Basic

Goolgule.com: የከረረው የአሜሪካና የህወሓት “ወዳጅነት ተበጥሷል”

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Tuesday, 20 February 2018

የከረረው የአሜሪካና የህወሓት “ወዳጅነት ተበጥሷል”

 
  • አጋራችን ብትሆኑ ኤምባሲችን ወደየሩሳሌም እንዲዛወር ድምፅ ትሰጡ ነበር – አሜሪካ ለህወሓት

ህወሓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳያውጅ በጌቶቹ ከተነገረው በኋላ በራሱ መንገድ መሄዱ የግንኙነት “ገመዱን እንደበጠሰው” ተነገረ። አሜሪካ ኤምባሲዋ ወደየሩሳሌም እንዳይሄድ የተቃወሙ አገራትን ዋጋ ትከፍላላችሁ ያለችውን በህወሓት ላይ ተግብራዋለች። አውሮጳውያን የጠነከረ ተቃውሟቸውን በህወሓት ላይ በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚያሰሙ ይጠበቃል።

በባራክ ኦባማ አስተዳደር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ቶም ማሊኖውስኪ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የአገሪቱን ሁኔታ የገለጹበትን አስመልክቶ ጎልጉል ይህንን መዘገቡ ይታወሳል። ለለውጥ የተገባውን ቃል ተግባራዊ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥትብቸኛ ሃላፊነት ነው፤ … በኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ ሥርዓቱን ለዝነተ ዓለም ለማፅናት በሚደረግ ትግል ወይንም ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በሚወሰድ እርምጃም ሊሆን አይገባም፤ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ሥልጣን ማስረከብ ደረጃ ሊደረስ ይችላል” ካሉ በኋላ ሲቀጥሉም “እንደ ወዳጅ መክረናል … ምክንያቱም … ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ቢፈጠር ሙሉ ምስራቅ አፍሪቃ ምን ሊከተል እንደሚችል ስለምናውቅ … ነው” ብለው ነበር። “አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ይመስላል። እናም እንዲህ የሚንተከተክ ማሰሮ ለማስተንፈስ ያለው ምርጫ ክዳኑን ማንሳት ብቻ ነው፤ ያ ካልተደረገ መንተከተኩ አያቆምም። በዚያ ከቀጠለ ደግሞ መገንፈሉ አይቀርም። ከዚያ በኋላ የሚሆነው ሁላችንም እናውቀዋለን” ብለው ነበር።

ህወሓት/ኢህአዴግ “በአሻባሪነት” ስም በሶማሊያ የሚያደርገው ማስፈራሪያ ጊዜው ያለፈበት ይመስላል። የህወሃትና የአልሸባብ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል አርባ ምንጭ የሰው-አልባ አሮፕላን ማረፊያ (ድሮን ቤዝ) ማቋቋም ደርሳ የነበረችው አሜሪካ ከህወሓት ጋር ያላትን ፕሮጀክት ያጠናቀቀች ይመስላል “ሶማሊያ ውስጥ … በኮንዶም አንዋጋም!” እያለ የሚያምታታ መለስ የሌለው ህወሃት/ኢህአዴግ ቁንጮውን ብቻ ሳይሆን ከበረሃ ጀምሮ ሲያግዙት የነበሩትን “ነጭ ወያኔዎችም” እያጣ ነው። ይህም ከሌሎች የአሜሪካ ማስጠንቀቂያዎችና ምክሮች ጋር ተዳምሮ የግንኙነት ገመዱ እንዲበጠስ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው።

ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ሁሉ ግምገማ በማካሄድ ራሱን ሲያብጠለጥል የኖረው ህወሓት/ኢህአዴግ እንደከዚህ በፊቱ በቃል ደረጃ ሟቹ መለስ እንዳለው “እስከ እንጥላችን ገምተናል” ባይልም ከዚያ ባልተለየ አገላለጽ አመራሩ እንደከሸፈ በገሃድ መስክሯል። ይህንን ካለ በኋላ ግን መላው አመራር ከያዘው ሥልጣን መነሳት ሲገባው ይኸው በመለስ አጠራር “እስከ እንጥሉ የገማው” አመራር በሥልጣኑ ላይ አንዳች ለውጥ ሳያደርግ ቀጥሏል።

በተደጋጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በአገሪቱ ውስጥ የተነሳውን የተቃውሞ ማዕበል ለማብረድ ህወሓት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም። ከጥቂት ወራት በፊት የተነሳውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ አገርሽቷል። በየአቅጣጫው ዜጎች ያነሱትን ጥያቄ በግድያና በእስር ለመመለስ የሞከረው ህወሓት ሕዝባዊ ጽናትና የHR 128 ጡንቻ ተባብረውበት “አሸባሪ” እያለ ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች ለመፍታት ተገድዷል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ የተለያዩ ማባበያዎችንና ማስፈራሪዎችን ለመጠቀም የሞከረው ህወሓት “እኛ ከተነሳን አልሸባብ ሶማሊያን ይቆጣጠራል፤ ቀጣናው ሰላም አልባ ይሆናል፤ …” የሚሉትን ራሱን የአሜሪካ እውነተኛ አጋር አድርጎ ለማቅረብ የሄደበትም መንገድ አልሠራለትም። እንዲያውም ሌላ አቧራ አስነስቶበታል።

የትራምፕ አስተዳደር በእስራኤል የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደየሩሳሌም እንዲዛወር ውሳኔ ካደረገ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ ድምፅ ሰጥቶበት ነበር። ኢየሩሳሌም ዓለምአቀፋዊ ከተማ ከመሆኗ አንጻር ኤምባሲው ወደዚያ እንዳይዛወር የመንግሥታቱ ድርጅት ያቀረበውን ሃሳብ ኢትዮጵያን ጨምሮ 128 አገራት ሲደግፉ አሜሪካንን ጨምሮ 9 አገራት ብቻ ተቃውመውታል። ከአፍሪካ ደቡብ ሱዳን፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎች አገራት ድምጸ ተዓቅቦ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከአሜሪካ ዕርዳታና ድጎማ እያገኙ አሜሪካንን መደገፍ ሲገባቸው የመንግሥታቱን ድርጅት በመደገፍ አሜሪካንን የተቃወሙትን 128 አገራት አስመልክቶ “ዋጋ እንደሚከፍሉ” በወቅቱ ከትራምፕ አስተዳደር ተነግሮ ነበር።

በምዕራባውያን የበጀት ድጎማና ዕርዳታ ኅልውናው የታሠረው ህወሓት ጌቶቹ የሚያዙትን በተግባር መፈጸም ግዴታው ከሆነ ሰነባብቷል። በአሜሪካ በኩል ያለውን የጠነከረ አቋም ለማለሳለስ፤ “እኛ ብቸኛ የአሜሪካ ጥቅም አስከባሪና አጋር ነን” በማለት በሹሞቹ በኩል ለማሳመን ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም። “አጋራችን ብትሆኑ ኖሮ ኤምባሲያችን ወደየሩሳሌም እንዲዛወር ያቀረብነውን ሃሳብ በተበባበሩት መንግሥታት ፊት ትደግፉ ነበር” በማለት “ተገቢ” ምላሽ እንደተሰጣቸው ጎልጉል ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በመሆኑንም ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተቀባይነት እንደማይኖረው የተነገረው ህወሓት ከምዕራባውያን የተሰጠውን ትዕዛዝ ሳይቀበል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ይህ እንደተሰማ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከዚህ በፊት ከሚያወጣው መግለጫ ለየት ባለ መልኩ የህወሓትን አስቸኳይ ጊዜአ አዋጅ “አጥብቆ” ተቃውሞታል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይልቅ ሊሰጥ የሚገባው “ምላሽ ነጻነትን በማሳነስ ሳይሆን በማብዛት” መሆን እንዳለበት ኤምባሲው እንደሚያምን በመግለጫው ጠቁሟል። ይህ የኤምባሲው አቋም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ (ስቴት ዲፓርትመንት) ውሳኔ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን እስካሁን ከወጡት መግለጫዎች በዓይነቱም በይዘቱና በቃላት አጠቃቀሙ ጠንከር ያለ ሆኗል።

ይህንን የአሜሪካ አቋም ተከትሎ በዚህ በያዝነው ሳምንት ውስጥ የአውሮጳ ኅብረት፣ እንደ ጀርመን ያሉ አገራት በተናጠል እንዲሁም ካናዳ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ ጎልጉል ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የጌቶቹ የተጠናቀረ ተቃውሞ ያሳሰበው ህወሓት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ተቃውሞውን ሰምቶ ያወጣውን አዋጅ ከሰረዘ ተሸናፊነቱን የሚያሳይ ይሆናል። አሻፈረን ብሎ ከገፋበትም ከድርጎ ሰፋሪዎቹ ጋር ሊቆራረጥ ነው። ስለዚህ “መንግሥት ይህንን (የአስቸኳይ ጊዜ) ውሳኔ በሚቀጥሉት 15ቀናት ለብሔራዊ ፓርላማ በማቅረብ ያስጽድቃል” በማለት በዕንጥልጥል ሊተወው ይችላል የሚል ግምት ይሰጣል።

ከመለስ ሞት በኋላ በህወሓትና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚከታተሉ እንደሚሉት፤ አሜሪካ በተደጋጋሚ በገሃድም ይሁን በምስጢር ህወሓትን ስትመክር ቆይታለች። ከዚህ በኋላም እንዲሁ በምክርና በመግለጫ ብቻ መቀጠሏ የማይታይ ከመሆኑ የተነሳ ነው “የህወሓት እና የአሜሪካ የግንኙነት ገመድ ተበጥሷል” በማለት የመረጃው ባለቤቶች ለጎልጉል ለመናገር የደፈሩት። ይህ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ በአገር ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል በአስቸኳይ ከውጪው ጋር በቅንጅት በመሥራት የጌቶቹ ድጋፍ እየተነፈገ ያለውን ህወሓት/ኢህአዴግን እንዳይመለስ አድርጎ መሸኘት ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል።  (ፎቶ: በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events