Basic

Goolgule.com: የህወሓት ፕሮግራም፤ የመለስ ሌጋሲ – ዜጎችን ማፈናቀል፤ ማጋደል!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Monday, 18 September 2017

የህወሓት ፕሮግራም፤ የመለስ ሌጋሲ – ዜጎችን ማፈናቀል፤ ማጋደል!

 

ገና ከመነሻው በበረሃ ያወጣው ፕሮግራሙ በግልጽ እንደሚያመለክተው የህወሓት ዋንኛ ዓላማ ኢትዮጵያን አዳክሞና በጎሣ ከፋፍሎ ትግራይን ታላቅ በማድረግ ሪፑብሊክ መመሥረት ነው። ባለፉት 26 ዓመታት ይህንን ለማሳካት በኢትዮጵያ ውስጥ ያልፈነቀለው የጎሳ ድንጋይ የለም፤ ያላጋጨው ሕዝብ፤ ያላጋደለው ወገን የለም፤ ትግራይን ሳይጨምር!

ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ሳያስበው አስፈነጠረው እንጂ የመለስና ዋናዎቹ የህወሓት መሥራቾች  ዕቅድ ይህንኑ ለማሳካት እንደሆነ ሰሞኑን በተከታታይ በምናትመው የአቶ ገብረመድኅን ጽሁፍ በግልጽ የተቀመጠ ሐቅ ነው

የወቅቱ የፍጅት ዓላማ ደግሞ ኦሮሞን ከሶማሊ ወገኖቹ ጋር በማጋጨት የአገዛዝ ዘመኑን ማራዘም፤ ሁለቱን ጎሣዎች በማይረሳ ቂምና ጥላቻ ውስጥ ማስገባት፤ ይህንንም እስካሁን በሌሎቹ ጎሣዎች መካከል ከፈጠረው ጥላቻና ቁርሾ ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን ኅልውና አጥፍቶ የትግራይን የበላይነት ማስፈን ነው። ለዚህ ደግሞ የሚደግፉት ከሁሉም ጎሣዎች የተውጣጡ ጥቅም ያሰከራቸው ወሮበላ ጎረምሶች መኖራቸው የሚካድ አይደለም።

አሁንም ከተቀናጀ ኅብረት፤ አሁንም ትኩረት ሁሉ ህወሓትንና ማንነቱን ተረድቶ ከመዋጋት ያነሰ አስተሳሰብ እስከተያዘ ድረስ ውጤቱ ንጹሐንን ማስፈጀት ብቻ ነው የሚሆነው። የሐረርጌ ሙስሊም ኦሮሞና ሙስሊም የኢትዮጵያ ሶማሊ ሊፋጁበት የሚችሉበት ምንም ምክንያት የላቸውም። (ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ)

የሰሞኑን የህወሓት ግፍ በተመከለከተ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የዘገበውን ከዚህ በታች አስፍረናል።

በኦሮምያና በሶማሌ ክልሎች ወሰኖች ባሉ ወረዳዎች ውስጥ እየተካሄደ ካለው የጥቃት እርምጃዎችና ግጭቶች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ከተፈጠረው የፀጥታ ቀውስ ጋር ተያይዞ ከሰማሌ ክልል የተፈናቀሉ ከአርባ ሺህ እስከ ሃምሣ ሺህ የሚሆኑ የኦሮሞ ተፈናቃዮች ምሥራቅ ሃረርጌ መግባታቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጭናቅሰን ውስጥ ዛሬ (አርብ) በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰው ሕይወት መጥፋቱ ተሰምቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚሁ የሁለቱ አጎራባች ክልሎች ቀውስ ጋር ተያይዞ ጎረቤት ሶማሌላንድ ውስጥ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ህይወት ያጠፋ ጥቃት እየተፈፀመባቸው መሆኑና ከፍተኛ ሥጋት ላይ እንደሚገኙ እየገለፁ ናቸው።

ሃርጌሣ ላይ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተገድለው አንደኛው ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የሶማሊላንድ የፀጥታ ሚኒስትር ዴኤታ አስታውቀዋል።

ሶማሊያዊያኑ በኢትዮጵያዊያን ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ ጥሪ ያስተላለፉት ሚኒስትር ዴኤታው ሞሐመድ ሙሣ ዴሬ ለኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ጥበቃ እንዲያደርጉ ኃይሎቻቸውን ማዘዛቸውን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ከተፈፀመው ጥቃቶችና እየታዩ ካሉ ግጭቶች ጋር በተያያዙ ሁከት አዘል ጥቃቶች አወዳይ ከተማ ውስጥ ቁጥሩ የበዛ ሰው ሕይወት መጥፋቱ ተገልጿል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎም የሰፋ መፈናቀል ከጅጅጋ እና ሌሎችም የሶማሌ ክልል ከተሞች መከተሉ ተነግሯል።

ማክሰኞ ዕለት መስከረም 2/2010 ዓ.ም. አወዳይ ከተማ ውስጥ ሁከት የቀላቀለ ሰልፍ ያደረጉ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት ሃምሣ ሰው መገደሉን የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ኢስማኤል ለቪኦኤ የገለፁ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል አቻቸው አቶ አዲሱ አረጋ ግን አድራጎቱ መፈፀሙን አረጋግጠው የተገደለው ሰው ቁጥር ግን 18 መሆኑን ከመካከላቸውም 12ቱ የሶማሌ ተወላጆች ስድስቱ የኦሮሞ ጃርሶ ጎሣ አባላት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በተፈፀመው ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንደሚያዝን ቃል አቀባዩ ጠቁመው ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ በጥቃቱ ላይ ተሣትፈዋል የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ መሆንን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ የአወዳይ ጥቃት ተከትሎ ከሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂጂጋ ከ21 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሎ ጭናቅሰን፣ ባቢሌና ሐረር ከተሞች ውስጥ የተጠለሉ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮችና የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ አመልክተዋል፡፡

ስለዚህ የመፈናቀል ጉዳይ ምላሽ የሰጡት የሶማሌ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ኢድሪስ ኢስማኤል ሶማሌ ክልል ውስጥ የሌላ የማንም ብሄር ብሄረሰብ አባል የሆነ ነዋሪ አንድም አለመነካቱንና ሰዎቹ እየወጡ ያሉት በፈቃዳቸው ነው ቢሉም ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ግን የምንፈርመው ተገድደን እንጂ መውጣት ፈልገን አይደለም ብለዋል።

እንዲያውም የልዩ ፖሊስ አባላት ቤት ለቤት እየዞሩ ትዕዛዝ እንደሰጧቸውና መጠጊያ ፍለጋ ሸሽተው በገቡባቸው የጦር ካምፖች ውስጥ ሁሉ ሳይቀር የደበደቧቸው መሆኑን፤ የተገደሉ ሁለት ሰዎችን በሸራ ጠቅልለው ሲወስዷቸው ማየታቸውን አንድ ተፈናቃይ ተናግረዋል።

አቶ ኢድሪስ በሰጡት ተጨማሪ መረጃ በአስራ አንድ የሶማሌ ወረዳዎች አካባቢዎች ውስጥ በተሠነዘሩ ጥቃቶች እስካሁን የሁለት መቶ አስራ ሦስት ሰው ህይወት መጥፋቱንና አርባ አንድ ሰው መቁሰሉን ገልጸዋል።

ጥቃቶቹን በኦሮሚያ ወረዳዎች ላይ እያደረሰ ያለው የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ነው መባሉንም አቶ ኢድሪስ አስተባብለው የኦሮሚያን ከፍተኛ አመራር አባላት የዘር ፍጅት በመምራት ወንጅለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ ይህንን ክሥ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አቋም ነው ብለው እንደማያምኑ ጠቁመው “የራሳቸውን ጥፋት ለመሸፋፈን የሚሉት፣ ኃላፊነት የጎደለውና ከአቶ ኢድሪስ የአቅም ብቃት ማነስ የመነጨ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events