Basic

Goolgule.com: ወርቅነህ አሜሪካኖችን “ምረጡኝ፤ አስመርጡኝ” ያለበት የጠ/ሚ ምርጫ ተውኔት ይፋ ሆነ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 22 February 2018

ወርቅነህ አሜሪካኖችን “ምረጡኝ፤ አስመርጡኝ” ያለበት የጠ/ሚ ምርጫ ተውኔት ይፋ ሆነ

 
  • እነ ለማ የሚያራምዱት የጽንፍ ፖለቲካ ነው – ወርቅነህ

ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” ለአሜሪካኖች “እኔ እንድመረጥ ድጋፍና ጫና ብታደርጉ የናንተን ፍላጎት ለማሳካት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነኝ” በማለት አሜሪካኖችን ሲወተውት እንደነበር ታወቀ። እርሱን እንዲመርጡ ድጋፍ ለመጠየቅ መነሻ አድርጎ ያቀረበው ሃሳብ “እነ ለማ ‹ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ› ቢሉም የሚያራምዱት የጽንፍ ፖለቲካ ነው፤ ከአማራው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢመደብ ወደ አማራ ማድላቱ አይቀርም፤ ከሁለቱም ያልሆነ እንደእኔ ያለ ሰው መመረጥ አለበት” የሚል ነው።

በግልጽ በማይነገር የጄኔራልነት ማዕረግ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” ይህንን ያለው ሰሞኑን በአሜሪካ ቆይታው ከፖሊሲ አውጪዎችና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ተገኝቶ ስለወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታና መፍትሄ ማብራሪያ ሲሰጥ ነው። ወርቅነህ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኒኪ ሄይሊ እንዲሁም ከሌሎች የአሜሪካ ፖሊሲ አማካሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሃላፊዎችና በፖለቲካው መስመር ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጋር መገናኘቱ በይፋ የተዘገበ ነው።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የጎልጉል የመረጃ ምንጭ እንዳሉት ወርቅነህ “ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ምረጡኝ፣ አስመርጡኝ፣ እኔ ነኝ መካከለኛ ሰው … አሜሪካ የምትፈልገውን ጥቅም ሁሉ አስከብራለሁ” በማለት በገሃድ ሲናገር ለሰሚዎቹ አስገራሚ ከመሆን አልፎ አስደንጋጭም ነበር። እጅግ ውድ የሆነውን ሮሌክስ ሰዓቱን እያሻሸ የአስመርጡኝ ዘመቻውን ለማካሄድ የሞክረው ወርቅነህ “እኛ ማንም እንዲመረጥ የምናደርገው ነገር የለም” ተብሎ ከተማመነባቸው ጌቶቹ ሲነገረው በትኩሱ አልቦት ነበር።

“ኦሮሞ ነኝ እያለ ነገር ግን ኦህዴድን ወክሎ ይህንን መናገሩ አስገራሚ ነው” ያሉት የመረጃ አቀባይ “እኔ ነኝ መካከለኛው ሰው” በሚለው ንግግሩ ትግሬ መሆኑንንም ማረጋገጫ እንደሰጠ የገባው አይመስልም። ይህ ለሥልጣን ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ገና ካሁኑ እንዴት ጭፍን አምባገነን እንደሆነ ጠቋሚ ነው ብለዋል። አያይዘውም “ይህ ጥሩ የዲክታተር ምሳሌ ነው” ሲሉም ተሳልቀውበታል።

በኦህዴድ እየማለ፣ ኦህዴድን የጽንፍ ፖለቲካ አራማጅ አድርጎ ሲሸቅጥ የነበረው ወርቅነህ ይህንን እንዲያደርግ ከህወሃት ፈቃድ ስለማግኘቱ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ የህወሃት የማህበራዊ ገጽ አራጋቢዎችና ተላላኪዎች ወርቅነህ እንዲመራ ምኞታቸውን፣ ማስታወቂያቸውን፣ ተልዕኳቸውን በስፋት እያሰሙ ነው። በነካ እጃቸው ኒኪ ሄሊን “የትራምፕ ውሽማ/ዕቁባት” በማለት ሲሳደቡ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካንን አምባሳደር “ጂኦግራፊ ተማር በሉት” የሚል ስድብ ሲያሰራጩ ቆይተዋል።

“ከሻሸመኔ ድንገት ተስፈንጥሮ ፖሊስ የሆነው ወርቅነህ ስሙን የቀየረ፣ ብሄሩ ኦሮሞ ያልሆነ በሚል ተቃውሞ ያልተለየው፣ የበርካታ ንጹሃን ደም እጁ ላይ ያለበት የህወሃት ኮማንዶ ነው። በኦሮሞ ስም የተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ሲደንስና ደም ሲያፈስ ኖሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመሆን በቃ፣ ይህንን ያህል የሚነግድበትን ድርጅት ‘ጽንፈኛ’ ሲል ቆመረበት” በማለት ለጎልጉል መረጃ ያቀበሉ እንዳሉት እነ ለማ መገርሳም ሆኑ ድርጅቱ ይህንን አንስተው ማብራሪያ ቢጠይቁ ወይም በመጠየቅ ተጨባጭ መረጃ ማግኘት ከፈለጉ ድጋፍ ሊያደርጉ ዝግጁ ናቸው።

ራሱን “ብልጣ ብልጥ” አድርጎ የወሰደው ሮሌክስ አድራጊው “ሸበላው”ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ”፤ በአቀራረቡ ሲሳቅበትና የማጣፊያ መልስ ሲሰጠው ጉዳዩን “ክፍተቱን የመሙላት ነው” ሲል እራሱን ብቸኛ አማራጭ ለማድረግ መገደዱን፣ እሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን የኦሮሞ ጉዳይ ምላሽ እንደሚያገኝ፣ ሰላም እንደሚፈጠርና አሜሪካም የምትፈልገው ጥቅሟ ያለአንዳች ገደብ እንደሚከበር ያለእፍረት በገሃድ ደስኩሯል። እንዲህ ዓይነቱን ድፍረት የሰጠው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ከመለስ ሞት በኋላ በዓለምአቀፍ ግንኙነት ላይ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቀንሷል” በማለት በቅርቡ በአገር ውስጥ በሰጠው መግለጫ ላይ ራሱን “አዲሱ መለስ” አድርጎ ለማቅረብ ከመሞከሩ ጋር የሚያገናኙትም አሉ።

በ“ትንታኔው” ሲደመሙ የነበሩት አድማጮች ወርቅነህ በዲፕሎማሲው መስክ በገሃድ የሚጠየቁና ከመጋረጃ በስተኋላ የሚደረጉ ጉዳዮችን በቅጡ ያልተረዳ እንጭጭ መሆኑን ከመታዘብ አልፈው የአስተሳሰቡን ኮሳሳነት በውል ለመረዳት አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። በምክትል ሊቀመንበርነት የሚመራውን ኦህዴድ “ጽንፈኛ” ብሎ ከፈረጀ በኋላ ራሱን ክፍተት መሙያ ማድረጉ በአሜሪካውያኑ ዘንድ ከማስገረሙም በላይ አስቂኝ ተውኔት ሆኖ መሰንበቱ ጎልጉል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

(የመግቢያ ፎቶ፤ በስተግራ ካሣ ተክለብርሃን ቀጥሎ ወርቃማ ሰዓቱ የሚታየው ወርቅነህ ከርሱ ቀጥሎ (ተሸፍኗል) በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ዳይሬክተር ፒተር ፓም፤ የአትላንቲክ ካውንስል በጠራው ስብሰባ ላይ ወርቅነህ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ፊት ስለ ህወሓት “ቅዱስነት” ሲናገር፤ በቀኝ በኩል ያለው ወርቅነህ “ኧረ ባካችሁ ምረጡኝ ወይም አስመርጡኝ” በሚል መልኩ የአሜሪካዋን አምባሳደር ኒኪ ሄይሊን ሲለምን)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events