግራይ ወጣቶች በተደላደለ የኢኮኖሚ ደረጃ እና በላቀ ማህበራዊ ቁመና ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ለአብነት ለአንድ የኦሮሞ ታዳጊ ወጣት ስደት የህይወት ግቡ ሲሆን፤ ለትግራይ ወጣት የህይወት ግብ ደግሞ ግብር-አልባ የከፍተኛ ኢንቨስትመንት ንግድ ባለቤት መሆን ነው፡፡

የአገሪቱን የኢኮኖሚ አውታሮች እየዋጠ ራሱን እያገዘፈ ያለው ኤፈርት፣ ዓለምአቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚበጅቱትን በጀት እንደየ ፕሮጀክቶች አይነት በየዘርፉ አብላጫውን በጀት ጠቅልለው የሚወስዱት “ትልማ” (የትግራይ ልማት ማኅበር) እና “ማረት” (ማኅበረ ረድኤት ትግራይ)፣ … የትግራይ ወጣቶችን ማህበራዊ ቁመና በማሳደግ እና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማፈርጠሙ ረገድ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡

ህወሓት ከልካይ አልባ በሆነ መልኩ ማዕከላዊ “መንግሥቱን” የተቆጣጠረ መሆኑ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነዉ፡፡ በዚህ ተግባሩ በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም ክልሎች ትልልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በመጠቅለል ለትግራይ ተወላጆች ማመቻመች የተለመደ አሰራሩ ሆኗል፡፡ ከኦሮሚያ የጫት ንግድ፣ ከጋምቤላ ሰፊ ለም መሬት ቅርምት፣ ከአፋር ልቅ የጨው ንግድ፣ ከደቡብ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛ፣ በሱማሌ ክልል ካለው የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ከአዲስ አበባ የመሬት ወረራና ግብር አልባ ንግድ፣ … በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የትግራይ ወጣቶች ተጠቃሚ ናቸው፡፡

በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫ ትግራዋያን ያልገቡበት የኢትዮጵያ ክፍል የለም፡፡ ከቋራ እስከ ኦጋዴን፣ ከአሳይታ እስከ ወልቃይት፣ ከጋምቤላ እስከ ባሌ፣ ከበርታ እስከ ሱርማ፣ … የቀራቸው አንድም ቦታ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው መጠን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት ነፃነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ ባይሆንም ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተከለከለ መብት ለእነርሱ ብቻ ለይቶ በመሰጠቱ ድርጊቱ ሊኮነን ይገባል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ አፓርታማዎች፣ ወርቅ ቤቶች፣ … የትግራይ ባለሃብቶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ሃብቶች “ወራሽ” የሆኑት ትግራዋይ ወጣቶች ኢትዮጵያን የሚመለከቱበት መንገድ ከቀደሙት እና አሁን ካሉት (አባቶቻቸው) በተለየ እንድንፈራቸው እና መፍትሄ እንድንፈልግላቸው ግድ ይለናል፡፡

ለብዙዎቹ የትግራይ ወጣቶች የህወሓት ከልካይ አልባ ሥልጣን የደም ካሳ ውጤት ነው፡፡ ይህ የደም ካሳ ከ … እስከ የሌለው ዘላለማዊ የሥልጣን ጊዜ ነው፡፡ መገለጫውም ከዘፈቀደ ግድያ እና እስር ባሻገር ለም መሬት መርጦ መቀራመት፣ ግብር አልባ ንግድ ማከናወን፣ ቀረጥ አልባ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ህጋዊ ጨረታ አልባ “ማሸነፍ”፣ … ሁሉንም ህገ-ወጥ ድርጊት የደም ዋጋ ውጤት አድርገው ይወስዱታል፡፡ በቀደመው ሳምንት ባህር ዳር ከነማ ከመቀሌ ከነማ ጋር በመቀሌ አዲ ሓቂ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ የትግራይ ወጣቶች ያሰሟቸው የነበሩ ፀያፍ ማንነት ተኮር ስድቦች በተለይም “አማራ አህያ፣ መቶ አመት እንገዛሃለን ገና” የሚለው ዕብሪታዊ “መፈክር” ለትግራይ ወጣቶች ገደብ የለሽ ትዕቢት ገላጭ ማስረጃ ነው፡፡ የህወሓት ጠባብ የዘረኝነት ምልከታ ውጤት የሆነው የበረሃ ማኒፌስቶው ለዚህኛው ዘመን የትግራይ ወጣት ተጋብቶበታል፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ ከትግራይ ወጣቶች ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ሞት፣ እስር፣ እንግልት፣ ስቅይት፣ ስደት፣ … ዕጣ ክፍላቸው ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ትግራዋይ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ቀርቶ ከአፍሪካ ወጣቶች በተሻለ ህይወት ሲኖሩ ይታያል፡፡ ለአንዲት የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣት ዱባይ መሄድ የእርሷን እና የቤተሰቧን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ለአንዲት የትግራይ ወጣት ግን የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ የጉዞ አጋጣሚ ነው፡፡ አንድ ጎጃሜ ወጣት ገበሬ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ተስፋው ሎተሪ አዟሪነት አልያም የባለፀጋ ቤት ጠባቂነት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንፃሩ አንድ የትግራይ ወጣት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ግብር አልባ ንግድ አልያም ጥራት ያለው ትምህርት መማር የህይወት ምዕራፉ አካል ይሆናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የወጣ አንድ የኦሮሞ ወጣት የኦህዴድ አባል ሆኖ ከቀናው የኮብል ስቶን ድንጋይ ፈለጣ ላይ ሲሰማራ አብሮት የተመረቀ የትግራይ ወጣት የመንገድ ሥራ ተቋራጭ አልያም ፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን  ለንጽጽር በማይበቃ ልዩነት የኢትዮጵያ ወጣት ህይወት ትቀጥላለች …

በዛሬዋ ኢትዮጵያ፣ ለብዙዎቹ የትግራይ ወጣቶች የትግራይ ተወላጅነት የደም ካሳን እያሰቡ ሳይሰሩ ለመበልፀግ የሚያስችል ሁነኛ “ማህበራዊ ዕድል” ነው፡፡ የህወሓት የአደባባይ ግድያ እና የጅምላ እስር የትግራይን የአገር ግንባታ ሂደት እስካላደናቀፈ ድረስ ትግራዋይ ወጣቶችን የሚያሳስብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያዊያን ረሃብና ስደት ለትግራይ ወጣቶች ግድ የማይል ሁነት ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሱ ህዝባዊ አመፆች የነፃነት ረሃብ የወለዳቸው ህዝባዊ እምቢተኝነቶች ሳይሆኑ የ“ጥጋብ” ውጤቶች መስሎ ይታያቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ እውነት ለመሆኑ፤ የትግራይን ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በንግድ ድርጅቶቻቸው፣ በየመሸታ ቤቱ፣ … ወዘተ የሚያራምዱት አቋማቸው እንዳለ ሆኖ የሚሊዮኖች መገናኛ በሆኑት የማህበራዊ ሚዲያ ውጤቶች የያዙትን የጋራ ዘመቻ ማየቱ የትግራይ ወጣቶችን ዕብሪታዊ ምልከታ ይበልጥ ለመረዳት ያስችላል፡፡

እጃቸው በትውልድ ደም የተጨማለቁ የህወሓት መሪዎች ለትግራይ ወጣቶች ወደር የሌላቸው “አርዓያ” ናቸውና አንዳች የርህራሄና የሞራል መሰረት የሌላቸው ሂትለራዊ ርዝራዦች ሆነዋል፡፡ የትግራይ ወጣቶችን ህወሓታዊ አመለካከት ዘላቂነት ያለው የዕለት ተዕለት ኑሮ አካል ለማድረግ ህወሓት በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሄው የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 19/2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የትግራይ ወጣቶች ማህበር ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን (ለብቻቸው) “ግንቦት 20” እንደሚያከብሩ ከህወሓት ጽ/ቤት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች የህወሓትንና የትግራይ ወጣቶችን ስር የሰደደ ቁርኝትና የጥቅም ትስስር ለማስተዋል ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለትግራይ ወጣቶች ህወሓትን የህልውናቸው መሰረት አድርገው ይወስዱታል፡፡ “ህወሓት ከሌለ ትግራይ የለችም” የሚለው ምልከታ ወደ “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” ካደገ ውሎ አድሯል፡፡ ህወሓት የትግራይ ወጣቶችን ፖለቲካዊ አቅም፣ ኢኮኖሚያዊ መደላድል፣ ማህበራዊ ቁመና ለማሳደግ በትጋት ሰርቷል፡፡ ዛሬም ድረስ “የጨቋኝ Vs ተጨቋኝ” የፈጠራ ታሪኮችን ለወጣቶቹ በመጋት “ወዳጅ” እና “ጠላት” በሚል በዘውጎች መካከል አገር አፍራሽ የሆነ የልዩነት መስመር በማስመር ላይ ይገኛል፡፡ የትግራይ ወጣቶችም የህወሓትን አዳኝነት፣ ህይወትም መንገድም እርሱ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል፡፡

በሌላኛው ጫፍ በ“አረና ፓርቲ” በኩል የሚሰሙ “የተቃውሞ ድምፆች” ጊዜ ያለፈባቸው ማወናበጃ “የፖለቲካ ቁማር” አካል ሲሆኑ እየታዩ ነው፡፡ ለብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከታታዮች “ክስተት” ሆኖ ሲታይ የነበረው አብርሃ ደስታ በጊዜ ሂደት ትክክለኛ ማንነቱን ሲገልጥ ታይቷል፡፡ አረና የሚታገለው ህወሓትን ከሥልጣን ለማንሳት እንደሆነ ቢያትትም ዋንኛና ቀዳሚ አጀንዳው ግን ህወሓትን በሌላ የዘር ድርጅት ተክቶ የትግራይን የበላይነት ማስጠበቅ እንደሆነ ፓርቲው እና አባላቱ ከሚያሰሟቸው ንግግሮች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ይመስላል እጃቸው በደም የጨቀዩ የህወሓት ባለሥልጣናት በዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሞገስ እንዲያገኙ ከህወሓት ካድሬዎች ጋር በእኩል ሲተባበሩ የሚታዩት፡፡ የህወሓት መዛል ከትግራይ ጥቅም አኳያ የሚያሳስባቸውን ያህል የብአዴን አልያም የኦህዴድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ  መፈርጠም እንቅልፍ ይነሳቸዋል፡፡ በጥቅሉ ከትግራይ አኩራፊ እንጂ እውነተኛ ተቃዋሚ ሲወጣ አልታየም፡፡ ስለትግራይ ወጣቶች ስናስብም ሁኔታዎችን በዚህ መልከ መፈተሽ ተገቢ ወደሚል ድምዳሜ እንድንሄድ ይገፋፋናል፡፡

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በተለይም ድህረ-ምርጫ 97 ተከትሎ የትግራይ ወጣቶች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ያላቸው ምልከታ እጅግ የተዛባ ሆኗል፡፡ ህወሓታዊ በሆነው የክልሉ የትምህርት ሥርዓት በድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍፁም ተጠልፈው ወድቀዋል፡፡ በርግጥ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት በተሻለ የማህበረ-ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከረሃብ ይልቅ ለጥጋብ ቅርብ ናቸው፡፡ ስደትን በቦሌ እንጂ በባሌ በኩል አያውቁትም፡፡ የገዳይ እንጂ የሟች ቤተሰብ አባል አይደሉም፡፡ ግብር ከመክፈል ይልቅ ከተከፈለ ግብር ላይ “ድርሻ” መውሰድን በተዋረድ ያውቁበታል፡፡ ከአሰቃቂ እስር ቤቶች ጋር ሳይሆን ከራቁት ዳንስ ቤቶች ጋር የተያያዘ ህይወት የሚኖሩት የትግራይ ወጣቶች በህወሓት ፊትአውራሪነት፣ በብዙሃኑ እጦት የብቻ ድሎት ህይወት መኖርን መርጠዋል፡፡

ገደብ የለሽ የሥልጣን ፍቅር የጭካኔ ሃዲድ ነው፡፡ በግድያና አፈና የሥልጣን ምሶሶውን  “ያቆመው” ህወሓት የውድቀት ጉዞውን ተያይዞታል፡፡ አወዳደቁም ብቻውን ሳይሆን የትግራይ ወጣቶችንም የሚጨምር ለመሆኑ የወጣቶቹ ውርስ ደመቀዝቃዛ ባህሪ የሚነግረን እውነት አለ!


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events